በኦሮሚያ ምሥራቅ ቦረና ውስጥ 18 ሰዎች በታጣቂዎች መታገታቸውን ባለሥልጣን ተናገሩ

ታጣቂ

በኦሮሚያ ክልል ምሥራቅ ቦረና ዞን፣ ጉሚ ኤልደሎ ወረዳ 13 የመንግሥት ሠራተኞችን ጨምሮ 18 ሰዎች በታጣቂዎች መታገታቸውን የወረዳው ባለሥልጣን ተናገሩ።

የጉሚ ኤልዳሎ ወረዳ ምክትል አስተዳዳሪ የሆኑት አቶ ዶዮ ዲባ፣ ታጣቂዎቹ ትናንት ሐሙስ 30/2017 ዓ.ም. ረፋድ ሦስት ሰዓት አካባቢ ከነገሌ ቦረና ወደ ጉሚ ኤልዳሎ በመኪና ሲጓዙ የነበሩ ሰላማዊ ሰዎችን በማስወረድ እንዳገቷቸው ለቢቢሲ ገልጸዋል።

እገታው የተፈጸመው ለሥራ ጉዳይ ከነገሌ ቦረና ወረዳ ወደ ወረዳዋ እየመጡ በነበሩ 18 ሰዎች ላይ መሆኑን እና አጋቾቹም መንግሥት ሸኔ የሚላቸው ታጣቂዎች መሆናቸውን ተናግረዋል።

ከታገቱት መካከል 13ቱ የመንግሥት ሠራተኞች ሲሆኑ፣ ቀሪዎቹ ደግሞ የአካባቢው ነዋሪዎች ናቸው። "ኃይል ከዚህ በፊትም የማሸበር ተግባር ሲፈፅም ቆይቷል። አሁን እገታን የገቢ ምንጭ በማድረግ ሰዎችን ወደ ጫካ እየወሰደ ከቤተሰቦቻቸው ገንዘብ በመጠየቅ ላይ ነው" ብለዋል አቶ ዶዮ።

የታገቱ ሁሉም የመንግሥት ሠራተኞች መሆናቸውን የጠቀሱት አስተዳዳሪው "አስራ አንዱ የወረዳችን፣ ሁለቱ ደግሞ ከመንገድ እና ሎጂስቲክስ የዞን ፅ/ቤት ለድጋፍ ሥራ እመጡ የነበሩ ናቸው። ከመካከላቸው አንድም የመንግሥት ሹመኛ የለም" በማለት መንግሥት በአጋቾቹ ላይ እርምጃ እንደሚወስድ ገልጸዋል።

በምዕራብ እና ደቡብ ኦሮሚያ ክፍሎች ውስጥ እንደሚንቀሳቀስ የሚነገረው መንግሥት ሸኔ የሚለው የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት በተደጋጋሚ ከሚፈጸሙ የእገታ ድርጊቶች ጋር ስሙ ይነሳል።

ምክትል አስተዳዳሪው አቶ ዶዮ ዲባ ለቢቢሲ እንደተናገሩትም አሁን የተፈጸመው እገታ የመጀመሪያ እንዳልሆነ እና በአካባቢው ታጣቂዎች በተደጋጋሚ የእገታ ወንጀሎች እንደሚጽሙ ተናግረዋል።

"ይህ ድርጊት የተለመደ ነው። ታጣቂዎቹ ከዚህ በፊትም የመንግሥት ሠራተኛን፣ ነዋሪዎችን አፍነው በመውሰድ የማስለቀቂያ ገንዘብ ከቤተሰቦቻቸው ይጠይቃሉ። እነዚህ የታገቱት ሰዎች ምንም ዓይነት የፖለቲካ ተሳትፎ የላቸውም። ለሕዝብ አገልግሎት እና ለግል ጉዳያቸው ሲጓዙ የነበሩ ናቸው።"

በድርጊቱ የተከሰሰው በመንግሥት በሽብርተኛ ቡድንነት የተፈረጀው የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ታጣቂ ቡድን እገታውን አስመልክቶ ያለው ነገር የለም። ከቢቢሲ ለቀረበለት ጥያቄም ምላሽ አልሰጠም።

ሆኖም ይህ ታጣቂ ቡድን በአካባቢው በስፋት እንደሚንቀሳቀስ እና በሚንቀሳቀስባቸው አካባቢዎች በተለያዩ ጊዜያት በተፈጸሙ እገታዎች ይከሰሳል።

ከዋና ከተማዋ አዲስ አበባ በቅርብ ርቀት ላይ በሚገኙ የኦሮሚያ ክልል ታጣቂ ቡድኑ ይንቀሳቀስባቸዋል በተባሉት አካባቢዎች ጭምር ተደጋጋሚ እገታዎች የሚያጋጥሙ ሲሆን፣ በዚህ መካከልም ጥቂት የማይባሉ ሰዎች ሕይወት መጥፋቱ ሲዘገብ ቆይቷል።

የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ታጣቂዎች በሚንቀሳቀሱባቸው ቦታዎች የሚፈጸሙ እገታዎችን በተመለከተ ከዚህ ቀደም በሰጠው ምላሽ እጁ እንደሌለበት ሲያስተባብል ቆይቷል።