ለከብቶቻችን የምንሰጠውን ያደረ ዳቦ ለራሳችንም አጥተናል፡ አፍጋኒስታናውያን

ያደረ ዳቦ ገበያ የደራባት ካቡል
የምስሉ መግለጫ, ያደረ ዳቦ ገበያ የደራባት ካቡል

አፍጋኒስታናውያን ናን የሚሉት ዳቦ አላቸው።

ናን አምባሻ የሚመስል በእስያ ተወዳጅ ምግብ ነው።

አፍጋኒስታናውያን ‘የዕለት እንጀራዬን አትንፈገኝ’ የሚሉት ይህን ዳቦ እያሰቡ ነው።

መሃል ካቡል ሰማያዊ መስጂድ ይገኛል።

በአቅራቢያው አነስተኛ ጉልት አለች። በዚህች ገበያ ትልልቅ ብርቱካናማ ከረጢቶች በደረቁ የናን ዳቦዎች ተሞልተዋል።

ከዚህ ቀደም በየቦታው የሚተራርፉ ዳቦዎች ለእንስሳት ምግብነት ይውሉ ነበር። አሁን ግን ነገሮች ተቀይረዋል። ብዙ አፍጋኒስታናውያን ረሃባቸውን ለማስታገስ ወደ እነዚህ ዳቦዎች ፊታቸውን እያዞሩ ነው።

ሻፊ መሐመድ የካቡል ፑል ኬሽቲ ገበያ ነጋዴ ነው። ላለፉት 30 ዓመታት ትኩስ ያልሆነ ዳቦ ይሸጣል።

ስለገበያው ሁኔታ ሲገልጽም "በፊት በፊት በቀን አምስት ያህል ሰዎች ብቻ ነበሩ የሚገዙን።አሁን ከ20 ሰው በላይ ይገዛናል" ይላል።

ያደረ ዳቦ ገበያው ደርቷል። ሁሉም ሰው በአገሪቱ ምጣኔ ሐብት መቆርቆዝ ቅሬታውን ይገልጻል።

ታሊባን ባለፈው ነሐሴ አገሪቱን ከተቆጣጠረ ወዲህ የዜጎች ገቢ በአንድ ሦስተኛ ቀንሷል። የምግብ ዋጋም ጣሪያ ነክቷል።

ሻፊ፣ ሻል የሚሉ ዳቦዎችን ከላስቲክ ከረጢቱ ውስጥ እያወጣ ያሳያል። አልሻገቱም እንጂ የቆዩ ዳቦዎች ናቸው። ቢሆንም ለምግብነት የሚገዟቸው ብዙዎች ናቸው።

"የአሁኑ የአፍጋኒስታናውያን ሕይወት ምንም ዓይነት ምግብና ውሃ እንደማታገኝ የታሰረች ወፍ ነው። ይህን መከራና ድህነት ከአገሬ እንዲወገድ እጸልያሁ" ይላል ሻፊ።

የረሃብ ስጋት በመኖሩ ሰብዓዊ ድጋፍ ይሰጣል።ግን በቂ አይደለም።

አፍጋኒስታን በልመና ዕርዳታ ላይ የተንጠለጠለች ናት። ታሊባን መንበረ ሥልጣኑን ሲቆጣጠር ምዕራባዊያን ይህንን ዕርዳታ አቋረጡ። የአገሪቱን ማዕከላዊ ባንክ ሐብትን ማገዳቸው ሲጨመርበት ደግሞ ቀውሱን አባባሰው።

እርምጃው የተወሰደው ከሴቶች አያያዝ ጋር በተያያዘ በተነሳ ስጋት ነው። ታሊባን አዲስ ይፋ ባደረገው ጥብቅ ገደብ ከሴቶች አለባበስ ጀምሮ የተለያዩ ሕጎችን አሳልፏል። ይህም ውሳኔውን አስቸጋሪ አድርጎታል።

ዳቦ ዋና ምግብ በሆነባት አፍጋኒስታን ብዙዎች ለመግዛት እየተፈተኑ ነው

የፎቶው ባለመብት, AFP

የምስሉ መግለጫ, ዳቦ ዋና ምግብ በሆነባት አፍጋኒስታን ብዙዎች ለመግዛት እየተፈተኑ ነው

ቀውሱ የሦስት ልጆች አባት እንደሆነው ሃሽማቱላህ ያሉ ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው ላይ ክንዱን አበርትቷል።

