እስራኤል ከሃይማኖት ግጭት በኋላ ወደ ድሩዝ ከተማ እየገቡ የነበሩ የሶሪያ ወታደሮችን በቦምብ ደበደበች

የፎቶው ባለመብት, Reuters
እስራኤል ለሁለት ቀናት የዘለቀውን አስከፊ የሃይማኖት ግጭት ተከትሎ የድሩዝ ህዝቦች በብዛት ወደሚኖሩባት ከተማ እየገቡ የነበሩ የሶሪያ መንግስት ወታደሮች ላይ በሱዌይዳ ዙሪያ የቦምብ ድብደባ መፈጸሟን ተናገረች።
በዩናይትድ ኪንግደም የተመሰረተው የሶሪያ የሰብአዊ መብት ተመልካች ቡድን በድሩዝ ሚሊሻዎች እና በቤዱዊን ጎሳዎች መካከል የተቀሰቀሰው ውጊያ እሁድ እለት ቢያንስ 200 ሰዎች መገደላቸውን ሪፖርት አድርጓል።
የእስራኤል ጠቅላይ ሚንስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ በሱዌይዳ አካባቢ በሚገኙ ኃይሎች እና የጦር መሳሪያዎች ላይ እንዲመታ ትዕዛዝ የሰጡበት ምክንያት መንግሥት "በድሩዞች ላይ ሊጠቀምባቸው ስላሰቡ ነው" ብለዋል።
ሶሪያ የእስራኤልን ተሳትፎ በማውገዝ ጥቃቱ የታጠቁ ሃይሎች እና ሲቪሎች ህይወት ማለፉን ተናግራለች።
በታህሳስ ወር በእስላማዊ መራሹ አማፂያን ፕሬዝዳንት በሽር አል አሳድን ከስልጣን ካስወገዱ በኋላ የሶሪያ መንግሥት ጦር ወደ ሱዋይዳ ሲሰማራ ይህ የመጀመሪያው ነው።
ድሩዞችን ጨምሮ ሃይማኖታቸው የሺአ ሙስሊም የሆኑ ብዙ አናሳ ማህበረሰቦች እነሱን ለመጠበቅ ቃል ቢገባም በጊዜያዊው የፕሬዚዳንት አህመድ አል ሻራ መንግስት ላይ ጥርጣሬ አላቸው።
እስካሁን ድረስ፣ የሱዌዳ ግዛት በአብዛኛው በድሩዜ ሚሊሻዎች ቁጥጥር ስር ነበር፣ ይህም የጸጥታ ኃይሉን ለመቀላቀል የሚደረጉ ጥሪዎችን በመቃወም ነበር።
ኔታንያሁ በሶሪያ ድሩዝ ላይ የሚደርሰውን ጉዳት ለመከላከል ቁርጠኛ ነኝ ያሉት፤ በእስራኤል ከሚኖሩት እና በእስራኤል ከተያዙት የጎላን ኮረብታዎች ጋር ባላቸው ጥልቅ ግንኙነት ነው።
የሶሪያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ማክሰኞ በሰጠው መግለጫ በደቡባዊ ሶሪያ ላይ ለደረሰው የቅርብ ጊዜ ጥቃት እና መዘዙ ሙሉ ሃላፊነቱ የእስራኤል መሆኑን አስታውቋል።
የትራምፕ አስተዳደር አሁን እስራኤል በሶሪያ ጦር ኃይሎች ላይ የምታደርገውን ጥቃት እንድታቆም መጠየቋን የዩናይትድ ስቴትስ ባለሥልጣንን ጠቅሶ የአገሪቱ የዜና አውታር አክሲዮስ ዘግቧል።
እስራኤል ማክሰኞ አመሻሽ ላይ ጥቃቱን እንደምታቆም ተናግራለች።
ትናንት ማክሰኞ ዕለት የሶሪያ የመከላከያ ሚኒስትር በሱዌይዳ የተኩስ አቁም ስምምነት መደረጉን ጠቁመው የጸጥታ ሃይሎች ወደዚያ እንዲሰማሩ ከአካባቢው ባለስልጣናት ጋር ስምምነት ላይ መደረሱን አስታውቀዋል። ሆኖም አንድ የድሩዝ መንፈሳዊ መሪ የአካባቢው ተዋጊዎች እንዲታገሉ አሳስቧቸዋል።
የሶሪያ ወታደሮችን ማሰማራቱን ተከትሎ የመንግስት ወታደሮች እና አጋሮቻቸውን የእንግዳ ማረፊያ የነበሩ 12 ሰዎችን ጨምሮ ጨምሮ በትንሹ 19 የድሩዝ ሲቪሎች ላይ ግድያ ፈጽመዋል ሲል የሶሪያ የሰብአዊ መብት ተመልካች ቡድን ወንጅሏል።
ቡድኑ በመቀጠል የመከላከያ ሚኒስቴር አባላት "የቤትን ንብረቶችን መስረቅ፣ በሮችና መስኮቶችን መስበር እና የተወሰኑትን ማቃጠል" ጨምሮ "በንጹሃን ቤቶች እና ንብረት ላይ ያነጣጠረ ስልታዊ የሆነ የጥሰት" ተግባራትን ፈጽመዋል ብሏል።
ወታደራዊ ዩኒፎርም የለበሱ ሰዎች ቤትና ሱቆች ሲያቃጥሉ እና ሲዘርፉ ታይቷል ሲል ሮይተርስ የዜና ወኪል ዘግቧል።
የሶሪያ ባለስልጣናት ለቀረበባቸው ክስ ወዲያውኑ ምላሽ አልሰጡም።
አንድ የሱዌይዳ ነዋሪ በአካባቢው ያለው ሁኔታ "አሰቃቂ" ነው ሲል ለቢቢሲ አረብኛ ተናግሯል፤ በሶሪያ ባለስልጣናት የሰዓት ዕላፊ ቢታወጅም ያለ ልዩነት የሚደረገው ተኩስ ሰዎች "ወደ ገጠር እንዲሸሹ" አድርጓል።












