አሜሪካ፤ እስራኤል በሶርያ ጥቃት የፈጸመችበትን ግጭት ለማስቆም "የተለዩ እርምጃዎች" ላይ ስምምነት መደረሱን አስታወቀች

በደማስቆ ህንጻ ላይ በደረሰ ጥቃት የተፈጠረ ፍንዳታ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የእስራኤል ጦር ረቡዕ ዕለት በደማስቆ በሚገኘው የሶርያ መከላከያ ሚኒስቴር እና በደቡብ ሶርያ በሚገኙ የመንግስት ኃይሎች ላይ ጥቃት ሰንዝሯል።

በሶርያ በተለይም የዱርዝ እምነት ተከታዮች በሚገኙበት ሱዌዳ ግዛት ውስጥ እየተካሄደ ያለው ሃይማኖት ተኮር ግጭትም አራተኛ ቀኑን ይዟል።

የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ፤ የአገሪቱ ኃይሎች "ድሩዝ ወንድሞቻችንን ለማዳን እና የስርዓቱን ወንበዴዎች ለማስወገድ እየሰሩ ነው" ብለዋል።

የሶርያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በበኩሉ እስራኤል "የክህደት ጥቃት" ፈጽማለች ሲል ከስሷል።

ከእሁድ ዕለት አንስቶ በዱርዝ ሚሊሻዎች እና በቤዶኤን ጎሳዎች መካከል በተነሳው ግጭት ምክንያት ከ300 በላይ ሰዎች መገደላቸው ተዘግቧል።

የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሩቢዮ፤ በደቡብ ሱዌዳ ግዛት በተከሰተው ግጭት "እጅጉን መጨነቃቸውን" የገለጹ ቢሆንም ሁኔታው በጥቂት ሰዓታት ውስጥ ያበቃል የሚል እምነት እንዳላቸው ተናግረዋል።

ሩቢዮ፤ "ይህንን አሳሳቢ እና አስፈሪ ሁኔታ ዛሬ ማታ ለማቆም በሚያስችሉ የተለዩ እርምጃዎች ላይ ተስማምተናል" ሲሉ ረቡዕ ምሽት በኤክስ ገጻቸው ጽፈዋል።

የሶርያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በበኩሉ ሀገሪቱ "የአሁኑን ቀውስ በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት በአሜሪካ እና በአረብ ወገኖች የተደረጉ ጥረቶችን እንደምትቀበል" አስታውቋል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

እስራኤል እስካሁን ድረስ ይህንን የተኩስ አቁም ስምምነት በተመለከተ አስተያየት አልሰጠችም።

እንደ የሶርያ መንግስት የዜና ወኪል ሳና ዘገባ የሶርያ ወታደሮች ከሱዌዳ መውጣት ጀምረዋል።

ወታደሮች ከተማውን ለቅቀው መውጣት የጀመሩት በሶርያ መንግሥት እና በሱዌዳ የሃይማኖት መሪዎች መካከል በተደረገው ስምምነት መሠረት እንደሆነ ተገልጿል።

እዚህ ስምምነት ላይ የተደረሰውም "ሰራዊቱ ህገወጥ ቡድኖችን የማደን ስራውን ማጠናቀቁን" ተከትሎ ነው ተብሏል።

የእስራኤል ጦር የሶርያን የፀጥታ ኃይሎች እና የጦር መሳሪያዎቻቸውን ማጥቃት የጀመረው ሰኞ ዕለት የሠራዊቱ አባላት በሱዌዳ ከተማ ከተሰማሩ በኋላ ነበር።

ታህሳስ ላይ በሱኒ እስላማዊ የተመሩት ታጣቂዎች ፕሬዚዳንት በሽር አል አሳድን ከስልጣን ካወረዱ በኋላ እስራኤል ወታደሮቿን ስታሰማራ ይህ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው።

የሶርያ ጊዜያዊ ፕሬዝዳንት አህመድ አል ሻራ ሐሙስ ዕለት በቴሌቪዥን በተላለፈ ንግግራቸው "የድሩዝ ህዝባችንን የጣሱ እና በደል የፈጸሙትን" ተጠያቂ ለማድረግ ቃል ገብተዋል።

