በለንደን የሚገኝ የእስራኤል ኤምባሲን የሽብር ድርጊት ዒላማ በማድረግ የተጠረጠሩ ሰዎች ተያዙ

ፖሊሶች የእስራኤል ኤምባሲ መግቢያን ዘግተው ቆመው

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ፖሊሶች መጋቢት ላይ ተቃውሞ በተደረገበት ጊዜ የእስራኤል ኤምባሲ መግቢያን ዘግተው ነበር

በለንደን በሚገኘው የእስራኤል ኤምባሲ ላይ የሽብር ድርጊት ለመፈጸም በመዘጋጀት የተጠረጠሩ አምስት ኢራናውያን በቁጥጥር ስር እንደዋሉ ቢቢሲ አረጋገጠ።

ፖሊስ ኦፕሬሽንን የተመለከቱ ምክንያቶችን በመጥቀስ፤ በኬንግስተን የሚገኘው ኤምባሲ ዒላማ እንደነበር ስለመጠርጠሩ በታይምስ የወጣውን ዘገባ እስካሁን አላረጋገጠም። ይሁን እንጂ ቢቢሲ ዘገባው ትክክል እንደሆነ ተረድቷል።

የሜትሮፖሊታን ፖሊስ ፀረ ሽብር ዕዝ ኃላፊ የሆኑት ኮማንደር ዶሚኒክ መርፊ፤ ስለ ድርጊቱ የሚደረገው ምርመራው "በፍጥነት እየሄደ ያለ" መሆኑን ገልጸዋል። ፖሊስ በጉዳዩ ላይ ተጨማሪ ዝርዝር መረጃዎችን እንዳያቀርብ ያስገደደዱት "ጉልህ ኦፕሬሽናል ምክንያቶች" መኖራቸውን ተናግረዋል።

የኢራን ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ሰይድ አባስ አራግቺ በኤክ ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት፤ ኢራን በድርጊቱ ላይ ማንኛውንም ዓይነት ተሳትፎ "በፍጹም እንደምትቃወም" ገልጸዋል። ሀገራቸው በምርመራው ላይ ለማገዝ ዝግጁ መሆኗንም አክለዋል።

በቁጥጥር ስር የዋሉት ሁለት የ29 ዓመት እንዲሁም የ40፣ 24 እና 46 ዓመት ወንዶች ቅዳሜ ዕለት የተያዙት "አንድ የተወሰነ ቅጽርን" ዒላማ አድርገዋል በሚል እንደሆነ ፖሊስ ገልጿል።

ግለሰቦቹ በቁጥጥር ስር የዋሉት በስዊንድን፣ ምዕራብ ለንደን፣ ስቶክፖርት፣ ሮችዴል እና ማንችስተር አካባቢዎች ነው።

በቁጥጥር ስር ከዋሉት ውስጥ አራቱ በሽብር ድርጊት የሚደረግባቸው ምርመራ ቀጥሏል። በፖሊስ እና በወንጀል ማስረጃነት የተያዘው አምስተኛው ሰው ደግሞ ግንቦት ወር ውስጥ የተቆረጠለት ቀን እስከሚደረስ በዋስ ወጥቷል።

 የታጠቁ ፖሊሶች ከአንድ ቤት ጀርባ ሲንቀሳቀሱ የሚያሳል ምስል
የምስሉ መግለጫ, ቅዳሜ ዕለት የታጠቁ ፖሊሶች በመላ ሀገሪቱ ተጠርጣሪዎች ለመያዝ ተንቀሳቅሰ ውነበር

የፖሊስ መኮንኖች በሚያደርጉት ምርመራ መሠረት በግሬተር ማንችስተር፣ ለንደን እና ስዊንድን አካባቢዎች ፍተሻዎችን አካሂደዋል።

የቪድዮ ቀረጻዎች፤ የታጠቁ ፖሊሶች አንድን ሰው በሮችዴል ከሚገኝ ቤት ሲወስዱ፣ በስዊንድን ደግሞ ክንዱ ላይ የፕላስቲክ ከረጢቶች የታሰሩበት ሌላ ሰው መንገድ ላይ እየተጎተተ ሲወሰድ አሳይተዋል።

ኮማንደር መርፊ፤ "በተቻለ ፍጥነት ተጨማሪ ዝርዝር መረጃዎቸን ለማጋራት [የምንችልበትን መንገድ] እንመለከታለን። እስከዚያው ድረስ ሕዝቡ ንቁ ሆኖ እንዲጠብቅ እንጠይቃለን" ብለዋል።

የሀገር ውስጥ ሚኒስትር ዳን ጃርቪስ ማክሰኞ ዕለት በዩናይትድ ኪንግደም ፓርላማ የታችኛው ምክር ቤት ባደረጉት ንግግር በመቶዎች የሚቆጠሩ የፖሊስ መኮንኖች በሀገሪቱ በሚገኙ የተለያዩ ቦታዎች ላይ የፎረንሲክ ምርመራ እያደረጉ መሆኑን ገልጸዋል።

ፖሊስ ያካሄደው እስር "በቅርብ ጊዜያት ውስጥ ከታዩ ትልቅ የሚባሉት የፀረ መንግሥት ስጋት እና ፀረ ሽብር ድርጊቶች መካከል እንደሆነ" ተናግረዋል።

አምስቱ ሰዎች በቁጥጥር ስር ዋሉት ሌሎች ሦስት ኢራናውያን በሌላ የፀረ ሽብር ምርመራ በተያዙበት ተመሳሳይ ቀን ነው።

ግለሰቦቹ በቁጥጥር ስረ የዋሉት ፖሊስ "በውጭ ኃይል የስጋት እንቅስቃሴ" የተጠረጠሩ ሰዎችን እንዲይዝ ሥልጣን በሚሰጠው ሕግ መሰረት ነው።