“ፌስቡክ ስከፍት የአባቴን አስክሬን አየሁት”

የፎቶው ባለመብት, Fiseha Adugnaw Mintesnot
በኅዳር 2018 ሞቲ ደረጀ የዩኒቨርስቲ ተማሪ ነበር። ድንገት ፌስቡክ ሲከፍት የገዛ አባቱን አስክሬን ተመለከተ።
ከዚህ በላይ ምን የሚያስደነግጥ ነገር ይኖራል?
ያን ጊዜ ገና 19 ዓመቱ ነበር።
“ምን ልበልህ በቃ ደርቄ ቀረሁ” ብሏል ለቢቢሲ።
ኢትዮጵያ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ በነውጥ ውስጥ ናት። በተለያዩ አካባቢዎች ሰላም የለም።
ይህን ተከትሎ ማኅበራዊ ሚዲያው ዘግናኝ እና ሰቅጣጭ ምስሎች አያጣውም።
ጸብ እና ግጭትን የሚቀሰቅሱ መልዕከቶች ይናኙበታል።
በርካቶች መልዕክቱ ልክ ነው፣ አይደለም አይልም። ለበቀል ይነሳል። ይህ ያሳሰባቸው የሰላም ተቆርቋሪዎች ፌስቡክ አደገኛ መልዕክቶችን በጊዜ እንዲያነሳ ማሳሰብ አላቆሙም።
ፌስቡክ ግን የሚሰማ አልሆነም። ወይም ግድ አልሰጠውም።
ሞቲ ደረጀ ለምሳሌ የአባቱን አስክሬን በፌስቡክ ከተመለከተ በኋላ ታሪኩ በዚያው አላቆመም።
ሌሎች በርካቶች የአባቱን ምሥሎች በፌስቡክ ሲጋሩ አለመመልከት አልቻለም።
ተመሳሳይ ምሥል በስፋት ለቀናት ሲሰራጭ ነበር።
የሞቲ አባት የቀድሞ የምክር ቤት አባል ነበሩ። የዩኒቨርስቲ አስተዳዳሪም ነበሩ። በምዕራብ ኦሮሚያ አመጽ ሲነሳ የፖለቲካ ግድያ ነበር የተፈጸመባቸው።
በዚያ ወቅት ያ አካባቢ ከፍተኛ ግድያዎች ይፈጸሙበት የነበረ ነው።
“አባቴን ከገደሉት በኋላ እየጨፈሩ ነበር የሚመስለው፤ ያን ማየት ደግሞ ከፍተኛ ህመም ነው” ይላል ሞቲ።
ቢቢሲ ሞቲ የተመለከታቸውን 15 የሚሆኑ አሰቃቂ ምሥሎች መመልከት ችሏል። እነዚህ ምሥሎች እንዲነሱ ለፌስቡክ አቤት ብሏል፤ ሞቲ። ከአንዴም ሁለት፣ ሦስቴ።
የፌስቡክ ደንብ እንደሚለው እንዲህ ዓይነት ምሥሎች ቤተሰብ ካመለከተ ወዲያው ይወገዳሉ።
በተግባር ግን ይህ አልሆነም።
“የኢትዮጵያ ጉዳይ ለፌስቡክ ግድ አይሰጠውም”
ሞቲ ለቢቢሲ ሲናገር የአባቱን አስክሬን ለመጀመሪያ ጊዜ ከተመለከተው በኋላ ለፌስቡክ ምሥሉ እንዲወገድ ካመለከተ ከአራት ዓመት በኋላ እንኳን ምሥሉ አልተነሳም ነበር።
አንዳንድ ምሥሎች ላይ ብቻ “ይህ ምሥል አሰቃቂ ነው” የሚል ማስጠንቀቂያ ተደርጎበታል።
“አንዳንድ ጊዜ ከፍተኛ ድንዛዜ ውስጥ ስለምገባ እጄ አላርፍ ብሎ የአባቴን ስም አስገብቼ አስሳለሁ። በነገሩ አእምሮዬ ሳይረበሽ አልቀረም” ይላል ሞቲ።
ቢቢሲ የፌስቡክ አስተዳዳሪ ኩባንያ ሜታ በሞቲ ጉዳይ አስተያየት እንዲሰጥ ጠይቆ፣ ያገኘው ምላሽ ምንም እንኳ ምሥሉ የፌስቡክ ፖሊሲን የሚቃረን ባይሆንም፣ ቤተሰብ ከጠየቀ ግን እንዲህ ዓይነት ምሥሎች ይወገዳሉ ብሏል።
አሁን የሞቲ አባት የአስክሬን ምሥሎች ተነስተዋል።
ፌስቡክ ቤተሰብ ካመለከተ እናነሳለን ቢልም ይህን ለመተግበር ሜታ ሁነኛ መንገድ አላስቀመጠም።
