ለተከታታይ 90 ሰዓታት ምግብ በማብሰል ክብረ ወሰን ለመስበር የሞከረችው ናይጄሪያዊት ሼፍ

ናይጄሪያዊቷ ምግብ አብሳይ (ሼፍ) የዓለም ክብረ ወሰንን ለመስበር ባደረገችው ሙከራ ከ90 ሰዓታት በላይ ምግብ በማብሰል የመጀመሪያዋ መሆኗ እስኪረጋገጥ እየጠበቀች ነው።
ሄልዳ ባቺ ከሐሙስ ከሰዓት በኋላ አንስታ ምግብ ማብሰል ከጀመረች በኋላ ከ100 በላይ የተለያዩ ምግቦችን አብስላለች።
ሌጎስ ውስጥ በሚገኝ ክፍት ስፍራ ሄልዳ ምግብ ስታበስል በርካታ ሰዎች በዙሪያዋ ተሰብስበው የተከታተሏት ሲሆን፣ ፖለቲከኞች እና ታዋቂ ሰዎች አበረታተዋታል።
ቀደም ብሎ የነበረው ምግብ የማብሰል ክብረ ወሰን የተያዘው ከአራት ዓመት በፊት በሕንዳዊ ምግብ አብሳይ ሲሆን፣ ሰዓቱም 87 ሰዓት ከ45 ደቂቃዎች የፈጀ ነበር።
የዓለም የክብረ ወሰን መዝገብ ‘ጊነስ ዎርልድ ሪከርድስ’ ሄልዳ ምግብ በማብሰል የወሰደችውን ሰዓት በዓለም ክብረ ወሰንነት ለመመዝገብ እያጣራ መሆኑን ገልጿል።
ሄልዳ ሌጎስ ውስጥ ምግብ ባበሰለችበት ስፍራ የክብረ ወሰን መዝጋቢው ድርጅት ተወካይ ባይኖርም፣ ካሜራዎች ሂደቱን በሙሉ ቀርጸውታል።
የ27 ዓመቷ ሄልዳ ባቺ በመጀመሪያ ከሐሙስ ከሰዓት ጀምራ አስከ ሰኞ ከሰዓት ለ96 ሰዓታት ምግብ በማብሰል ነበር ክብረ ወሰኑን ለማሻሻል ያቀደችው።
ነገር ግን በዙሪያዋ ተሰብስበው ሲያበረታቷት የነበሩት ደጋፊዎቿ ምግብ የማብሰሉን ክብረ ወሰን በ100 ሰዓት እንድታሻሽለው ገፋፍተዋታል ተብሏል።
በዚህ ሂደትም በሺዎች የሚቆጠሩ ምግብ የያዙ ሳህኖችን አዘጋጅታ ሥራዋን ለመመልከት ለታደሙ ሰዎች አቅርባለች።
ምግብ በምታዘጋጅበት ወቅት አንድ ረዳት የነበራት ሲሆን፣ በየአንድ ሰዓቱ ለአምስት ደቂቃ ወይም በበርካታ ሰዓታት ውስጥ የዚያን ተመጣጣኝ ደቂቃዎች እረፍት ስታደርግ ነበር።
“ወጣቶች ትክክለኛውን ቦታ እና ድጋፍ ካገኙ ምን ያህል ጠንካሮች መሆናቸውን ለማሳየት ይህ ሙከራዬ ማሳያ ነው” በማለት ሄልዳ ምግብ ማብሰሏን ከመጀመሯ በፊት ለቢቢሲ ተናግራ ነበር።
በሂደቱ ውስጥ አካላዊ ድካም ይታይባት የነበረ ሲሆን፣ እረፍት በምታደርግበት ማበረታቻ እና የህክምና ባለሙያም ክትትል ይደርግላት ነበር።
ክብረ ወሰኑን ለማሻሻል ባደረገችው ሙከራ ወቅት በመላዋ ናይጄሪያ ትኩረት አግኝታ የነበረ ሲሆን፣ ፖለቲከኞች እና ታዋቂ ሰዎችም ሲያበረታቷት ነበር።
የሌጎስ ግዛት አስተዳዳሪ ባባጂዴ ሳንዎ-ኢሉ እሁድ እለት በስፍራው ተገኝተው ነበር። ከአገሪቱ ምክትል ፕሬዝዳንትም ስልክ ተደውለውላታል።
ሄልዳ ባቺ እንዲህ አይነቱ ፉክክር ውስጥ ስትገባ ይህ የመጀመሪያዋ አይደለም፣ ከሁለት ዓመት በፊት እዚያው ናይጄሪያ ውስጥ ጋናውያን ጭምር ተሳትፈውበት በተደረገ የምግብ ማብሰል ውድድር ላይ አሸናፊ ለመሆን ችላለች።
ለምግብ ማብሰል ያላት ፍቅር የተጸነሰው በእናቷ የምግብ ማብሰል ጥበብ እና ቤታቸው ውስጥ በሚያዘጋጇቸው ምግብ ቅመሞች የተነሳ መሆኑን ተናግራለች።












