የመድፈር ወንጀልን ስለሚፈጽሙ ሰዎች ያሉ አምስት የተሳሳቱ አመለካከቶች

በር የተደገፈ እጅ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ከአንድ ዓመት በፊት የመጀመሪያ ልጇ በቤት አከራይዋ ተደፍራ የተገደለችባት አበቅየለሽ አደባ የሰሞኑ የማህበራዊ ሚዲያ መነጋገርያ፣ የበርካታ መብት ተሟጋቾች ርዕሰ ጉዳይ ናት።

የሰባት ዓመቷን ሄቨን አወት ደፍሮ የገደለው ጌትነት ባዬ የተባለው ወንጀለኛ የ25 ዓመት እስረ ቅጣት ተጥሎበታል።

ይህ የፍርድ ቤት ውሳኔ ከተላለፈ በኋላ የተሰጠው ቅጣት በቂ አይደለም በሚል በበርካቶች ዘንድ ቁጣን ቀስቅሷል።

የሴቶች መብት ተከራካሪዎች እና ሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች ማኅበረሰቡ ስለ ደፋሪዎች ያለው የተሳሳተ አመለካከት ወንጀሉ እንዲስፋፋ ድርሻ እንዳለው ያምናሉ።

እነዚህ የመብት ተሟጋቾች የመድፈርን ወንጀል ስለሚፈጽሙ ሰዎች በስፋት የሚታመኑ ነገር ግን እውነት ያልሆኑ ጉዳዮች ብለው የለይዋቸውን አምስት ነጥቦች ለማየት እንሞክር።

የተሳሳተ አመለካከት 1፡ የመድፈር ወንጀል በማይታወቁ ሰዎች ይፈጸማል

የመድፈር ወንጀል ተጎጂዎች በማያውቁት ሰው፣ በአሳቻ ቦታ እና በጨለማ የሚፈጸም ወንጀል እንደሆነ በስፋት ይታመናል።

የጾታ እኩልነት እና የሴቶች መብት ባለሙያ የሆነችው ሕሊና ብርሃኑ ደገፋ፣ ይህ ሀሳብ የተሳሳተ ከመሆኑም በላይ ወንጀሉ እንዲስፋፋ እና ፍትህ እንዳይኖር ያበረታታል ትላለች።

“ሴት ልጆችን ማኅበረሰቡ ሲያሳድግ በዚህ መንገድ አትሂጂ፣ በጨለማ አትውጪ እያለ ይነግራቸዋል።ይህ የሚያሳየን ማኅበረሰቡ በአጠቃላይ መደፈርም ሆነ ወሲባዊ ጥቃት ሊደርስ እንደሚችል ስለሚያስብ ነው ” ትላለች።

የመድፈርን ወንጀል ስለሚፈጽሙ ሰዎች ያለው የተሳሳተ አመለካከት “ከቤት ስንወጣ የምናገኛቸው፣ ጓደኞቻችን፣ ቤት ስንሄድ ወይንም ደግሞ መዝናኛ ስፍራ ስንሄድ የሚገጥሙን ብቻ መምሰሉ ነው” ስትል ታክላለች።

ይኹን እንጂ በተጨባጭ የመድፈርን ወንጀል የሚፈጽሙ ሰዎች ተጎጂዎች በቅርበት የሚያውቋቸው ግለሰቦች ናቸው።

“በጥናት ጭምር የተረጋገጠው አባት፣ አጎት፣ ጎረቤት፣ የእንጀራ አባት እንዲሁም ይጠብቁናል ብለው የሚያስቧቸው ሰዎች ናቸው ይህንን ወንጀል የሚፈጽሙት።”

ሕሊና አንደምትለው ይህ ወንጀል “በቤታችን፣ በአቅራብያችን እና በምናውቃቸው ሰዎች የሚፈጸም ቢሆንም ሰው በሌለበት እና በድብቅ ነው የሚደረገው” ትላለች።