"እናንተን ጎትቶ የውጭ አካል እጅ ለማስገባት የሚደረገውን ማንኛውንም ሙከራ እንቃወማለን" ሲሉ የተደመጡት ጊዜያዊ ፕሬዝዳንቱ፤ ደህንነታችሁን ማስጠቅ "ቅድሚያ የምንሰጠው ጉዳይ ነው" ብለዋል።

"እኛ ጦርነትን ከሚፈሩ ሰዎች መካከል አይደለንም። ህይወታችንን ያሳለፍነው ፈተናዎች በመጋፈጥ እና ሕዝባችንን በመከላከል ነው። ነገር ግን ከሁከት እና ከጥፋት በፊት የሶርያውያንን ፍላጎት አስቀምጠናል" በማለት ተናግረዋል።

ፕሬዚዳንት አህመድ አል ሻራ እና መንግስታቸው፤ የሺዓ ኢስላም ተነጥሎ ልዩ ማንነት እንዲሁም እምነት ያዳበረውን ድሩዝ እና መሰል ህዳጣን ቡድኖችን ለመጠበቅ ቃል ቢገቡም፤ ቡድኖቹ ጥርጣሬ አላቸው።

ይህንን ፍርሃት ካጠናከሩ ምክንያቶች አንዱ ባለፉት ስምንት ወራት የተከሰቱት በርካታ የሃይማኖታዊ ግጭቶች ናቸው።

ግንቦት ላይ በደማስቆ እና በሱዌዳ ግዛት በድሩዝ፣ በጸጥታ ኃይሎች እና በተባበሩት እስላማዊ ታጣቂዎች መካከል በተከሰቱ ግጭቶች የበርካታ ሰዎች ህይወት እንዳለፈ ተዘግቧል።

ከዚህ ግጭት በኋላ መንግስት ከድሩዝ ሚሊሻዎች ጋር ባደረገው ስምምነት በመድረስ በሱዌዳ ግዛት ከታጣቂዎቹ መካከል የፀጥታ ኃይሎች ለመቅጠር ቃል ገብቷል።

በሶርያ የሚገኙት ድሩዞች በእስራኤል በተወረሩት የጎላን ከፍታዎች ከሚገኙ ነዋሪዎች ጋር ጥልቅ ትስስር እንዳላቸው የሚናገሩት ኔታያናሁ፤ መንግስታቸው በድሩዞች ላይ ጉዳት እንዳይደርስ ለመከላከል ቁርጠኛ መሆኑን ተናግረዋል።

የእስራኤል መከላከያ ሚኒስትር እስራኤል ካትዝ ረቡዕ ዕለት በኤክስ ገጻቸው ባሰፈሩት ጽሁፍ፤ "ለደማስቆ የተሰጡት ማስጠንቀቂያዎች" ጊዜያቸው መጠናቀቁን ገልጸዋል።

የእስራኤል ጦርም "በድሩዞቹ ላይ ጥቃት ያደረሱትን ኃይሎች ሙሉ በሙሉ ለቅቀው እስከሚወጡ ድረስ በሱዌዳ የሚያካሂደውን ዘመቻ አጠናክሮ እንደሚቀጥል" አስታውቀዋል።

ከጀርባቸው ታንክ የቆመ ታጣቂዎች መሳሪያቸውን ከፍ አድርገው ይዘው

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የመከላከያ ሚኒስትሩ ቀጥለውም፤ አንዲት የቴሌቪዥን አቅራቢ በቀጥታ ስርጭት ላይ እያለች በደረሰ ጥቃት ምክንያት ጠረጴዛ ስር ስትሸሸግ የሚያሳይ ቪድዮ በማያያዝ "የሚያምሙት ድብደባዎች ተጀምረዋል" በማለት ገጻቸው ላይ ለጥፈዋል።

በደማስቆ ጉብኝት ላይ የሚገኘው እና በለንደን የሚኖረው ሶርያዊ ፊልም ሰሪ ፋዲ አል ሀላቢ፤ የእስራኤል ተዋጊ አውሮፕላኖች ሲቃረቡ መስማቱን ተናግሯል።

