በ2025 የአፍሪካ አስር ወታደራዊ ኃያል አገራት፣ ኢትዮጵያ ስንተኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች?

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ተቀማጭነቱ በአሜሪካ የሆነው ግሎባል ፋየር ፓወር ኔትዎርክ (ጂኤፍፒ) የዓለም አገራት ባላቸው የጦር መሳሪያ መጠን፣ በሠራዊት ብዛት እና ጥንካሬ፣ በችሎታ፣ በበጀት አቅም፣ በመልክአ ምድራዊ አቀማመጥ እንዲሁም ባላቸው ሃብት ላይ በመመሥረት በየዓመቱ ደረጃ ያወጣል።
የአገራትን አጠቃላይ ወታደራዊ አቅም ከተለያዩ መስኮች አንጻር በመገምገም ተቀባይነት ያለው ግሎባል ፋየር ፓወር በየዓመቱ ከሚያወጣው ሪፖርት የአውሮፓውያኑ 2025ን የ145 አገራትን ወታደራዊ ጥንካሬ በመገምገም የሰጠውን ደረጃ ይፋ አድርጓል።
በተጨማሪም የአገራቱ ወታደራዊ አቅም ከሌሎች አገራት ጋር ባላቸው ትብብር፣ የዲፕሎማሲ ግንኙነት እና በሚጠቀሙት ወታደራዊ ቴክኖሎጂ አማካኝነት ይወሰናል።
የአፍሪካ አገራትም የግዛት እና የሕዝባቸውን ደኅንነት ለመጠበቅ እንዲሁም በውስጣቸው ያሉ ታጣቂ ቡድኖችን ለመቆጣጠር ከምጣኔ ሀብታቸው አንጻር ከፍተኛ በጀት በመመደብ የሰው ኃይላቸውን በማሠልጠን፣ ወታደራዊ መሠረተ ልማቶችን በመግንባት እና በማዘመን እንዲሁም ዘመናዊ የጦር መገልገያዎችን በመታጠቅ ላይ ይገኛሉ።
ግሎባል ፋየር ለአውሮፓውያኑ 2025 ዓመት ባወጣው የዓለም አገራት ወታደራዊ አቅም ደረጃ ውስጥ ከተካተቱት የአፍሪካ አገራት መካከል ቀዳሚ የሆኑትን አስር ኃያል አገራት የሚከተሉት ናቸው።
10ኛ ሊቢያ
ሰሜን አፍሪካዊቷ በነዳጅ ሀብት የበለጸገችው ሊቢያ ረጅም ዓመታት የመሯት መሪዋ የሙአማር ጋዳፊ መንግሥት ከወደቀ በኋላ በእርስ በርስ ጦርነት ውስጥ ብትሆንም በወታደራዊ አቅሟ ከአፍሪካ በአስረኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች።
ሊቢያ በዓለም ደረጃ በወታደራዊ ኃይሏ 76ኛ ደረጃ ላይ የምትገኝ ሲሆን፣ ምንም እንኳን አገሪቱ በእርስ በርስ ጦርነት ክፉኛ ብትጎሳቆልም በምትገኝበት ስትራተጂካዊ ቦታ እና ባላት የተፈጥሮ ሀብት ምክንያት በሠንጠረዡ ላይ ከፍ ብላ ለመቀመጥ ችላለች።
ሊቢያ የምድር ጦር፣ የአየር ኃይል እና የባሕር ኃይል ያላት ሲሆን፣ ከ30 ሺህ በላይ መደበኛ ሠራዊት አላት።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
9ኛ ሱዳን
በሰሜን ምዕራብ በኩል ከኢትዮጵያ ጋር የምትጎራበተው ሱዳን ላለፉት ሁለት ዓመታት በእርስ በርስ ጦርነት ውስጥ የምትገኝ ሲሆን፣ ባላት ወታደራዊ አቅም ከአፍሪካ 9ኛ እንዲሁም በዓለም ደግሞ 73ኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች።
የሱዳን ጦር ኃይል ከፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ ጋር በሚደረግ የእርስ በርስ ጦርነት ውስጥ ሆኖ ከባድ ፈተና የገጠመው እና አገሪቱም በከባድ ፖለቲካዊ ቀውስ ውስጥ ብትገኝም ሠራዊቷ በአፍሪካ ጠንካራ ከሚባሉት ውስጥ ይገኛል።
ሱዳን የምድር ጦር፣ የአየር ኃይል እና የባሕር ኃይል ያላት ሲሆን፣ ከ90 ሺህ በላይ መደበኛ ሠራዊት አላት።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
8ኛ ዲሞክራቲክ ኮንጎ
የዲሞክራቲክ ኮንጎ ሠራዊት በተለይ በአገሪቱ ምሥራቃዊ ክፍል ውስጥ ከሚንቀሳቀሱት አማጺያን ጋር እየተዋጋ የቆየ ቢሆንም በጥንካሬው በአፍሪካ ስምንተኛ፣ በዓለም 66ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።
በማዕድን ሀብቷ የበለጸገችው ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ የወታደራዊ ኃይሏ ጥንካሬውን ያገኘው በዓለም አቀፍ ትብብር ከሚያገኘው ድጋፍ እና አገሪቱም በምትመድበው በጀት ነው።
ዲሞክራቲክ ኮንጎ የምድር ጦር፣ የአየር ኃይል እና የባሕር ኃይል ያላት ሲሆን፣ ከ160 ሺህ በላይ መደበኛ ሠራዊት አላት።

