ከአንድ ሚሊዮን በላይ በምግብ እጥረት የተጎዱ ኢትዮጵያውያን እና ናይጄርያውያን ሕጻናት አደጋ ላይ ናቸው - ዩኒሴፍ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የተባበሩት መንግሥታት የሕጻናት ኤጀንሲ (ዩኒሴፍ) በኢትዮጵያ እና ናይጄርያ እድሜያቸው ከአምስት ዓመት በታች የሆነ እና ለከፋ የምግብ እጥረት የተጋለጡ 1.3 ሚሊዮን ሕጻናት በዚህ ዓመት ወሳኝ የሆነውን ሕይወት አድን ድጋፍ የማጣት አደጋ ተጋርጦባቸዋል አለ።
ኤጀንሲው በሚቀጥሉት ሁለት ወራት ውስጥ በሁለቱም አገራት ሕጻናት ላይ የሚደርሰውን የተመጣጠነ ምግብ እጥረት ለማከም የሚያቀርበውን የነፍስ አድን ምግብ እርዳታ በማጣት ምክንያት እንደሚጨርስ ገልጿል።
ኤጀንሲው የገጠመው የሕይወት አድን ምግብ ድጋፍ በአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ የውጭ ዕርዳታን በማቋረጣቸው ምክንያት ተባብሷል።
የዩኒሴፍ ምክትል ሥራ አስፈፃሚ ኪቲ ቫን ደር ሃይጅደን አርብ ዕለት በጄኔቫ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ እንዳስታወቁት ባለፉት ሃያ አምስት ዓመታት የተመዘገቡት ውጤቶች በከፍተኛ የገንዘብ ድጋፍ ማሽቆልቆልን ምክንያት ወደ ኋላ ሊመለሱ እና ሊቀለበሱ ይችላሉ ብለዋል።
"አዲስ የገንዘብ ምንጭ እስካልተገኘ ድረስ ዩኒሴፍ በግንቦት ወር በምግብ እጥረት የሚሰቃዩ ሕጻናትን ለማከም የሚያግዘውን ሕይወት አድን ምግብ (RUTF) እንደሚያልቅ እንገምታለን። ይህም በኢትዮጵያ በየወሩ ሕክምና የሚያስፈልጋቸው 74,500 የሚገመቱ ሕጻናት ላይ አስከፊ መዘዝ ያስከትላል።"
"በናይጄሪያ በወር ወደ 80,000 የሚጠጉ ሕጻናት ሕክምና የሚያስፈልጋቸው ሲሆን፣ የሕይወት አድን ምግቦቹ (RUTF) አቅርቦቶች በዚህ ወር እና በግንቦት መጨረሻ መካከል ባለው ጊዜ ውስጥ ሊያልቅብን ይችላል" ሲሉ ቫን ደር ሃይጅደን ተናግረዋል።
በጥር ወር ፕሬዝዳንት ትራምፕ የመንግሥትን ወጪ ለመቀነስ በሚል የዩኤስኤይድ ሥራዎችን ማቋረጣቸው ይታወሳል።
ይህ የፕሬዝዳንቱ እርምጃ በዓለም ጤና ድርጅት እና በሌሎች ዓለም አቀፍ የልማት አካላት የተወገዘ ሲሆን ብዙ በውጪ እርዳታ ላይ ጥገኛ የሆኑ ታዳጊ አገራትን፣ በተለይም በአፍሪካ፣ስጋት ውስጥ ጥሏቸዋል።
ዩኤስኤይድ በአፍሪካ ከሦስት አስር ዓመታት በላይ ወባን፣ ኤችአይቪ/ኤድስን፣ ሳንባ ነቀርሳን እና ሌሎች በሽታዎችን ለመዋጋት በሚደረጉ ጥረቶች ውስጥ ትልቁ ለጋሽ ድርጅት ነው።
የድጋፍ ቅነሳው በኢትዮጵያ ለነፍሰ ጡር እናቶች እና ሕጻናት የተመጣጠነ ምግብ እና የወባ ሕክምና አገልግሎት የሚሰጡ የጤና ፕሮግራሞች ላይ ከፍተኛ አሉታዊ ተጽዕኖ ማሳደሩን የተናገሩት የዩኒሴፍ ምክትል ኃላፊ፣ በዚህ ምክንያት ብቻ በአፋር ክልል በፈንድ ቅነሳው ምክንያት ሃያ ሦስት ተንቀሳቃሽ የጤና ክሊኒኮች ከአገልግሎት ውጪ ሲሆኑ ሰባት ብቻ በአሁኑ ወቅት አገልግሎት እየሰጡ መሆኑን ተናግረዋል።
በናይጄሪያ ሰሜናዊ ምሥራቅ በሽብርተኞች እና በታጣቂዎች ምክንያት ባለው የፀጥታ መደፍረስ የተነሳ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን መገደላቸውን እና ሚሊዮኖችን መፈናቀላቸውን ተከትሎ ሕጻናት ለከፍተኛ የምግብ እጥረት ተጋልጠዋል።
ትራምፕ ወደ ሥልጣን በተመለሱ በሰዓታት ውስጥ ነበር ለውጭ አገራት የሚሰጡ ድጋፎች ከእሳቸው ፖሊሲ ጋር ምን ያህል የተጣጣሙ መሆናቸው እስኪረጋገጥ ድረስ እንዲቋረጡ የሚያዝ ትዕዛዝ ማስተላላፋቸው ይታወሳል።
በቀዳሚነትም በዓለም ዙሪያ በሚገኙ ደሃ አገራትን ጨምሮ በ120 አገራት ውስጥ የጤና እና የአስቸኳይ ጊዜ እርዳታን የሚያቀርበው ዩኤስኤይድ ሥራውን ለሦስት ወራት እንዲያቆም ታዟል።
በዓለም ላይ ከፍተኛውን የሰብአዊ እርዳታ በመስጠት አሜሪካ ትልቋ እና ዋነኛዋ ስትሆን፣ የዩኤስኤይድ ዓመታዊ በጀት 40 ቢሊዮን ዶላር ነው።
ይህ የአሜሪካ መንግሥት ውሳኔ በዓለም ዙሪያ በተለይ በኤችአይቪ/ኤድስ እና በሰብአዊ እርዳታ አቅርቦት ላይ ከፍተኛ ጉድለትን የሚያስከትል መሆኑን የመንግሥታቱ ድርጅት እና ሌሎችም የእርዳታ ተቋማት እየገለጹ ነው።