"የሰዎች ገጽታ ፍርሃትን ያንጸባርቃል። ሁሉም ሰው በጎዳና ላይ መሮጥ ጀመረ። ማንም ወደ የት መሄድ እንዳለበት አያውቅም ነበር። ድንገት የአየር ድብደባው ተጀመረ፤ የመከላከያ ሚኒስቴርን ጨምሮ እጅጉን የተጨናነቁ አካባቢዎችን ዒላማ አደረጉ" ሲል ለቢቢሲ ተናግሯል።

የእስራኤል ጦር በዋና ከተማዋ በሚገኘው የፕሬዝዳንቱ ቤተ መንግሥት አካባቢ የሚገኝ "ወታደራዊ ዒላማን" ፣ ወደ ሱዌዳ እየተጓዙ የነበሩ ከባድ መሳሪያዎች የታጠቁ እና መሳሪያዎች የተጫኑ ተሽከርካሪዎችን እንዲሁም በደቡብ ሶርያ የሚገኙ የጦር መሳሪያ ማከማቻዎችን መምታቱን አስታውቋል።

የሶርያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በበኩሉ ጥቃቱ በደማስቆ እና በሱዌዳ የሚገኙ የመንግሥት ተቋማትን እና ሲቪል ተቋማትን ዒላማ መደረጋቸውን እና በዚህም "በርካታ ንጹሃን ዜጎች" መገደላቸውን ገልጿል።

"ውጥረትን ለማቀጣጠል፣ ትርምስ ለማስፋፋት እና በሶርያ ውስጥ ያለውን ደህንነትን እና መረጋጋትን ለማዳከም የሚተገበረው የእስራኤል ፖሊሲ አካል የሆነው ይህ ግልጽ ጥቃት፤ የተባበሩት መንግስታት ቻርተር እና ዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብት ጥሰት ነው" ሲል ከስሷል።

በዩናይትድ ኪንግደም የሚገኘው 'ሲሪያን ኦብዘርቫቶሪ ፎር ሂውማን ራይትስ' የተባለው የሰብአዊ መብት ታዛቢ ተቋም በሱዌዳ ከተማ ያለው የሰብአዊነት ሁኔታ በፍጥነት መባባሱን ሪፖርት አድርጓል።

በከተማዋ በበርካታ አካባቢዎች ግጭቶች እንደተከሰቱና ታንኮች በብሔራዊ ሆስፒታል ላይ ጥቃት እንደሰነዘሩ እና በታካሚዎች ላይ መደናገጥ መፈጠሩን ምንጮችን ጠቅሶ አስታውቋል።

በተጨማሪም ከፍተኛ የውሃ እና የህክምና አቅርቦት እጥረት እንዳለ ተነግሯል።

የሶርያ የጤና ሚኒስቴር በበኩሉ፤ "ህገወጥ ቡድኖች ለቅቀው ከወጡ በኋላ" የመንግሥት ኃይሎች ወደ ሆስፒታሉ ሲገቡ "በርካታ አስከሬኖችን" እንዳገኙ ገልጿል።

በሱዌዳ ግዛት ከእሁድ ጀምሮ ከ300 በላይ ሰዎች መገደላቸውን የሰብዓዊ መብቶች ታዛቢው ተቋም አስታውቋል።

ከሟቾቹ መካከል 69 የድሩዝ ተዋጊዎች እና 40 ሲቪሎች እንደሚገኙበት የጠቀሰው ተቋሙ፤ ከእነዚህ ውስጥ 27 የሚሆኑት በአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስቴር እና በመከላከያ ሚኒስቴር ኃይሎች መገደላቸውን ገልጿል።

ቢያንስ 165 የመንግሥት ኃይሎች አባላት እና 18 የቤዶኤ ጎሳ ተዋጊዎች በግጭቱ እንደተገደሉ፤ 10 የመንግስት ኃይሎች አባላት ደግሞ በእስራኤል ጥቃቶች መገደላቸውን አስታውቋል።

ቢቢሲ በሰብዓዊ መብቶች ታዛቢው ተቋም የተገለጹትን የጉዳት ቁጥሮች ማረጋገጥ አልቻለም።