የፎቶው ባለመብት, AFP
7ኛ ሞሮኮ
ከአውሮፓ ጋር የምትዋሰነው ሰሜን አፍሪካዊቷ ንጉሣዊት አገር የሞሮኮ ወታደራዊ ኃይል በአፍሪካ በሰባተኛ ደረጃ ላይ ሲቀመጥ ከዓለም አገራት ደግሞ 59ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።
ሞሮኮ ወታደራዊ ኃይሏን በሰው እና በትጥቅ በየምታጠናክረው በተለይ የድንበር ጥበቃዋን ለማጠናከር እና በምዕራብ አፍሪካ የሚንቀሳቀሱ የሽብር ቡድኖችን ለመቆጣጠር ነው።
ሞሮኮ ባላት ጠንካራ ምጣኔ ሀብት እና ከምዕራባውያን ጋር ባላት ጠንካራ ዲፕሎማሲያዊ እና የመከላከያ ትብብር አማካኝነት ጠንካራ ሠራዊት ለመገንባት ችላለች።
ሞሮኮ የምድር ጦር፣ የአየር ኃይል እና የባሕር ኃይል ያላት ሲሆን፣ 200 ሺህ የሚጠጉ የመደበኛ ሠራዊት አባላት አላት።

የፎቶው ባለመብት, FMSO
6ኛ አንጎላ
ደቡብ አፍሪካዊቷ አገር አንጎላ በወታደራዊ ኃይሏ ጥንካሬ በዚህ ዓመት በአፍሪካ ስድስተኛ በዓለም 56ኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች። የአንጎላ ጦር ኃይል ጥንካሬ ምንጭ አገሪቱ ከነዳጅ ሀብቷ ከምታገኘው ገቢ በምትመድበው በጀት ነው።
አንጎላ ጦር ሠራዊቷን በማጠናከር በአፍሪካ ኃያል ከሚባሉት አገራት ጋር እንዲሰለፍ ያደረገችው በአገር ውስጥ ሊያጋጥሟት የሚችሉ የደኅንነት ስጋቶችን ለመቋቋም በሚል ነው።
አንጎላ የምድር ጦር፣ የአየር ኃይል እና የባሕር ኃይል ያላት ሲሆን፣ ወደ 110 ሺህ የሚጠጋ መደበኛ ሠራዊት አላት።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
5ኛ ኢትዮጵያ
ኢትዮጵያ በጦር ኃይል ጥንካሬ በአፍሪካ የአምስተኛ ደረጃ ላይ የምትገኝ ሲሆን፣ በዓለም ደግሞ 52ኛ ደረጃን ይዛለች። ኢትዮጵያ ግዙፍ ሠራዊት የገነባችው በአገር ውስጥ ደኅንነት ለማስጠበቅ እና በቀጠናዊ የደኅንነት ሁኔታ በተለይም በአፍሪካ ቀንድ ያሉትን ግጭቶች መሠረት በማድረግ ነው።
ኢትዮጵያ ሠራዊቷን ዘመናዊ የጦር መሳሪያዎች ለማስታጠቅ፣ ወሳኝ ወታደራዊ መሳሪያዎችን ለመሥራት እና የሠው ኃይሏን ለማሠልጠን ከፍተኛ መዋዕለ ነዋይ ታፈሳለች።
ኢትዮጵያ ከተለያዩ አገራት ጋር ባላት ወታደራዊ ትብብር አማካኝነትም የሠራዊቷን አቅም በማጠናከር ላይ የምትገኝ ሲሆን፣ በአፍሪካ ቀንድ አካባቢ በወታደራዊ አቅሟ ቀዳሚዋ ናት።
የኢትዮጵያ ጦር በዋናነት በአገር ውስጥ የሚንቀሳቀሱ ታጣቂ ቡድኖችን ለመቆጣጠር የሚሰማራ ሲሆን፣ አገሪቱ በሌሎች አገራት የሰላም ማስከበር ተልዕኮዎች ውስጥም ሠራዊቷን በመላክ ዋነኛዋ ናት።
ኢትዮጵያ የምድር ጦር፣ የአየር ኃይል እና የባሕር ኃይል ያላት ሲሆን፣ ከ160 ሺህ በላይ መደበኛ ሠራዊት አላት።