ለምን በዚህ መልኩ እንደሚፈጸም ስትገልጽም፣ የወንጀሉ ባህሪ ተጎጂዋን ረዳት አልባ ማድረግ፣ ማንነቷን መንጠቅ፣ ጉልበቷን እና የበላይነትን መውሰድ ነው" ትላለች።

የመድፈር ወንጀል በአብዛኛው ወደ ሕግ አስፈጻሚ አካላት ቀርቦ አይመዘገብም የምትለው ሕሊና፣ ይህ የሆነበት ዋናው ምክንያት ተጎጂዎች የበቀል ጥቃትን ስለሚፈሩ እና ወንጀሉ በሚቀርቡት ሰው ስለሚፈጸም "ድምጻቸውን" በመነጠቃቸው ነው።

የተባበሩት መንግሥታት ሪፖርት እና ሌሎች በዚህ ጉዳይ ላይ የተሰሩ ጥናቶች እንደሚያሳዩት 80 በመቶ የመድፈር ወንጀል ተጎጂዎች በሚያቁት ሰው የሚፈጸሙ ናቸው።

የተሳሳተ አመለካከት 2፡ የመድፈር ወንጀል የሚፈጽሙ ሰዎች የአእምሮ ሕመም አለባቸው

አሰቃቂ የሆነ የመድፈር ወንጀል በሴቶችም ሆነ በሕጻናት ላይ ሲፈጸም፣ ማኅበረሰቡ የወንጀል ፈጻሚውን የአእምሮ ጤንነት ይጠራጠራል።

ናሽናል ላይብረሪ ኦፍ ሜዲስን የተሰኘ የምርምር መጽሔት የመድፈርን ወንጀል በፈጸሙ ሰዎች ላይ ባደረገው ጥናት አብዛኛዎቹ የአእምሮ ጤና ችግር የሌለባቸው ሆነው ተገኝተዋል።

ይህንን ጥናት ያካሄዱት ባለሙያዎች “ምንም እንኳ እነዚህ ሰዎች የአእምሮ ጤና ችግር ያለባቸው ቢሆኑም የጤናቸው ችግር የመድፈር ወንጀል እንዲፈጽሙ አድርጓቸዋል ለማለት አንደማይቻል ይናገራሉ”

የመድፈር ድርጊት እና የአእምሮ ጤና ችግር ቀጥታ የሆነ ግንኙነት እንደሌላቸው ይገልጻሉ።

የጾታ እኩልነት ባለሙያዋ ሕሊና በበኩሏ “እንደ ማኅበረሰብ ተጠያቂነትን መውሰድ ስለማንፈልግ ይህንን ጉዳይ ከአእምሮ ሕመም ጋር እናያይዘዋለን" ትላለች።

ለዚህም ደግሞ እንደ ምክንያቷን ስታስረዳ ይህንን ወንጀል የፈጸመው ግለሰብ ጥፋትን የመፈጸም ውሳኔ መቀበል፣ እንደ ማኅበረሰብ ሁላችንም ላይ ተጠያቂነትን ስለሚያመጣ ነው በማለት ታብራራለች።

ይህንን ወንጀል የሚፈጽም ሰው “ከእኛ አንደ አንዱ” እንዳልሆነ በማቅረብ እና በመነጠል ራሳችንን ጤነኛ አእምሮ ያለን አድርገን በመቀበል ስለ ወንጀሉ ለአእምሯችን የምንነግረው “ውሸት” ነው ስትልም ሀሳቧን ታጠናክራለች።

የተሳሳተ አመለካከት 3- ወንዶች የወሲብ ስሜታቸውን “መቆጣጠር አይችሉም”

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ይህ አመለካከት የመድፈርን ወንጀል ስለሚፈጽሙ ሰዎች በስፋት የሚታመን ሌላኛው የተሳሳተ አመለካከት ነው።

