አቡነ ማትያስ "ችግሮች በሰላማዊ ውይይት" እንዲፈቱ እና "ሀገር እፎይታ እንድታገኝ" ጠየቁ

የፎቶው ባለመብት, EOTC Broadcasting Service
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ የሚያግባቡ ጉዳዮች ተፈልገው "ችግሮችን በሰላማዊ ውይይት" እንዲፈቱ በማድረግ "እናት ሀገር እፎይታ እንድታገኝ" እንዲደረግ ጠየቁ።
"በተለያየ ምክንያት" ከሲኖዶሱ የወጡ ወገኖች እንዲመለሱ ማድረግ የቤተ ክርስቲያኗ ሲኖዶስ ጉባኤ "ተቀዳሚ ተልዕኮ" እንደሆነም ፓትርያርኩ አስታውቀዋል።
የቤተ ክርስቲያኗ ፓትርያርክ ይህንን ጥሪ ያስተላለፉት ረቡዕ ግንቦት 6/2017 ዓ.ም. በተጀመረው ዓመታዊ የርክበ ካህናት የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ ላይ ባደረጉት ንግግር ነው።
ዛሬ የተጀመረው ይህ ጉባኤ፤ የቤተ ክርስቲያኗን "መንፈሳዊ፣ ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና አስተዳደራዊ" አፈጻጸሞች "በመገምገም ለቀጣዩ ጊዜ የሥራ አቅጣጫን" የሚያስቀምጥ እንደሆነ ፓትርያርኩ በመክፈቻ ንግግራቸው ገልጸዋል።
አቡነ ማትያስ፤ በአሁኑ ሰዓት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በሁሉም የዓለም ክፍሎች እንደምትገኝ መናገራቸውን በቤተ ክርስቲያኗ መገናኛ ብዙኃን ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ የተሠራጨው የፓትርያርኩ ንግግር አመልክቷል።
"የሲኖዶሱ መንበር በሚገኝባት ምድረ ኢትዮጵያ ከመቸውም የተሻለ ሥራ በመሥራት ለእግዚአብሔር መታዘዝ ሕዝቡንም ማገልገል ይገባናል" ሲሉ የሲኖዶሱ አባላትን አሳስበዋል። አቡነ ማትያስ በዚህ ንግግራቸው "በተለያየ ምክንያት" ከሲኖዶሱ የወጡ ወገኖች መኖራቸውን ጠቅሰዋል።
"ሁላችንም እንደምንገነዘበው በሲኖዶሳችን ያልታቀፉ ብዙ ወገኖች በሀገር ውስጥ አሉን፤ እነዚህ ወገኖች አንዳንዶቹ በተለያየ ምክንያት ከእኛ የወጡ ናቸው" ብለዋል።
ፓትርያርኩ ከሲኖዶሱ ወጥተዋል ያሏቸውን ወገኖች ለይተው ባይጠቅሱም በትግራይ የሚገኙ የኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን አባቶች የራሳቸውን ቤተ ክህነት እንዳቋቋሙ ይታወቃል።
የሃይማኖት አባቶቹ "የትግራይ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን መንበረ ሰላማ" የተባለውን ቤተ ክህነት የመሠረቱት የትግራይ ጦርነትን ተከትሎ በተፈጠረ ልዩነት ነው።
ጦርነቱን ያስቆመው የፕሪቶሪያ ስምምነት ከተፈረመ በኋላ የቤተ ክርስቲያኗ መሪ አቡነ ማስያስ ወደ ትግራይ ተጉዘው የነበረ ቢሆንም ከትግራይ አባቶች ጋር እርቅ ለማውረድ የተደረጉ ጥረቶች አልተሳኩም።
