በሶሪያ የኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ በደረሰ የአጥፍቶ መጥፋት ፍንዳታ 22 ሰዎች መገደላቸው ተገለጸ

የጻድቃን ምስል ያለበት የቤተ ክርስቲያን ግድግዳ ላይ ደም ተረጭቶ፤ መርማሪ ፖለሲ ግድግዳው ፊት ለፊት ቆሟል

የፎቶው ባለመብት, Reuters

በሶሪያ ዋና ከተማ ደማስቆ ውስጥ በሚገኝ የግሪክ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ላይ በተፈጸመ የአጥፍቶ ጠፊ የቦምብ ጥቃት ቢያንስ 22 ሰዎች ሲገደሉ 63 ሰዎች መቁሰላቸውን የሀገሪቱ ጤና ሚኒስቴር አስታወቀ።

የሀገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስቴር እንዳስታወቀው አንድ ግለሰብ እሁድ ምሽት በድዋይላ ሰፈር በሚገኘው በነቢዩ ኤልያስ የግሪክ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ውስጥ በመግባት ልብሱ ላይ የታጠቀውን ፈንጂ ከማፈንዳቱ በፊት ተኩስ ከፍቷል።

ጥቃት አድራሹ ከጂሃዳዊው ኢስላሚክ ስቴት (አይኤስ) ቡድን ጋር ግንኙነት እንዳለው ተገልጿል። ቡድኑ ግን ለተፈጸመው ጥቃት ኃላፊነቱን አልወሰደም።

በቤተክርስቲያኑ ውስጥ የተነሱ ፎቶግራፎች እና ቪዲዮዎች በከፍተኛ ሁኔታ የተጎዳ መሰዊያ፣ በተሰበረ ብርጭቆ የተሸፈኑ ወንበሮች እንዲሁም ግድግዳው ላይ የተረጨ ደም አሳይተዋል።

የዓይን እማኝ የሆነው ሎውረንስ ማማሪ ለኤኤፍፒ የዜና ወኪል እንደገለጸው፤ "አንድ ሰው ከውጭ የጦር መሳሪያ ይዞ [ወደ ቤተክርስቲያኗ]" በመግባት ተኩስ ጀምሯል። ቤተ ክርስቲያኗ ውስጥ የነበሩ ሰዎች "[ጥቃት አድራሹ] ራሱን ጭምር ከማፈንዳቱ በፊት ለማስቆም ሞክረዋል" ብሏል።

በአቅራቢያ በሚገኝ ሱቅ ውስጥ የነበረ ሌላ ሰው ደግሞ በመጀመሪያ የተኩስ ድምፅ፣ ቀጥሎም የመስታወት ስብርባሪዎች እንዲፈናጠሩ ያደረገ ፍንዳታ እንደሰማ ተናግሯል።

ዚያድ "በቤተክርስቲያኗ ውስጥ እሳት መኖሩን እና የእንጨት አግዳሚ ወንበሮች እስከ [ቤተክርስቲያኗ] ደጃፍ ድረስ ሲወረወሩ አየን" በማለት እማኝነቱን ሰጥቷል።

እስላማዊ መራሽ አማጺ ኃይሎች ባሻር አል-አሳድን ከሥልጣን ካወረዱ በኋላ እና 13 ዓመታትን ያስቆጠረውን አውዳሚ የእርስ በርስ ጦርነት ካስቆሙ በኋላ ደማስቆ ውስጥ እንዲህ ዓይነት ጥቃት ሲፈጸም ይህ የመጀመሪያው ነው።

የቤተ ክርስቲያኑ መግቢያ ላይ ሰዎች ተሰብስበው

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የአንጾኪያ የግሪክ ኦርቶዶክስ ፓትርያርክ ባወጣው መግለጫ፤ "ተንኮለኛው የክፋት እጅ ዛሬ ምሽት አጥቅቶ፣ ሕይወታችንን ቀጥፏል፣ በምሽት መለኮታዊ ቅዳሴ ወቅት ሰማዕታት ሆነው የሞቱትን የምንወዳቸውን ሰዎች ሕይወት ወስዷል" ብሏል።

የመጀመሪያ የተገኙ መረጃዎች እንደሚያመለክቱት የቦምብ ፍንዳታው የተከሰተው በቤተክርስቲያኑ መግቢያ ላይ ሲሆን በዚህም ምክንያት በሕንፃው ውስጥ እና በአቅራቢያው የነበሩ ሰዎች ተገድለዋል።

ፓትርያርኩ፤ የሶሪያን ጊዜያዊ ባለሥልጣናት "በቤተክርስቲያናት ቅድስና ላይ ጥሰት በመፈጸም ለተፈጸመው እና አሁንም እየተከሰተ ለቀጠለው ነገር ሙሉ ኃላፊነት እንዲወስዱ እና የሁሉም ዜጎችን ጥበቃ እንዲያረጋግጡ" ጥሪ አቅርበዋል።

የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስቴር ሚኒስትር አናስ ካታብ ድርጊቱን "የተወገዘ ወንጀል" ብለው የገለጹትን ሲሆን፣ ጉዳዩን የሚመለከቱ የልዩ ባለሙያዎች ቡድን ምርመራ መጀመሩን ተናግረዋል።