ሕሊና “በመድፈር ወይንም ደግሞ ወሲብን ያለፈቃድ በመፈጸም ሊሟላ የሚችል የወሲብ ፍላጎት የለም” ትላለች።

ለዚህም ምክንያቷን ስታስረዳ መድፈር የግለሰቧን ሰውነት የመግፈፍ፣ የመገርሰስ በተለይም የሴትን ሰውነት የመቆጣጠር ጉዳይ ነው ትላለች።

ግብረ ስጋ ግንኙነት በሁለት ፈቃድ መስጠት በሚችሉ ሰዎች መካከል በፈቃድ የሚደረግ ጉዳይ እንደሆነም ታስረዳለች።

የበላይነት እና የመቆጣጠር ጉዳይ ስለመሆኑ በትግራይ ጦርነት ወቅት የተፈጠረውን በመጥቀስ እንደ ማስረጃ ታቀርባቸለች።

"ሁለት የሚዋጉ አካላት ከእነርሱ በተቃራኒ የነበሩ ሴቶችን ሆን ብለው ሲደፍሩ የነበረው፣ መልዕክት ለማስተላለፍ ነው። የእኔ የምላትን ሴት እንደፈለጉ አደርጋታለሁ። እቃ ናት፣ እጠቀምባታለሁ የሚሉ መልዕክቶችን ለማስተላለፍ ይሞክራሉ። በጦርነት ወቅትም እነደ ጦር መሳርያ ይጠቀሙበታል።"

ሕሊና ከዚህም ባሻገር ትላለች “ ‘በሰላሙ ጊዜ’ ስለ ሴት በየቋንቋችን በተለያየ መንገድ በማወቅም ሆነ ባለማወቅ የምናስተላልፋቸው መልዕክቶች የሴትን የበታችንት የሚሰብኩ እና የወንድን የበላይነት የሚያሳዩ ናቸው። በሌላ መንገድ ማኅበረሰብ እምነት እና ሀገር ሳይቀር የሴቶችን ሰውነት መቆጣጠር ይፈልጋሉ። በዚህም መንገድ የመድፈርን ወንጀል የሚፈጽሙ ወንዶች ምንም አይደለሽም፤ የማንም አይደለሽም፤ የእኔ አንኳን ባትሆኙ ልክ እንደ እቃ የኔ ነሽ በሚል አስተሳስብ ነው የበላይነታቸውን የሚፈጽሙት።"

ማኅበረሰብ አለባበሷ፣ አካኋና፣ የነበረችበት ቦታ፣ ያለችው ነገር ነው ወንዱን ለጥቃት ያነሳሳው የሚለው የእርሱ ፍላጎት በዚህ ሰዓት እንኳ ሳይቀር ከእርሷ እንደሚበልጥ ለማሳየት ነው ስትል ትሞግታለች።

“ወንድ እንደ እንስሳ ወሲብ ፍላጎቱን መቆጣጠር አይችልም" የሚለው አመለካከት በስፋት የሚታመን እንደሆነ ተናግራ፣ "ይሁን አንጂ ወንዶችም እንደ ማንኛውም ስሜታቸው፣ እንደ ንዴት እና ደስታቸው ሁሉ የወሲብ ስሜታቸውንም የሚቆጣጠሩት ጉዳይ ነው”

ይህንን ማድረግ አንደማይችሉ የሚያሳይ ምንም ዓይነት ማስረጃ የለም ስትል ሀሳቧን ታጠናክራለች።

በተለያየ ጊዜ ወሲባዊ ጥቃት ደርሶባቸው የተገደሉ ሴቶች

የተሳሳተ አመለካከት 4- እርሷ ናት ‘ያሳሳተችው”

በማኅበረሰቡ ውስጥ ስር የሰደደ ተበዳይን ወይንም ተጠቂን የመኮነን፣ የመወንጀል ተግባር ይታያል የምትለው ሕሊና፣ ይህንን ተጠቅሞም ወንጀለኛን ከተጠያቂነት የማስመለጥ እርምጃ ይታያል ትላለች።

