እስራኤል በሐማስ ታግተው ሕይወታቸው ያለፉ የ6 ሰዎችን አስክሬን ከጋዛ ማስወጣቷን አስታወቀች

የፎቶው ባለመብት, Hostages Families Forum
የእስራኤል መከላከያ ኃይል በሐማስ ታግተው ሕይወታቸው ያለፈ የ6 ታጋቾችን አስክሬን ከጋዛ ማስወጣቱን አስታወቀ።
የእስራኤል ጦር እሁድ ንጋት ነሐሴ 26/2016 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ ስድስቱ ሰዎች መስከረም 26/2016 ዓ.ም. በሐማስ ድንገተኛ ጥቃት ታግተው ወደ ጋዛ የተወሰዱ ናቸው።
ታጋቾቹ በምን አይነት ሁኔታ ሕይወታቸው እንዳለፈ የተባለ ነገር ባይኖርም አስክሬናቸው በጋዛ ራፋህ አካባቢ ባለ ዋሻ ውስጥ ተደብቆ እንደነበረ ጦሩ አስታውቋል።
የእስራኤል ጦር አስክሬናቸው ወደ እስራኤል ግዛት የተመለሱት ሰዎች ካርሜል ጋት፣ ኢደን ዬሩሻለሚ፣ ሄራሽ ጎልድበርግ-ፖሊን፣ አሌክሳንደር ሎቫኖቭ፣ አለሞግ ሳሩሲ እና ማስተር ሳርጀንት ኦሪ ዳኒኖ ይባላሉ ብሏል።
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን፤ ጎልድበርግ-ፖሊን የተባለው ታጋች አሜሪካዊ መሆኑን ገልጸው በሕልፈተ ሕይወቱ ማዘናቸውን ገልጸዋል።

የፎቶው ባለመብት, Reuters
ፕሬዝዳንት ባይደን የሙዚቃ ፌስቲቫል ላይ እየታደሙ ሳሉ "በሐማስ ጭካኔ የተሞላበት ጥቃት ከተከፈተባቸው ሰላማዊ ሰዎች መካከል ጎልድበርግ-ፖሊን አንደኛው" መሆኑን ገልጸዋል።
ፕሬዝዳንቱ በጥቃቱ ወቅት ጎልድበርግ-ፖሊን ጓደኞቹን በሚረዳበት ወቅት እጁን በጉዳት ማጣቱን ገልጸዋል። የ23 ዓመቱ ወጣት ጎልድበርግ-ፖሊን ዓለምን የመዞር ሕልም እንደነበረው በመግለጫቸው ገልጸዋል።
የእስራኤል ጦር በመግለጫው ሁሉም ሟቾች መስከረም 26 ታግተው የተወሰዱ መሆናቸውን አስታውሶ፤ “ታጋቾቹ በአሸባሪው ሐማስ ጋዛ ውስጥ ተገድለዋል” ብሏል።
ጦሩ ጨምሮ የታጋቾቹ አስክሬን ወደ እስራኤል ግዛት መመለሱን ለሟች ቤተሰቦች ማስታወቁን ጨምሮ አስታውቋል።
ሐማስ መስከረም 26 በእስራኤል ድንገተኛ ጥቃት በከፈተ ወቅት ወደ 1ሺህ 200 ሰዎችን ገድሎ 251 ሰዎችን አግቶ ወደ ጋዛ መውሰዱ ይታወሳል።
ይህን ድንገተኛ ጥቃት ተከትሎ እስራኤል ሐማስ ላይ በከፍተችው ጦርነት አብዛኛዎቹ ሕጻናት እና ሴቶች የሆኑ 40ሺህ 500 ሰዎች በጋዛ ተገድለዋል፤ መሠረተ ልማቶች ወድመዋል እንዲሁም የከፋ ሰብዓዊ ቀውስ በጋዛ ተከስቷል።
እስራኤል እና ሐማስ ለሰብዓዊ ተግባራት የተኩስ አቁም ስምምነት እንዲያደርጉ አሜሪካ፣ ግብጽ እና ኳታር የማሸማገል ጥረቶችን ሲያደርጉ ቆይተዋል።
ከዚህ ቀደም ለቀናት በዘለቀ የተኩስ አቁም እና የእስረኛ ልውውጥ ስምምነት ሐማስ አብዛኛዎቹ ሴቶች እና አዛውንቶች የሆኑ 105 ሰዎችን መልቀቁ ይታወሳል።
በአሁኑ ወቅት ሐማስ፤ ሳይሞቱ አይቀሩም የተባሉ የ27 ሰዎችን አስክሬን ጨምሮ ከ97 በላይ ታጋቾችን እንዲለቅ የማደራደር ስራ እየተሰራ ይገኛል።
በምላሹ እስራኤል በእስር ቤቶቿ የያዘቻቸውን በርካታ ፍልስጤማውያንን ትለቃለች።












