ኦፌኮ ለኦሮሚያ የጸጥታ መደፍረስ የአማራ ኃይሎችን ተጠያቂ ማድረጉን አብን ኮነነ

የፎቶው ባለመብት, NAMA
በኦሮሚያ ክልል ለሚስተዋለው የጸጥታ መደፍረስ የአማራ ክልል የጸጥታ ኃይሎች ተጠያቂ ናቸው ሲል የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ (ኦፌኮ) ያወጣውን መግለጫ የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) ኮነነ።
አብን ሚያዝያ 4/2014 ዓ. ም. ባወጣው መግለጫ "በተለያዩ የኦሮሞ የፖለቲካ ኃይሎች መካከል እየተደረገ ባለው የፖለቲካ ግብግብ ምክንያት በኦሮሚያ ክልል ለተፈጠረው የጸጥታ መደፍረስ እና የሰላም እጦት የአማራን ሕዝብ እና የአማራን የፖለቲካ ኃይሎች የጦስ ዶሮ ለማድረግ የሚኬድበትን መንገድ አብን አጥብቆ ያወግዛል" ሲል ለኦፌኮ መግለጫ ምላሽ ሰጥቷል።
የኦፌኮ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ሚያዝያ 3/ 2014 ዓ. ም. ባወጣው መግለጫ "ከአማራ ክልል የመጡ" ያላቸው ታጣቂዎች ወደ ኦሮሚያ ክልል በመግባት "የመሬት ወረራና የግዛት ማስፋፋት እየፈጸሙ እንዲሁም ሰላማዊ ሰዎችን እየገደሉ፣ አርሶ አደሮችን ከመሬታቸው በማፈናቀል የኦሮሚያ ክልልን ወደማያባራ የግጭት ቀጠና እየለወጡት ነው" ማለቱ ይታወሳል።
ኦፌኮ በተለይም በምሥራቅ ወለጋ፣ በሆሮ ጉድሩ ወለጋ፣ በሰሜን ሸዋ፣ በምዕራብ ሸዋ እና በምሥራቅ ሸዋ ዞኖች "በተቀናጀ አኳኋን የጦር ዘመቻና የመሬት ወራራ እየተፈጸመ እንደሆነ" ጠቅሷል።
አብን በምላሹ፣ ኦፌኮ በመግለጫው የጠቀሳቸው አካባቢዎች "በንጹሃን የአማራ ተወላጆች ላይ በተደጋጋሚ ጭፍጨፋ እና መፈናቀል የሚፈጸምባቸው ቦታዎች" መሆናቸውን ጠቅሶ፣ እነዚህ አካባቢዎች "በግልጽ የኦነግ-ሸኔ ታጣቂዎች የሚንቀሳቀሱባቸው እና ታጣቂዎቹ አብዛኞቹን አካባቢዎችን የሚቆጣጠሯቸው" በመሆናቸው ለጸጥታ መደፍረሱ ተጠያቂነቱ ወደ አማራ ክልል የፖለቲካ ኃይሎች መዞሩን አጣጥሏል።
አብን ባወጣው መግለጫ "በእነዚህ አካባቢዎች ለተፈጠረው የጸጥታ መደፍረስ እና የሰላም እጦት አማራ ተጠያቂ የሚሆነው ኦነግ-ሸኔ አማራ ነው፣ ታጣቂዎቹም የአማራ ገበሬዎች ናቸው ከተባለ ብቻ ነው። ኦፌኮ ኦነግ-ሸኔን እና ታጣቂዎችን በአማራነት እንደማይከስ ተስፋ እናደርጋለን" ብሏል።
በሌላ በኩል ኦፌኮ፣ በኢትዮጵያ መንግሥትና በኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት (መንግሥት ኦነግ-ሸኔ እያለ የሚጠራው ቡድን) መካከል እየተካሄደ ያለው ጦርነት እንዲቆምና ልዩነታቸውን በድርድር እንዲፈቱ መጠየቁን አብን እንደሚደግፍ ተገልጿል።
የኦሮሚያ ክልል "አሸባሪ" ተብሎ የተፈረጀውን እና እራሱን የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት ብሎ የሚጠራውን ታጣቂ ቡድን "ሙሉ በሙሉ ለመደምሰስ" የሚያስችለው "ጠንካራ ዘመቻ" እንደጀመረ ማስታወቁ አይዘነጋም።
የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት በበከሉ በቃል አቀባዩ በኩል ከመንግሥት ኃይሎች ጋር "ከፍተኛ ውጊያ" እያካሄደ እንደሚገኝ ገልጿል።
አብን ትላንት በሰጠው መግለጫ "የኦነግ-ሸኔ ታጣቂዎች" በኦሮሚያ ክልል ውስጥ እየፈጠሩ ካሉት የጸጥታ መደፍረስ እና ሰላም እጦት በተጨማሪ በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል፣ በሲዳማ ክልል፣ በደቡብ ክልል እና በአማራ ክልል በርካታ አካባቢዎች በንጹሃን ዜጎች እና በሕዝብ መሠረተ ልማቶች ላይ ጥቃት ሲያደርሱ ቆይተዋል ሲል ከሷል።
"ኦነግ-ሸኔ" በሚንቀሳቀስባቸው እና በሚቆጣጠራቸው የኦሮሚያ አካባቢዎች፣ ከአማራ ክልል የተነሱ ታጣቂዎች ወረራ ፈጸሙ የሚል መግለጫ መውጣቱ "አብንን አሳዝኗል" ሲልም ፓርቲው በመግለጫው አስፍሯል።
የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) በመግለጫው አክሎም "የሁሉም ኢትዮጵያውያን ጥቅሞች እና መብቶች የሚከበሩበት አማካይ እና አስቻይ የፖለቲካ ሥርዓት ለመፍጠር" የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ (ኦፌኮ) ጨምሮ ከየትኛውም ሕጋዊ የፖለቲካ ኃይል ጋር "ተቀራርቦ ለመሥራት" ዝግጁ ነው ብሏል።