ሜታ ግን ይህን ዓይነት ሁኔታ ሲከሰት ቤተሰብ የሚያመለክትበት አንድ መንገድ እያዘጋጀ መሆኑን ይናገራል።
በኢትዮጵያ በማኅበራዊ ሚዲያ መድረኮች ላይ የሚጋሩት ይዘቶች ከዕለት ወደ ዕለት ቁጥራቸው እየጨመረ መጥቷል።
በተለይ የትግራይ ጦርነት ከተጀመረ ወዲህ ወደ ሰዎች ሰሌዳ የሚመጡ የአሰቃቂ ምሥሎች ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ ጨምሮ ታይቷል።
በ2011 ዓም የፌስቡክ የበላይ ተቆጣጣሪ ቦርድ ኩባንያው በኢትዮጵያ ግጭቶች እንዲበራከቱ የጥላቻ ንግግሮች እንዲዛመቱ አድርጎ ከሆነ ገለልተኛ ወገን እንዲፈትሸው ምክረ ሐሳብ አቅርቦ ነበር።
ይሁንና ይህ ጥናት አልተደረገም። ቢቢሲ ሜታ ኩባንያን ለምን ምክረ ሐሳቡ ሳይተገበር ቀረ ብሎ ጠይቆ ነበር።
ቃል አቀባዩ እንዲህ ዓይነት ግምገማዎች አዋጪነታቸው ምን ያህል ነው የሚለው እየታየ እንደሆነ ካብራሩ በኋላ፣ ከዚህ ቀደም ከኢትዮጵያ ጋር ተያይዥ ግምገማዎች መደረጋቸውን ብቻ ገልጸዋል።
ባለፈው የፈረንጆች ዓመት ሜታ በሁለት ኢትዮጵያውያን ክስ ተመስርቶበታል።
ምክንያቱ ደግሞ ከሳሾቹ ኩባንያው በሚጠቀመው የበይነ መረብ ስልተ ቀመር (አልጎሪዝም) የተነሳ ጥላቻ እና ግጭት መስፋፋቱን፤ በእነርሱም ላይ ጉዳት እንደደረሰ ገልጸዋል።
ሜታ በበኩሉ ይዘቶች ላይ ቁጥጥር እንዲደረግ በሚል ከፍተኛ ገንዘብ ፈሰስ እንደሚያደርግ ነው የሚናገረው።
በአዲስ አበባ የፋክት ቼክ ባለሙያ የሆኑት ሮሆቦት አያሌው፣ ኩባንያው ችግሩን ለመፍታት ምን ያህል ርቀት ሄዷል በሚለው ላይ ጥያቄ አላቸው።
“በበኩሌ ኩባንያው ስለ ኢትዮጵያ እምብዛም ግድ የሚሰጠው አይመስለኝም” ይላሉ።
“ኩባንያው ለኢትዮጵያ ትኩረት ሰጠሁ ይላል። ምን ያህል ትኩረት እንደሰጠ ግን አናውቅም፤ እንዲያውም ይዘት ቁጥጥር አድራጊዎች ኢትዮጵያ ውስጥ ሳይሆን ከኬንያ ነው የሚሰሩት።”
ጨምረውም አደገኛ ይዘቶች ከፌስቡክ እስኪወገዱ ድረስ ዘለግ ያለ ጊዜ እንደሚወስደበትም አብራርተዋል።

የፎቶው ባለመብት, Fiseha Adugnaw Mintesnot
“ቁጣን ማቀጣጠል”
ሮሆቦት ባለፈው ዓመት መጋቢት ወር ላይ በስፋት የተሰራጨን አንድ ቪዲዮን ይጠቅሳሉ። ቪዲዮው አንድ የትግራይ ተወላጅ በሕይወት እያለ ሲቃጠል የሚያሳይ ነበር።
“በመጀመሪያ ይዘቶችን የሚከታተለው የሰው ሰራሽ አስተውሎት (አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ) ሥርዓት በራሱ ቪዲዮውን ማስወገድ ነበረበት” ሲሉ ሮሆቦት ያብራራሉ።
“ሪፖርት ከቀረበ በኋላም ቢሆን በፍጥነት መነሳት ነበረበት፤ ነገር ግን ቪዲዮው ለተወሰኑ ሰዓታት ቆይቷል።”
የሜታ ቃል አቀባይ ለቢቢሲ እንደተናገሩት በፌስቡክ እና በኢንስታግራም ላይ ስለተፈቀዱ እና ስለሚከለከሉ ጉዳዮች ጥብቅ መመሪያ እንዳለቸው ይገልጻሉ።