የፎቶው ባለመብት, AFP
4ኛ ደቡብ አፍሪካ
በአፍሪካ በጠንካራ ምጣኔ ሀብቷ የምትታወቀው ደቡብ አፍሪካ ባላት ወታደራዊ ኃይል ጥንካሬ በአህጉሪቱ በአራተኛ ደረጃ ላይ የምትገኝ ሲሆን፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ በ40ኛ ላይ ተቀምጣለች።
ባሏት እጅግ ዘመናዊ የመከላከያ ኢንዱስትሪዎቿ የምትታወቀው ደቡብ አፍሪካ፣ ለጦር ሠራዊቷ የሚያስፈልጓትን አብዛኞቹን ትጥቆች እና መገልገያዎች ራሷ ናት የምታመርተው።
ደቡብ አፍሪካ የምድር ጦር፣ የአየር ኃይል እና የባሕር ኃይል ያላት ሲሆን፣ ከ70 ሺህ በላይ መደበኛ ሠራዊት አላት።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
3ኛ ናይጄሪያ
ምዕራብ አፍሪካዊቷ አገር ናይጄሪያ ባላት የወታደራዊ ኃይል ጥንካሬ በአፍሪካ ሦስተኛ ስትሆን፣ በዓለም ደግሞ 31ኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች።
ሠራዊቷን በግዛቷ ውስጥ የሚንቀሳቀሱ አማጺያን እና የሽብር ቡድኖችን ለመቋቋም የገነባቸው ናይጄሪያ ከነዳጅ ምርቷ ከምታገኘው ገቢ ከፍተኛ መዋዕለ ነዋይ መድባ አጠናክራዋለች።
ናይጄሪያ የምድር ጦር፣ የአየር ኃይል እና የባሕር ኃይል ያላት ሲሆን፣ ከ230 ሺህ መደበኛ ሠራዊት አላት።

የፎቶው ባለመብት, AFP
2ኛ አልጄሪያ
ሰሜን አፍሪካዊቷ አገር አልጄሪያ በጦር ሠራዊት ጥንካሬ ከአፍሪካ በሁለተኛ ደረጃ፣ እንዲሁም ከዓለም ደግሞ 26ኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች።
የአልጄሪያ ጦር ሠራዊት ጥንካሬ የተገነባው አገሪቱ ከምታገኘው የነዳጅ ዘይት ገቢ በምትመድበው በጀት አማካኝነት ሲሆን፣ ይህም ወታደራዊ ኃይሉ ዘመናዊ ትጥቅ እና በደንብ የሠለጠነ ሠራዊት እንዲኖረው አድርጓል።
አልጄሪያ የምድር ጦር፣ የአየር ኃይል እና የባሕር ኃይል ያላት ሲሆን፣ ከ325 ሺህ መደበኛ ሠራዊት አላት።

የፎቶው ባለመብት, AFP
1ኛ ግብፅ
ከመካከለኛው ምሥራቅ ጋር በመዋሰን በሰሜን አፍሪካ የምትገኘው ግብፅ በወታደራዊ ኃይል ከአፍሪካ ቀዳሚዋ አገር ስትሆን፣ በዓለም ደግሞ በ19ኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች።
ግብፅ ወታደራዊ ኃይሏን ለማጠናከር ከአሜሪካ የምትገኘውን ከ1.5 ቢሊዮን ዶላር ዓመታዊ ወታደራዊ ድጋፍን ጨምሮ ከሌሎች አገራትም ከፍተኛ መጠን ያለው ወታደራዊ እርዳታን ታገኛለች።
የግብፅ ሠራዊት ግጭት በማይለው የመካከለኛው ምሥራቅ አካባቢ የምትገኘውን የአገሪቱን ደኅንነት ከመጠበቅ ባሻገር በአገር ውስጥም ታጣቂዎችን ለመቆጣጠር ይሰማራል።
ግብፅ የምድር ጦር፣ የአየር ኃይል እና የባሕር ኃይል ያላት ሲሆን፣ 440 ሺህ መደበኛ ሠራዊት አላት።