የዕለት ጉርሱን የገበያተኞችን ዕቃ በመሸከም ያገኛል። ገቢው በከፍተኛ ሁኔታ ቀንሷል። ካለፈው ዓመት አንድ አምስተኛውን ነው እያገኘ ያለው።

የተረፈ ዳቦ የገዛበትን ፌስታል እያሳየ “ከነጋ በሠራሁት መግዛት የቻልኩት ይህንን ነው” ብሏል።

የተረፈ ዳቦ ከሚሸጡት ሰዎች ጀርባ አንድ አነስተኛ ኢንዱስትሪ አለ። ቆሻሻ ሰብሳቢዎች ከምግብ ቤቶች፣ ከሆስፒታሎች እና ከግለሰብ ቤቶች ዳቦዎቹን ይሰበስባሉ። ከዚያም ለነጋዴዎች ይሸጣሉ።ገዢዎች ከእነዚህ ነው የሚገዙት።

ግማሽ ያህሉ ሕዝብ ወደ ረሃብ አረንቋ እየተገፋ ነው። ይህ ደግሞ የተረፈ ዳቦ የማግኘት ዕድልን ያጠበዋል።

ከአንድ ሳምንት በላይ የተሰበሰበውን አንድ ጆንያ የተረፈ ዳቦ እያሳየ "ሰዎች እየተራቡ ነው" ይላል አንድ የተጣሉ ዕቃዎች ነጋዴ። ቀደም ሲል ግን በቀን አንድ ጆንያ ይሰበስብ እንደነበር ይናገራል።

የተጣሉ ዕቃዎች ነጋዴ

ሌላ ነጋዴ ደግሞ "ንጹህ ዳቦ ካገኘን ብዙውን ጊዜ ራሳችን እንበላዋለን" ብሏል።

ሃሽማቱላህ የድሃዎች መናኸሪያ በሆነችው የካቡል ሰፈር በሚገኝው ቤቱ ለቤተሰቡ ምግብ ያዘጋጃል።

ሦስቱ ልጆቹ እንዲማሩለት የቻለውን ሁሉ ያደርጋል። ብዙ ወላጆች እንደሚያደርጉት ልጆቹን ወደ ሥራ ከመላክም ተቆጥቧል።

ሕይወታቸው በበሰበሰ ቲማቲም እና ሽንኩርት እና በከረመ ዳቦ ላይ ተንጠልጥሏል።

"በጣም ድሃ በመሆኔ እና ጥሩ ምግብ የማቅረብ አቅም ስለሌለኝ ቤተሰቦቼ ፊት አፍራለሁ" ይላል።

"ምንም ማድረግ አልችልም። ልበደር ብልስ ማን ያበድረኛል . . . ልጆቼ ጥሩ ምግብ ስለማያገኙ በጣም ቀጫጭን ናቸው።" ብሏል ሃሽማቱላህ በተሰበረ ስሜት።

ሃሽማቱላህ ለልጆቹ ምግብ ሲያዘጋጅ

ካቡል በሚገኙ ዳቦ መጋገሪዎች በር ላይ ህጻናት እና ሴቶች ተሰልፈው ማየት የተለመደ ነው። ምሽት ላይ ያልተሸጠ ትኩስ ናን ካገኘን በሚል ነው የሚሰበሰቡት።

አንዳንዶች እዛው ቁጭ ብለው ልብስ ይሰፋሉ። ቤት ሆነው ሲሰፉ ዳቦ ከተሰጠ ዕድሉ እንዳያመልጣቸው ነው ይህን የሚያደርጉት።

በአንድ ወቅት በቢሊዮን ዶላሮች ወደ አፍጋኒስታን ይፈስ ነበር።በዚያ ወቅትም ሙስና እና ጦርነት የዜጎችን ሕይወት ትግል አድርጎት ነበር።

አሁን ጦርነቱ አብቅቷል። ከሕይወት ጋር ያለው ግብግብ ግን እየከበደ መጥቷል።