በርካታ የፍልስጤም ደጋፊ ሰልፈኞች በኮሎምቢያ ዩኒቨርሲቲ በፖሊስ በቁጥጥር ስር ዋሉ

የጭንቅላት ጥምጣም (ከፊያ) ያደረጉ ተቃዋሚዎች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የኒው ዮርክ ከተማ ፖሊስ ረዕቡ ዕለት የኮሎምቢያ ዩኒቨርሲቲ ዋና ቤተ መጽሐፍት የተወሰነ ክፍሎችን ተቆጣጥረው የያዙ በርካታ የፍልስጤም ደጋፊ ሰልፈኞችን በቁጥጥር ስር አዋለ።

የዩኒቨርስቲው ፕሬዝዳንት ክሌር ሺፕማን ባወጡት መግለጫ፤ ሰልፈኞቹ ወደ በትለር ዋና ቤተ መጽሐፍት በኃይል በገቡበት ወቅት ሁለት ዩኒቨርስቲው የጥበቃ መኮንኖች መጎዳታቸውን ገልጸዋል። ድርጊቱንም "ከልክ ያለፈ" ሲሉ ኮንነዋል።

በማኅበራዊ ሚዲያ ገጾች የተለጠፈ አንድ ቪድዮ፤ የጭንቅላት ጥምጣም (ከፊያ) እና ጭንብል ያደረጉ በርካታ ተቃዋሚዎች በትራምፕ አስተዳደር የተጣለውን ዕገድ በመጣስ እየጮሁ ወደ ቤተ መጽሐፍቱ ሲገቡ አሳይቷል።

ፕሬዝዳንቷ ሺፕማን የኒው ዮርክ ፖሊሲን እገዛ እንደጠየቁ የገለጹ ሲሆን፣ ብዙዎቹ ተቃዋሚዎች ተማሪዎች እንዳልሆኑ ተናግረዋል።

ከ70 በላይ ተቃዋሚዎች በፖሊስ በቁጥጥር ስር እንደዋሉ 'ኮሎምቢያ ስፔክቴተር' የተባለው የዩኒቨርስቲው ካምፓስ ጋዜጣ ዘግቧል።

የኒው ዮርክ ከተማ ፖሊስ በኤክስ ገጹ ላይ ባሰፈረው መልዕክት፤ "በኮሎምቢያ ዩኒቨርሲቲ ቀጥተኛ ጥያቄ መሠረት የኒው ዮርክ ፖሊስ ግለሰቦቹ ቤተ መጽሐፍቱን ለተቆጣጠሩበት እና ጥሰው ለገቡበት ሁኔታ ምላሽ እየሰጠ ነው" ብሏል።

ቪድዮዎች፤ ተቃዋሚዎቹ "ነጻ ፍልስጤም" ብለው በመጻፍ የመጽሐፍ መደርደሪያዎችን ሲያወድሙ አሳይተዋል።

ሌላ ቪድዮ ደግሞ፤ የሕዝብ ደኅንነት መኮንኖች የቤተ መጽሐፍቱን መውጫ ሲዘጉ እና ውስጥ ያሉ ግለሰቦችን የኮሎምቢያ ዩኒቨርሲቲ መታወቂያቸውን እንዲያሳዩ አልያም እንዲታሰሩ ሲጠይቋቸው፤ ይህም ለሰዓታት የዘለቀ ፍጥጫን ሲያስከትል ያሳያል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት፤ ምንም እንኳን ተቃዋሚዎቹ ተነጥለው በቤተ መጽሐፍቱ አንድ ክፍል ውስጥ የነበሩ ቢሆንም፤ "ተማሪዎቻችን እያጠኑ እና ለማጠቃለያ ፈተና እየተዘጋጁ ባሉበት የተወሰኑ ግለሰቦች አካዳሚያዊ እንቅስቃሴዎችን ለማወክ መምረጣቸው ሙሉ በሙሉ ተቀባይነት የለውም" ብለዋል።

የቀድሞው ፕሬዝዳንት ከኃላፊነት መልቀቃቸውን ተከትሎ በመጋቢት ወር ቦታውን የተረከቡት ሺፕማን፤ ተማሪዎች ከቤተ መጽሐፍቱ እንዲርቁ ጠይቀዋል።

