እስራኤላዊያን መንግሥት ከሐማስ ጋር በመደራደር ታጋቾችን እንዲያስለቅቅ በሰልፍ ጠየቁ

በቴል አቪቭ ፖሊስ ሰልፈኞችን ለመበተን ውሃ ሲጠቀም

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የምስሉ መግለጫ, በቴል አቪቭ ፖሊስ ሰልፈኞችን ለመበተን ውሃ ተጠቅሟል

በሐማስ ተይዘው የነበሩ ስድስት ታጋቾች አስክሬን በጋዛ መገኘቱን ተከትሎ በእስራኤል ከፍተኛ ቁጣ ተቀስቅሷል።

የእስራኤል መንግስት ታጋቾችን ለማስለቀቅ ከስምምነት እንዲደርስ በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በሰልፍ ጠይቀዋል።

በቴል አቪቭ፣ እየሩሳሌም እና ሌሎች ከተሞች በተካሄዱ ሰልፎች በርካቶች የእስራኤልን ሰንደቅ ዓላማ ለብሰው ታይተዋል።

ሰልፈኞቹ በሐማስ የታገቱ ሰዎችን ለማስለቀቅ ቤንያሚን ኔታኒያሁ እና እሳቸው የሚመሩት መንግሥት በቂ ሥራ አልሰራም ሲሉ ወቅሰዋል።

ትላንት ዕሁድ የተካሄደው ሠልፍ በአመዛኙ ሰላማዊ የነበረ ቢሆንም የቴል አቪቭን ዋና ጎዳና ሰልፈኞች እንዳይተላለፉ ፖሊስ ያስቀመጠውን ማገጃ ጥሰው የገቡ ሰዎች ታይተዋል።

ይህ ከመሆኑ አስቀድሞ በእስራኤል የሚገኘው ትልቁ የሠራተኞች ማኅበር ዛሬ ሰኞ ሀገር አቀፍ የሥራ ማቆም አድማ ጥርቷል። የሥራ ማቆም አድማው ታጋቾችን ለማስለቀቅ ከስምምነት እንዲደረስ መንግስት ላይ ጫና ለማድረግ ያለመ ነው።

ከትላንቱ ሰልፍ አንድ ቀን አስቀድሞ ቅዳሜ በደቡባዊ ጋዛ ራፋህ በሚገኝ ከምድር ስር ባለ ዋሻ የ6 ታጋቾችን አስክሬን ማግኘቱን የእስራኤል መከላከያ ኃይል ገልጾ ነበር።

የእስራኤል ጦር፤ ታጋቾቹ የእስራኤል ወታደሮች ቦታው ለመድረስ ጥቂት ሲቀራቸው መገደላቸውን አሳውቋል።

ይህ ክስተት ትላንት በእስራኤል በርካታ ከተሞች በ10 ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ለተቃውሞ አደባባይ እንዲወጡ ምክንያት ሆኗል። ሰልፈኞቹ የእስራኤለ መንግስት እና ጠቅላይ ሚኒስትር ኔታኒያሁን ደግሞ በግል የተቀሩትን ታጋቾች ለመታደግ ‘እዚህ ግባ’ የሚባል ሥራ አልሠሩም ሲሉ ኮንነዋል።

ሰልፈኞቹ “ታጋቾቹ በህይወት እንዲገኙ ነው የምንፈልገው” ሲሉ ጠይቀዋል።

አንድ ሰልፈኛ ይዞ የወጣው ጽህፉ ኔታኒያሁ ላይ ያነጣጠረ ሲሆን “[የመንግስቱ] ራስ አንተ ነህ። የምትወቀሰውም አንተ ነህ” ይላል።

አንዳንድ ሰልፈኞች መንገድ ላይ እሳት ያያዙ ሲሆን ለታጋቾቹ ያላቸውን አጋርነት ለመግለጽ ቢጫ ቀልም ያላቸው ጭርቆችን አሳይተዋል።

ከሰልፈኞቹ መካከል ልጁ በሃማስ የተያዘበት ኤሊ ሺቲቪ “ይህንን ውሳኔ የወሰኑ ሰዎች ከእንቅላፋቸው እንደሚነቁ ተስፋ እናደርጋለን” ብሏል።

ጨምሮም “ምንም ተጫማሪ ጊዜ የለንም። ልጄ በጣም ናፍቆኛል። ሁሉም ቤተሰብ የአጋቾቹ ሰለባ ሆኗል” ሲል ለቢቢሲ ተናግሯል።