አቡነ ማትያስ በዛሬው ንግግራቸው ከሲኖዶሱ የተነጡ ወገኖችን መመለስ የጉባኤው "ተቀዳሚ ተልዕኮ" እንደሆነ ተናግረዋል። "የሄዱት ወደ ቤታቸው እንዲመለሱ፣ ሌሎችም ወደ መንጋው እንዲቀላቀሉ በርትቶ መሥራት የዚህ ጉባኤ ተቀዳሚ ተልዕኮ ነው፤ ምክንያቱም ጸጋን እና ሐዋርያነትን የተቀበልንበት ዋናው ምክንያት ይህንን ለማድረግ ነውና" ብለዋል።
ከዚህ ጋር በተያያዘም የቤተ ክርስቲያኗ ተደራሽነት "በሳሳበት አካባቢ ሁሉ የተለየ ትኩረት" ሰጥቶ መሥራት እና "ተጨባጭ ለውጥ ማምጣት" እንደሚገባም አሳስበዋል።

የፎቶው ባለመብት, EOTC Broadcasting Service
አቡነ ማስትያስ በመክፈቻ ንግግራቸው የሀገሪቱን ወቅታዊ ሁኔታ የሚመለከቱ ጉዳዮችንም አንስተዋል። የሃይማኖት አባቶች የሚያበረክቱት አገልግሎት "በመንፈሳዊ ብቻ ሳይሆን በኢኮኖሚው እና በማኅበራዊው" ዘርፍ ያሉ ጉዳዮችንም ጭምር እንደሚያካትት ገልጸዋል።
ሕዝቡ፤ "የተሻለ ማኅበራዊ አገልግሎት እንዲያገኝ፣ በኢኮኖሚውም ከድህነት የተላቀቀ እንዲሆን፤ እንደዚሁም ሰላሙ እና አንድነቱ የተጠበቀ እንዲሆን " መሥራት እንደሚገባም ተናግረዋል።
የሃይማኖት አባቶች ይህንን ኃላፊነት "በማስተማርም በተግባር በመሳተፍም የሕዝቡ መሪዎችና አርአያ" ሆነው መፈጸም እንዳለባቸው አንስተዋል።
አቡነ ማትያስ አክለውም፤ "በተለይም ከሰላም እጦት የተነሣ በእጅጉ እየተጎዳ ያለውን ሕዝባችን ሰላም እና ፍትሕ እንዲያገኝ በጸሎትም በትምህርትም፣ በምክርም ተግተን መሥራት አለብን" ብለዋል።
"የኢትዮጵያ ሕዝብ ከእንግልት የተላቀቀበት ጊዜ ብዙ እንዳልሆነ" ያስታወሱት አቡነ ማትያስ፤ የሀገሪቱ ሕዝብ "ለእንግልት እየተዳረገ ያለውም የሌሎች እጅ ባይለየውም በዋናነት በገዛ ልጆቹ" መሆኑን ገልጸዋል። "እናት በገዛ ልጆቿ ስትንገላታ ማየት እጅግ አሳዛኝ ነገር ነው" ሲሉም አክለዋል።
ይህንን ዓይነቱን "በደንብ ያልታሰበበት አካሄድ በብስለት እና በንስሐ ማስተካከል አሸናፊነትን እንጂ ተሸናፊነትን" እንደማያሳይ የጠቀሱት ፓትርያርኩ፤ "እንዲታሰብበት እንመክራለን" ብለዋል።
አቡነ ማትያስ፤ "ከዚህ አንጻር 'ኢትዮጵያን ወደ ተሻለ ልማት እና ዕድገት እናሻግራለን' ብላችሁ እየደከማችሁ ያላችሁ ወገኖቻችን እባካችሁ መለስ ብላችሁ እናታችሁ የተንገላታችበትን እዩና በቃ በሉ" ሲሉ ተማጽነዋል።
"ሁሉን የሚያግባባ ነገር ፈልጉና ችግሮችን በሰላማዊ ውይይት ፍቱ፤ በዚህ አማራጭ እናት ሀገር እፎይታ እንድታገኝ አድርጉ" ሲሉም የሰላም አማራጭ እንዲታይ ጥሪ አቅርበዋል።
ይህንን አማራጭ መከተልን "ለውድ እናት የሚደረግ ካሣ አድርጋችሁ ውሰዱት" ያሉት ፓትሪያርኩ፤ የቤተ ክርስቲያኗ "ወቅታዊ መልዕክት እና ጥሪ" ይህ እንደሆነ አስታውቀዋል።