የኒው ዮርክ ከተማ ከንቲባ ኤሪክ አዳምስ፤ "በከተማችን ውስጥ ማንኛውንም ዓይነት ጥላቻ እና አመጻ አንታገስም" ሲሉ በኤክስ ገጻቸው ጽፈዋል።

ተቃዋሚዎች በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ባወጧቸው ልጥፎች፤ ዩኒቨርሲቲውን "ኃይል የተቀላቀለበት አፈና" በማድረግ ከስሰዋል። ለፖሊስ እና ለካምፓስ የሕዝብ ደኅንነት መኮንኖች መታወቂያቸውን ለማሳየት ፈቃደኛ እንዳልነበሩን ተናግረዋል።

የፍልስጤም ደጋፊ ተቃዋሚዎች የሃሚልተን አዳራሽን 24 ሰዓት ለሚጠጋ ጊዜ ከተቆጣጠሩበት ካለፈው ዓመት ሚያዝያ ወር ክስተት ወዲህ የኒው ዮርክ ከተማ ፖሊስ ወደ ኮሎምቢያ ዩኒቨርሲቲ ሲጠራ ይህ ለመጀመሪያው ጊዜ ነው።

ኮሎምቢያ፤ ብዙ ዩኒቨርሲቲዎች ፀረ ሴማዊነት እና አይሁድ ተማሪዎች ላይ የሚደርሱ ጥቃቶችን ታግሰዋል የሚል ወቀሳ በሚያቀርቡት ፕሬዝዳንት ትራምፕ ጥርስ ተነክሶበታል።

ትራምፕ ለዩኒቨርሲቲው የሚሰጥ 400 ሚሊዮን ዶላር የፌደራል መንግሥት የገንዘብ ድጋፍ እንዳይተላለፍ የያዙ ሲሆን፣ አስተዳደራቸውም ከዚህ ቀደም በነበሩ የካምፓስ ተቃውሞዎች ላይ የተሳተፉ ሰልፈኞችን ከሀገር ለማባረር ዒላማ ማድረጉን ቀጥሏል።

የፌደራል ፈንዱ መታገዱን ተከትሎ ኮሎምቢያ፤ በተቃውሞ ወቅት ጭንብል እንዳይደረግ መከልከልን እና አንዳንድ አካዳሚክ ፕሮግራሞች ላይ ቁጥጥር የሚደረግበትን መንገድ መቀየርን ጭምሮ ከትራምፕ አስተዳደር የቀረቡ በርካታ ጥያቄዎችን መጋቢት ላይ ተቀብሏል።

በሚሊዮኖች የሚቆጠረው ፈንድ ይመለስ አይመለስ ግልጽ ባይሆንም የተወሰኑ የዩኒቨርሲቲው አባላት እገዳውን በመቃወም ክስ አቅርበዋል።

የኒው ዮርኩ ዩኒቨርሲቲ፤ የፍልስጤም ደጋፊዎች በጋዛ የሚደረገውን ጦርነት እና አሜሪካ ለእስራኤል የምታደርገውን ድጋፍ በመቃወም ባለፈው ዓመት ያደረጓቸው ተቃውሞዎች ማዕከል ነበር።

ማክሰኞ ዕለት ትራምፕ የፌደራል ፋይናንስ እንዲገመገም ትዕዛዝ ካስተላለፉ በኋላ ለሀርቫርድ ዩኒቨርሲቲ ይሰጥ የነበረን 2.2 ቢሊዮን ዶላር የግብር ከፋዮች ገንዘብ አቋርጠዋል።

የትራምፕ አስተዳደር፤ ለ60 ዩኒቨርሲቲዎችን በሰጠው ማስጠንቀቂያ በካምፓሶች ውስጥ አለ ሲል የገለጸውን ፀረ ሴማዊነት በተመለከተ ዩኒቨርሲቲዎቹ ምላሽ የማይሰጡ ከሆነ ያገኙ የነበረው ገንዘብ እንደሚቋረጥ ዝቷል።