የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ዜሌንስኪ የጦርነት ግንባር ከተሞችን ጎበኙ

የፎቶው ባለመብት, UKRAINIAN PRESIDENTIAL PRESS SERVICE
ፕሬዝዳንት ቮሎድሚር ዜሌንስኪ የዩክሬን ጦር ዝግ ብሎም ቢሆን ወደፊት እየገሰገሰ ባለባቸው እና በአውዳሚ ጦርነት ውስጥ በሚገኙት ደቡባዊ ግንባር ከተሞችን ጎብኝተዋል።
ፕሬዝዳንቱ በከፍተኛ ጦርነት ውስጥ የምትገኘውን ማይኮሊቫ ከተማ ተገኝተው የወደሙ ህንጻዎችን ከመጎብኝት በተጨማሪ ወታደሮችን፣ የጦር መኮንኖችን እና የጤና ባለሙያዎችን አነጋግረዋል።
ዜሌንስኪ ጦርነቱ ከተቀሰቀሰ ጀምሮ የሩሲያ ጦር ከፍተኛ ድብደባ እየፈጸመባት ያለውን ኦዴሳ የተሰኘችውንም ከተማ ጎብኝተዋል።
ሁለቱ ከተሞች የሩሲያ ጦር የጥቁር ባህርን ለመያዝ በሚያደርገው ጥረት ዋናኛ ኢላማ ናቸው።
ሩሲያ ምስራቃዊ ዶምባስ ላይ ትኩረት ካደረገች በኋላ ጧሯን ከዋና ከተማዋ ኪዮቭ አርቃለች። ይህንንም ተከትሎ ፕሬዝዳንት ዜሌንስኪ የሀገራት እና ተቋማት መሪዎች በቋሚነት በኪዬቭ ማግኘት ጀምረዋል።
ሆኖም ፕሬዝዳንቱ ከቅርብ ሳምንታት ወዲህ በምስራቃዊ ዩክሬን የምትገኘውን ካሪኩቨ የተባለችውን ከተማ ጨምሮ የጦር ግንባር የሆኑ አከባቢዎች ጉብኝት ማድረግ ጀምረዋል።
ዜሌንስኪ ኦዴሳ ከተማ ላይ ለወታደሮች ንግግር ሲያደርጉ “በጣም ጠቃሚው ነገር እናንተ በህይወት አላችሁ። እናንተ እስካላችሁ ድረስ ሀገራችንን የሚጠብቃት ጠንካራ ግንብ ይኖራል” ያሉ ሲሆን “እያደረጋችሁ ላላችሁት ታላቅ ተግባር እና ወደር የሌለው አገልግሎት ላመሰግናችሁ እወዳለሁ” ሲሉ አክለዋል።
በማይኮሊቭ ከተማ ደግሞ ፕሬዝዳንቱ ለወታደሮች ሜዳሊያ የበረከቱ ሲሆን “ ያለን ብቸኛ ነገር እሱን ስለሆነ ዩክሬንን ጠብቁ። ማድረግ የምትችሉት እሱን ብቻ ስለሆነ ራሳችሁን ጠብቁ” በማለት አሳስበዋል።
ከተማዋ ለረጅም ጊዜ የሩሲያ ጦር ኢላማ የነበረች እና ከባድ ሮኬትና መድፍ ሲወርድባት ነበር።
ከተማዋ በምስራቅ ደቡባዊ ክፍል ከምትገኘው ኬርሶን ከተማ በ100 ኪሎ ሜትር ርቀት ውስጥ የምትገኝ ናት። ኬርሶን ጦርነቱ ከተጀመረ ጀምሮ በሩሲያ ጦር ቁጥጥር ስር የነበረች ሲሆን አሁን ግን የዩክሬን ጦር በዝግታ እየገሰገሰባት ይገናኛል።
ባለፈው ሳምንት አንድ የዩክሬን ባለስልጣን ሩሲያ የዩክሬንን ጦር ግስጋሴ ለመግታት ድልድዮችን እያደባየች ነው ሲሉ ተደምጠዋል።












