የዩኤስኤይድ ሠራተኞች የግዳጅ እረፍት እንዲወጡ የሚያዘው የትራምፕ ውሳኔ ታገደ

የዩኤስኤይድ መዘጋትን የሚቃወሙ ሰልፈኞች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, የዩኤስኤይድ መዘጋትን የሚቃወሙ ሰልፈኞች

የአሜሪካ የልማት ተራድኦ ድርጅት ዩኤስኤይድ 2,200 ሠራተኞችን ተከፍሏቸው እረፍት እንዲወጡ የሚያዘው የፕሬዝዳንት ትራምፕ ውሳኔ ተግባራዊ ከመሆኑ ከሰዓታት በፊት በአንድ ዳኛ ጊዜያዊ ዕግድ ተጣለበት።

ዳኛው ካርል ኒኮልስ በሺህ የሚቆጠሩ ሠራተኞችን ከአርብ እኩለ ሌሊት ጀምሮ የግዳጅ እረፍት እንዲወጡ የሚያደርገውን ዕቅድ በመቃወም በሠራተኞች ማኅበራት በኩል ለቀረበው ክስ በሰጡት ምላሽ "በጣም የተገደበ" ጊዜያዊ የዕግድ ትዕዛዝ እንደሚያወጡ አሳውቀዋል።

የአሜሪካ መንግሥት ዓለም አቀፍ ልማት ተቋም የሆነው ዩኤስኤይዲ ወደ 10,000 የሚጠጉ ሠራተኞች ያሉት ሲሆን፣ ከእነዚህ ውስጥ ሁለት ሦስተኛው ከአሜሪካ ውጪ የሚሰሩ ናቸው። የተቀሩት ሠራተኞች ቀጣይ የሥራቸውን ዕጣ ፈንታ በተመለከተ ምንም ግልጽ ነገር የለም።

በትራምፕ ዕቅድ መሰረት 611 የሚሆኑ ሠራተኞች በኤጀንሲው ውስጥ እየሠሩ እንዲቆዩ ተደርገው ነበር። የዳኛው ውሳኔ የተገለጸው ባለሥልጣናት በዋሽንግተን ዲሲ በሚገኘው የድርጅቱ ዋና መሥሪያ ቤት የዩኤስኤይዲ ዓርማዎችን በማንሳት እና በመሸፈን ላይ ሳሉ ነው።

የፕሬዝዳንቱ ሪፐብሊካን ፓርቲ በአሜሪካ መንግሥት ተቋማት ላይ ለውጥ ለማድረግ ዘመቻ እያካሄዱ ሲሆን፣ ይህንን ሥራ የሚያከናውነውን የመንግሥት አካል የሚመራው ቢሊየነሩ ኢላን መስክ በከፍተኛ መጠን የበጀት ቅነሳ ለማድረግ እርምጃ እየወሰደ ነው።

በመጀመሪያ የሥልጣን ዘመን በትራምፕ የተሰየሙት እገዳውን ያስተላለፉት ዳኛ ኒኮላስ እንዳሉት፣ የውሳኔያቸው የጽሑፍ ትዕዛዝ ዘግየት ብሎ በዝርዝር እንደሚወጣ አሳውቀዋል።

የዩኤስኤይድ ዋና ጽህፈት ቤት በር ላይ ያለው ዓርማው ተሸፍኖ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, የዩኤስኤይድ ዋና ጽህፈት ቤት በር ላይ ያለው ዓርማው ተሸፍኖ

የአሜሪካ መንግሥትን በመክሰስ ዕግዱን ያስወሰኑት ማኅበራት ውሳኔው ምን ያህሉን የድርጅቱን ሠራተኞች የሚያካትት መሆኑን ለማወቅ ዝርዝሩን በጽሑፍ እየጠበቁ መሆናቸውን ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ነገር ግን ለአሁኑ ከሁለት ሺህ በላይ የሚሆኑ የዩኤስኤይድ ቀጥተኛ ተቀጣሪ ሠራተኞች በሥራ ላይ ይቆያሉ በማለት ክሱን ካቀረቡት ጠበቆች አንዱ ሎሪን ባትማን ተናግረዋል።

እስካሁን 500 የሚሆኑ የድርጅቱ ሠራተኞች በትራምፕ አስተዳደር ውሳኔ መሠረት በግዳጅ እረፍት እንዲወጡ ተደርገዋል።

ክሱን ያቀረቡት የሕግ ባለሙያዎች ዩኤስኤይድን ለማፈረስ ፕሬዝዳንት ትራምፕ እየወሰዱት ያለው እርምጃ በአገሪቱ ምክር ቤት ይሁንታን ያላገኘ በመሆኑ የአሜሪካንን ሕገ መንግሥት የሚጥስ ነው በማለት ተከራክረዋል።

በፍርድ ቤቱ የትራምፕን አስተዳደር በመወከል የቀረቡት የፍትሕ ሚኒስቴር ባለሥልጣን የሆኑት ብሬት ሹሜት ለዳኛው ፕሬዝዳንት ትራምፕ እዚህ ውሳኔ ላይ የደረሱት "በዩኤስኤይድ ውስጥ ሙስና እና ማጭበርበር በመኖሩ ነው" ሲሉ ተናግረዋል።

ትራምፕ ወደ ሥልጣን በተመለሱ በሰዓታት ውስጥ ነበር ለውጭ አገራት የሚሰጡ ድጋፎች ከእሳቸው ፖሊሲ ጋር ምን ያህል የተጣጣሙ መሆናቸው እስኪረጋገጥ ድረስ እንዲቋረጡ የሚያዝ ትዕዛዝ ማስተላላፋቸው ይታወሳል።

በቀዳሚነትም በዓለም ዙሪያ በሚገኙ ደሃ አገራትን ጨምሮ በ120 አገራት ውስጥ የጤና እና የአስቸኳይ ጊዜ እርዳታን የሚያቀርበው ዩኤስኤይድ ሥራውን ለሦስት ወራት እንዲያቆም ታዟል።

በዓለም ላይ ከፍተኛውን የሰብአዊ እርዳታ በመስጠት አሜሪካ ትልቋ እና ዋነኛዋ ስትሆን፣ የዩኤስኤይድ ዓመታዊ በጀት 40 ቢሊዮን ዶላር ነው።

ይህ የአሜሪካ መንግሥት ውሳኔ በዓለም ዙሪያ በተለይ በኤችአይቪ/ኤድስ እና በሰብአዊ እርዳታ አቅርቦት ላይ ከፍተኛ ጉድለትን የሚያስከትል መሆኑን የመንግሥታቱ ድርጅት እና ሌሎችም የእርዳታ ተቋማት እየገለጹ ነው።