“እርሱ እንደዚህ ዓይነት ተግባር የሚፈጽም አይደለም። የተከበረ እና ጥሩ ባህሪ ያለው ነው። እርሷ አሳሳተችው እንጂ” ሲባል እነደሚሰማ ታስረዳለች።

ይሁን እንጂ መድፈር “ከግብረገብ፣ ከጥሩ ሰብዕና እና የተከበረ ሰው መሆን ጋር የሚያያዝ አይደለም” ትላለች ሕሊና።

ወንዶች ልጆቻችን ስናሳድግ እንዳይሰርቁ እና እንዳይዋሹ እንደምንነግራቸው፣ ይህንንም ፈጽመው ከተገኙም ቅጣት እንዳለው እነደምናስተምራቸው ሴትን ያለፈቃዷ መንካትን፣ መጎንተልን ከሰው በታች ዝቅ አድርጎ መመለከት እና መግለጽን ከጥሩ ባህሪ የሚያስቀንስ አንደሆነ አናስተምርም ስትልም ትሟገታለች።

"ይህም ከማህበረሰባችን ጾተኛ አስተሳሰብ የሚመነጭ ነው።" አክላም “ማኅበረሰብ ውስጥ ጥሩ ሰው የሚባል የመድፈር ወንጀል ፈጸመ ቢባል እኔ አምናለሁኝ። ከዚህ በተጨማሪ ይህንን የተከበረ የምንለውን ሰው ከተጠያቂነት ለማስመለጥ እና ተጎጂን ለመክሰስ የምንጠቀምበት ሰበብ ነው።"

“የመልካምነት ጉዳይ ቢሆን ከዛሬ 4 ዓመት በፊት በኮቪድወረርሽኝ ምክንያት በቤት ውስጥ ስንቀመጥ አባቶች ልጆቻቸው ላይ የወሲብ ጥቃት ባላደረሱ ነበር።”

በሌላ በኩል ሰውነቷን የሚያሳይ አለባበስ ለብሳ ነው፣ ቤቱ ሄዳ ነው፣ ቆንጆ ስለሆነች እርሱ ማለፍ አይችልም፣ ከሚሉ አሰተሳሰቦች በተጨማሪ ሴቶች ግልጽ ያልሆነ መልዕክቶች ይሰጣሉ። ይግደረደራሉ። ስለሚሉ ሀሳቦችም ታብራራለች።

“የወሲብ ጉዳይ ላይ ሲመጣ አብረን ግንኙነት የምንፈጽመው ሰው ያለውን ነገር ብቻ እንጂ መቀበል ያለብን በይሆናል እንዲህ ስትል ይህን ማለቷ ነው ማለት የለብንም። በተጨማሪም አንዴ የተሰጠ ፈቃድ በማንኛውም ሰዓት ላይ፣ በግንኙነት ላይ ራሱ፣ ፈቃዱ ቢከለከል ሊከበር ይገባል" ትላለች።

ሴቷ አሳሳተችው የሚለውን ጉዳይ ስናጠቃልል የመድፈር ወንጀል በባል፣ በፍቅረኛ፣ በአባት እና በመሳሰሉት ቅርብ ሰዎች ከተፈጸመ አሳሳተችው የሚለው አመለካከት ራሱ የተሳሳተ ነው ማለት ነው።

የተሳሳተ አመለካከት 5- የመድፈርን ወንጀል የሚፈጽሙ ሰዎች ከሕግ ውጪ ርምጃ ሊወሰድባቸው ይገባል።

ከአራት ዓመት በፊት በኮቪድ ወረርሽኝ ወቅት፣ ሕጻናት እና ሴቶች በቤተሰብ አባላቶቻቸው ሲደፈሩ እንደነበር የሚያሳዩ መረጃዎች ሲወጡ ነበር።

