የናይጄሪያ እርሻ ሚኒስቴር ለአገሪቱ የምግብ ዋስትና ሠራተኞቹ ጾም እና ጸሎት እንዲያደርጉ ጥሪ አቀረበ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ናይጄሪያ የምግብ ዋስትናን እንድታረጋግጥ ፈጣሪን ለመማጸን ፆም እና ጸሎት እንዲያደርጉ የአገሪቱ የእርሻ ሚኒስቴር ሠራተኞቹን መጠየቁን ተከትሎ ውዝግብ ተፈጥሯል።
በናይጄሪያ እርሻ ሚኒስቴር የሰው ኃይል አስተዳደር ክፍል ኃላፊ አማካኝነት ለመሥርያ ቤቱ ሠራተኞች በተሰራጫው ማስታወሻ የሚኒስትር መሥሪያ ቤቱ ባልደረቦች ለተከታታይ ሦስት ሰኞዎች በሚካሄደው የተማጽኖ ፆም እና ጸሎት ላይ እንዲሳተፉ ይጠይቃል።
ይህ ዜና መውጣቱን ተከትሎ አንዳንድ ናይጄሪያውያን መንግሥታቸው በአገሪቱ እያነረ ያለውን የምግብ ዋጋ እንዲቀንስ ለማድረግ ያለውን ቁርጠኝነት ጥያቄ ውስጥ በመክተት ተችተዋል።
የፆም ጸሎት ጥሪው መነጋገሪያ መሆኑን ተከትሎ የናይጄሪያ እርሻ ሚኒስቴር ቅዳሜ ዕለት ባወጣው መግለጫ ማስተባበያ ሰጥቷል።
ጥሪው በአገሪቱ ያለውን የምግብ ዋስትና ችግር ለመቅረፍ ጸሎት የመንግሥት ይፋዊ ፖሊሲ አለመሆኑን አመልክቶ፣ ነገር ግን ጸሎቱ የሠራተኞችን ደኅንነት ለማዳበር ነው ብሏል።
ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ በመግለጫው "ሠራተኞቻችን አካላዊ ጤናቸው እንዲጠበቅ በአሁኑ ጊዜ በመሥሪያ ቤታችን እንዳለው የኤሮቢክስ እንቅስቃሴ እና የስፖርት መሥሪያ ቦታ እንዳለን እንዲሁም ሠራተኞች መደበኛ የጤና ምርመራ እንሚያደርጉት ሁሉ" የጸሎት ጥሪው ተመሳሳይ ነው ብሏል።
አዲሱ የናይጄሪያ መንግሥት ከሁለት ዓመት በፊት ወደ ሥልጣን መምጣቱን ተከትሎ ባካሄዳቸው የፖሊሲ ለውጦች ምክንያት አገሪቱ አይታው በማታውቀው ሁኔታ አስከፊ የምጣኔ ሀብት ቀውስ ገጥሟታል።
ይህንንም ተከትሎ በአገሪቱ ቢያንስ 4.4 ሚሊዮን ሰዎች የሚመገቡት በቂ ምግብ እንዳሌላቸው የተባበሩት መንግሥታት ግምት ያመለክታል።
ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ የሕዝቡ መሠረታዊ ምግቦች ላይ በታየው ከፍተኛ ጭማሪ የተነሳ ባለፈው ዓመት በናይጄሪያ ውስይ አገር አቀፍ ተቃውሞ ተቀስቅሶ ነበር። ለምሳሌም አብዛኛው ሕዝብ የሚመገበው ያምስ የተባለው የምግብ ምርት በአራት እጥፍ ጭማሪ አሳይቷል።
ከጸሎት ጥሪው ጋር ተያይዞ ተቺዎች መንግሥት ኃላፊነቱን መውጣት አለመቻሉን እና ሁሉን ነገር በሕዝቡ ላይ በመጣል መለኮታዊ ጣልቃ ገብነትን እየጠበቀ ነው ሲሉ ወቅሰዋል።
ነገር ግን የናይጄሪያ ባለሥልጣናት በአገሪቱ ያለውን የምግብ ዋስትና ችግር ለመፍታት ለገበሬዎች ከአንድ ሺህ በላይ ትራክተሮችን እና ከሁለት ሚሊዮን ኩንታል በላይ ማደባሪያ ማደላቸውን ጨምሮ በርካታ እርምጃዎችን መውሰዳቸውን ተናግረዋል።
መንግሥት የሚጠበቅበትን ሳየሠራ ለጸሎት ጥሪ አቅርቧል ብለው የተቆጡ ናይጄሪያውያን የእርሻ ሚኒስቴሩ መመራት ያለበት በፓስተሮች ወይም በኢማሞች መሆን አለበት በማለት በባለሥልጣናቱ ላይ ተሳልቀዋል።















