በረመዳን የጾም ወቅት በአደባባይ ሲበሉ የተገኙ ናይጄርያውያን ታሰሩ

እስላማዊ ፖሊስ (ሂስባህ) እስሩ በረመዳን ሙሉ እንደሚቀጥል ተናግሯል

የፎቶው ባለመብት, AFP

የምስሉ መግለጫ, እስላማዊ ፖሊስ (ሂስባህ) እስሩ በረመዳን ሙሉ እንደሚቀጥል ተናግሯል

በሰሜናዊ ናይጄርያ ካኖ ግዛት በረመዳን ወቅት መጾም ሲገባቸው በአደባባይ ምግብ ሲሸጡ፣ ሲበሉ እና ሲጠጡ የተገኙ ሙስሊሞች በቁጥጥር ስር ዋሉ።

እንደ የእስላማዊ ፖሊስ (ሂስባህ) ምክትል ኮሚሽነር፣ ሙጃህዲ አሚኑዴን ገለጻ 20 ሰዎች መጾም እያለባቸው ባለመጾማቸው፣ አምስት ሰዎች ደግሞ ምግብ በመሸጣቸው በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ገልጸው፣ ይህ እርምጃ የረመዳን ጾም እስከሚጠናቀቅ ድረስ እንደሚቀጥል ተናግረዋል።

ኮሚሽነሩ " መገንዘብ የሚያስፈልገው ሙስሊም ያልሆኑ ሰዎች ላይ ይህንን ተግባራዊ እንደማናደርግ ነው" ብለዋል።

አሚኑዲን በረመዳን ወቅት ማንኛውም "ክብርን ዝቅ የሚያደርግ" ነገርን እንደማይታገሱ ተናግረዋል።

"በዚህ የተቀደሰ ወር አዋቂ ሙስሊሞች መጾም ሲገባቸው በአደባባይ ሲበሉ እና ሲጠጡ ማየት ልብ ይሰብራል። ይህንን ጉዳይ አንታገስም። ለዚያም ነው በቁጥጥር ስር ማዋል የጀመርነው" ብለዋል።

አክለውም በቁጥጥር ስር የዋሉት 25 ግለሰቦች በሙሉ በሸሪዓ ፍርድ ቤት ቀርበው እንደ ጥፋታቸው መሰረት ቅጣት ይጣልባቸዋል ብለዋል።

የፖሊስ ባለስልጣናት አንዳንድ ጊዜ ሰዎች በአደባባይ ሲበሉ ሲታዩ ጥቆማ እንደሚደርሳቸው ተናግረዋል።

"ሰዎች በአደባባይ ሲበሉ የተመለከቱ እና የተቆጡ ሰዎች ይደውሉልናል። እኛም ወደ ቦታው በፍጥነት በመሄድ በቁጥጥር ስር እናውላቸዋለን።"

አክለውም "ጸጉራቸውን ተገቢ ባልሆነ ሁኔታ የተቆረጡ"፣ ከጉልበታቸው በላይ የሆነ ቁምጣ ያደረጉ፣ ወንድ እና ሴት አቀላልለው የሚያሳፍሩ ባለ ሦስት ጎማ መኪና አሽከርካሪዎችም በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ተናግረዋል።

ባለፈው ዓመት ባለመጾማቸው ምክንያት በቁጥጥር ስር ውለው የነበሩ ሰዎች ለመጾም ቃል ከገቡ፣ አልያም ቤተሰቦቻቸው ተጠርተው መጾማቸውን እንዲከታተሉ ከተነገራቸው በኋላ ተለቅቀዋል።

በዚህ ዓመት በቁጥጥር ስር የዋሉት ግን ይህ እድል ያልገጠማቸው ሲሆን ፍርድ ቤት ቀርበው ጉዳያቸው እንዲታይ ተወስኗል።

ከሁለት አስርታት በፊት ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው የእስልምና እምነት ተከታዮቸ በሚገኙባቸው 12 የሰሜን ናይጄርያ ግዛቶች ከመደበኛው ሕግ ጎን ለጎን የሸሪአ ሕግ ስራ ላይ እንዲውል ተደርጓል።

በሙስሊሞች ካላንደር ዘጠነኛ የሆነው የረመዳን ወር በእስልምና ዘንድ ልዩ ስፍራ አለው።

የእስልምና እምነት ተከታዮች የቅዱስ ቁርዓን አምስት አናቅጽት ለነብዩ መሐመድ የተገለጡት በዚህ ወር እንደሆነ ያምናሉ።

መጾም ከአምስቱ የእስልምና አዕማዳት መካከል አንዱ ነው።