የጥላቻ ንግግሮች እና ግጭትን የሚያነሳሱ ይዘቶች ከደንቡ ጋር የሚቃረኑ በመሆናቸው፣ እንዲህ ያሉ ይዘቶችን ለማስወገድ በሰው ኃይል እና በቴክኖሎጂ ላይ ከፍተኛ መዋዕለ ነዋይ እያፈሰሱ መሆናቸውን ጠቅሰዋል።
“በዚህም እውቀቱ እና ሙያው ያላቸው ሠራተኞችን ቀጥረናል፣ አደገኛ ይዘቶችንም ለመቆጣጠር አማርኛ፣ ኦሮሚኛ፣ ሶማሊኛ እና ትግረኛን በመሳሰሉ በአገሪቱ በስፋት በሚነገሩ ቋንቋዎች ዙሪያ ያለንን አቅም ለማዳበር ጥረታችንን ቀጥለናል።”
አሰቃቂ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች ሲፈጸሙ የሕዝቡን ትኩረት እንዲያገኙ ማድረግ ጥሩ ነገር ቢሆንም፣ እንዲህ ያሉ ይዘቶች የተወሰኑ ግለሰቦችን ወይንም ቡድኖችን ተጠያቂ በማድረግ ቁጣን ሊያቀጣጥሉ ይችላሉ።
በተጨማሪም ይዘቶቹ በሺዎች ወይም በሚሊዮኖች በሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን ስለሚታዩ፣ ሰቆቃን የሚፈጥር ውጤት ይኖራቸዋል።
ከባድ ሰብአዊ ቀውስን ያስከተለው የትግራይ ጦርነት ባለፈው ጥቅምት ወር መጨረሻ ላይ በተደረሰው የሰላም ስምምነት ቆሟል።
በዚህ ሳቢያ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች እንደሞቱ የሚገመት ሲሆን፣ አብዛኛው ሞት በጦርነቱ ሳቢያ በተከሰተው በረሃብ እና በሕክምና አቅርቦት ችግር ምክንያት እንደሆነ ይነገራል።
በትግራይ ውስጥ ያለው ጦርነት ቢቆምም የኦሮሚያ ክልል እየጠነከረ በመጣ የአማጺያን እንቅስቃሴ እየተናጠ ነው።
በማኅበራዊ ሚዲያዎች ላይ በተደጋጋሚ የሚታዩት ሰቆቃዎች እርቅ እና መረጋጋትን ለማምጣት እንቅፋት ሊፈጥሩ እንደሚችሉ አክቲቪስቶች ይሰጋሉ።
“ሰዎች በማኅበራዊ ሚዲያዎች ላይ የሚወጡ ይዘቶችን ወደ ማመን ያዘነብላሉ፤ ስለዚህም በስፋት የተሰራጩ አፍራሽ ምስሎች በእርግጠኝነት የሰላም እና የእርቅ ሂደትን ዘገምተኛ ያደርጉታል” ብለዋል ሮሆቦት።
አሁን 23 ዓመት የሆነው ሞቲ፣ በፎቶግራፍ እና በቪዲዮ ቀረጻ ሙያ ላይ በመሰማራት ተረጋግቶ ሕይወቱን ለመቀጠል እየሞከረ ሲሆን፣ ስላለፈበት ሁኔታም ዘጋቢ ፊልም እያሰናዳ ነው።
“የደረሰብኝን ለመቋቋም የእራሴን ታሪክ ለመናገር ጊዜው አሁን ነው ብዬ አስባለሁ፣ ከተሳካልኝም ለውጥ ማምጣት እችል ይሆናል” ብሏል።
ነገር ግን አሰቃቂ ምስሎች በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ እንዳይስፋፉ ቁጥጥር ተደርጎ አስካልተገቱ ድረስ የሚሰማው ሰቆቃ እንደሚቀጥል ይናገራል።
“በፌስቡክ ወይም ሌላ ቦታ ላይ ከጦርነቱ ጋር በተያያዘ አስከሬን ስመለከተ፣ አንድ ሰው እኔ የተሰማኝ አይነት ስሜት እንደሚፈጠርበት ስለማስብ በጣም ነው የማዝነው።
“ይህም በጣም ነው የሚጎዳኝ።”