በማሕበራዊ ሚዲያ ሳይቀር ይህንን ድርጊት የሚፈጽሙ ሰዎች ይሰቀሉ፣ የሚል ዘመቻ ተከፍቶ በስፋት ሲጋራ ነበር።

በሰሞኑ የሕጻን ሄቨን አወት መደፈር እና ግድያ ላይም የተሰጠው ውሳኔ በቂ አይደለም ከማለት በተጨማሪም ደፋሪው እንዲገደል ከሚሉ አስተያየቶች ጀምሮ ባየው ወይንም ባገኘው እገድለዋለሁ የሚሉ አስተያየቶች የሚሰጡ ግለሰቦች ነበሩ።

ሕሊና እንደምትለው እንዲህ ዓይነት ሀሳብ እና አስተያየት የሚሰጡ ሰዎች የሄቨን አይነት አሰቃቂ ታሪኮች ሲሰሙ መዓት ወረደ የሚመስላቸው፣ ከዚህ በፊት ተፈጥሮ የሚያቅ የማይመስላቸው ጉዳዩም ከሕግ ውጪ ቅጣት በመስጠት የሚቀረፍ ነው ብለው የሚያስቡ ናቸው ትላለች።

አሁን የተፈፀመው ድርጊት እንደሚያሳዝናት ብትናገርም፣ ጉዳዩን በዘመቻ ማየት ላይ እና እንደ ተናጠል የጥቃት ጉዳይን መውስድን ግን ትቃወማለች።

እርሷ እንደምትለው "ይህ ችግር ከየት መጣ? ከምንጩ እንዴት ማድረቅ አንችላለን?" የሚሉ ጉዳዮች ላይ መሰራት አለበት።

ምክንያቱም “ የመድፈር ወንጀል የአንድ ቀን ጉዳይ ሳይሆን ማኅበረሰቡን በውስጡ ይዞ የሚኖረው ነው። ይህንን ወንጀል በበቂ ሊቀጣ የሚችል ሕግ እንኳ ቢኖረን፣ ሕግ አስፈጻሚ እና ሕግ አስከባሪ አካላት የማኅበረሰቡ አባላት በመሆናቸው የአመለካከት ችግር አለ" ስትል ታስረዳለች።

ፖሊስን እንደ ምሳሌ በማንሳት፣ "መደፈር ላይ እንኳ ሳይደርስ ሴቶች በባላቸው ተደብድበው ወይንም ሌሎች ጾታዊ ጥቃት ደርሶባቸው ሪፖርት ሲያደርጉ አንደኛ የተለመደ ስለሆነ ጉዳዩን እንደ ወንጀል ያለመቀበል ክፍተት አለ። አቃቤ ሕግ እና ዳኛም ጾተኛ በሆነ መዋቅር ውስጥ ስለሚሰሩ ተመሳሳይ አመለካከቶችን ያንጸባርቃሉ።"

"በአጠቃላይ በየቀኑ ለሚፈጸም ለዚህ ዓይነት ወንጀል፣ የሕግ አፈጻጸሙን ማጠናከር፣ በፈቃድ መጠየቅ እና መስጠት የሚያምን ማኅበረስብ መፍጠር፣ ጾታን የሚያገሉ አስተሳሰቦችን እና መዋቅሮችን መታገል እንዲሁም የሕግ ተቋማት በአግባቡ ሴቶችን እንዲያገለግሉ" ማድረግ ላይ መሰራት አለበት ስትል ትመክራለች።

ሕሊና ሃሳቧን ስታጠቃልል ይህንን ወንጀል የሚፈጽሙ ሰዎችን እንግደል ማለት እኛው አካባቢ ያሉ ሰዎችን፣ የቤተሰቦቻችንን አባላት፣ ገድለን እንጨርሳቸው ማለት መሆኑን ገልጻ፣ ለጉዳዩ ስር ነቀል የሆነ ለውጥ በማምጣት ረገድ ጥቅም የሌለው እንደሆነ ታስረዳለች።