"እነዚህ የሽብር ድርጊቶች የሶሪያን መንግሥት የሲቪል ሰላም ለማምጣት የሚያደርገውን ጥረት አያስቆሙትም" ብለዋል።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሶሪያ ልዩ መልዕክተኛ ጌር ፔደርሰን፤ ጥቃቱን በማውገዝ ሶሪያውያን "ሽብርተኝነትን፣ አክራሪነትን፣ ትንኮሳን እና ማንኛውንም ማኅበረሰብን ዒላማ የማድረግ ተግባርን ለመቃወም አንድ እንዲሆኑ" አሳስበዋል።

የአሜሪካ ልዩ መልዕክተኛ ቶም ባራክ በበኩላቸው፤ "እነዚህ አስከፊ የፈሪነት ድርጊቶች ሶሪያውያን ለማሳካት እየጣሩ ባሉትን አዲስ የተቀናጀ የመቻቻል እና የአቃፊነት ሂደት ውስጥ ቦታ የላቸውም" ብለዋል።

ከፍንዳታ በኋላ ቤተ ክርስቲያኑ ውስጥ የሚገኙ ወንበሮች ተበታትነው እና ሌሎች መገልገገያዎች ወድቀው ይታያል

የፎቶው ባለመብት, EPA

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ጊዜያዊ ፕሬዝዳንቱ አልመህ አል ሳሃራ የሱኒ እስላማዊ ቡድን የሆነውን ሃያስ ታህሪር አልሻም የተባለ ቡድን የሚመራ ሲሆን፣ ይህ ቡድን ከዚህ ቀደም ከአል ቃኢዳ ጋር ግንኙነት የነበረው እንዲሁም በተባበሩት መንግሥታት፣ በአሜሪካ እና በዩናይትድ ኪንግደም አሸባሪ ቡድን ተብሎ የተፈረጀ ነው።

ፕሬዝዳንቱ በሃይማኖት እና በብሔር ህዳጣን የሆኑ ቡድኖችን ለመጠበቅ በተደጋጋሚ ቃል ገብቷል። ይሁን እንጂ ሶሪያ በቅርብ ወራት ውስጥ ሁለት የሰዎች ሕይወት የተቀጠፈባቸው ማንነት ተኮር ግጭቶችን አስተናግዳለች።

አይኤስ ሶሪያ ውስጥ ክርስቲያኖችን እና ሌሎች ህዳጣን የሃይማኖት ቡድኖችን በተደጋጋሚ ዒላማ አድርጓል።

ቡድኑ እ.አ.አ በ2016 በደማስቆ ደቡባዊ አካባቢ በሚገኘው የሺዓ ሙስሊም ሳይዳ ዘይነብ መቅደስ አቅራቢያ ተከታታይ ፍንዳታዎችን በመፈጸም ከ70 በላይ ሰዎችን ገድሏል።

አይኤስ በአንድ ወቅት ከምዕራብ ሶሪያ እስከ ምሥራቅ ኢራቅ ድረስ የተዘረጋን 88 ሺህ ስኩዌር ኪሎ ሜትር መሬት በመያዝ ስምንት ሚሊዮን ገደማ ሰዎችን በጭካኔ የተሞላበት አኳኋን ሲገዛ ነበር።

ምንም እንኳ ቡድኑ በ2019 ሶሪያ ውስጥ ወታደራዊ ሽንፈት ቢያጋጥመውም፤ አይኤስ እና ተባባሪዎቹ የፈጠሩት ስጋት ከፍተኛ ሆኖ እንደሚቀጥል የተባበሩት መንግሥታት አሳስቧል።

የካቲት ላይ የታተመ አንድ ሪፖርት፤ ቡድኑ የሶሪያን የሽግግር ወቅት እንደ ዕድል ተጠቅሞ ጥቃቶችን ሊጨመር እና ሀገሪቱን አዲስ የውጭ ተዋጊዎችን ምልመላ ማዕከል ሊያደርግ እንደሚችል አስጠንቅቋል።

አይኤስ በሶሪያ እና በአጎራባቿ ኢራቅ ከ1,500 እስከ 3,000 የሚደርሱ ታጣቂዎች እንዳሉት ይገመታል። የቡድኑን ቁልፍ አመራሮችን ጨምሮ አብዛኞቹ ታጣቂዎች በሶሪያ ግዛት ውስጥ ሰፍረዋል።

ወደ 300 የሚጠጉ ታጣቂዎች የውጭ ኦፕሬሽኖችን ለማቀድ ማዕከል ሆኖ ጥቅም ላይ በሚውለው በማዕከላዊው ባዲያ በረሃ ይገኛሉ።

በሰሜን ምሥራቅ ሶሪያ በተለያዩ እስር ቤቶች ውስጥ ከዘጠኝ ሺህ በላይ የአይኤስ ተዋጊዎች ታስረው ይገኛሉ። ሌሎች ከአይኤስ ጋር ግንኙነት ያላቸው ሌሎች 40,000 ሰዎችም በተለያዩ ካምፖች ውስጥ የሚገኙ ሲሆን፣ ከእነዚህ ውስጥ አብዛኞቹ ሴቶች እና ህጻናት ናቸው።