መንግሥትና የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት ጦርነቱን አቁመው ልዩነታቸውን በድርድር እንዲፈቱ ኦፌኮ ጠየቀ

የፎቶው ባለመብት, OFC
በኢትዮጵያ መንግሥትና በአሮሞ ነጻነት ሰራዊት መካከል እየተካሄደ ያለው ጦርነት እንዲቆምና ልዩነታቸውን በድርድር እንዲፈቱ የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ ጥሪ አቀረበ።
በሁለቱ አካላት መካከል ያለው ግጭት መንስዔው "ፖለቲካዊ ነው ያለው" ኦፌኮ መፍትሄውም "ፖለቲካዊ" መሆን እንዳለበትም በትናንትናው ዕለት ሚያዝያ 3፣ 2014 ዓ.ም የስራ አስፈፃሚ ኮሚቴው ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።
የኦሮሚያ ክልል ከቀናት በፊት "አሸባሪ" ብሎ የጠራውን የ"ሸኔን ኃይል" ሙሉ በሙሉ ለመደምሰስ የሚያስችል ጠንካራ ዘመቻ ተጀምሯል ብሏል።
በመንግሥት ኃይሎች እና በታጣቂ ቡድኑ መካከል ከፍተኛ ውጊያ እየተካሄደ መሆኑን የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት ቃለ አቀባይ ኦዳ ተርቢ በትዊተር ገጻቸው ላይ አስፍረዋል።
በአሁኑ ወቅት ጦርነቱ ከመፋፋሙና እንደ አዲስ ዘመቻ ከመጀመሩ ጋርም ተያይዞ ኦፌኮ ይህ ሁኔታ የኦሮሚያን ክልልን እንዲሁም አገሪቱን ለተጨማሪ አደጋ የሚዳርግ መሆኑንም አፅንኦት ሰጥቷል።
"መንግሥት ሰሞኑን በአዲስ መልኩ ያወጀው ዘመቻ በጥቂቱ ፈንጥቆ የነበረውን የሰላም ጭላንጭል መልሶ የሚያደበዝዝ፤ኦሮሚያና አገሪቱን ለተጨማሪ አደጋ የሚያጋልጥ እንጂ ዘላቂ መፍትሄ እንደማያስገኝ ደጋግመን ማሳሰብ እንፈልጋለን። " ብሏል
ከሰሞኑ የኦሮሚያ ክልል የፌደራል ኃይሎች እና የክልል ኃይሎች በቅንጅት በወለጋ፣ በጉጂ፣ በምዕራብ እና ሰሜን ሸዋ በሚንቀሳቀሱ የታጣቂዎቹ አባላት ላይ እርምጃ እየወሰዱ መሆናቸውን ገልጿል።
መግለጫው መንግሥት "ሸኔን" እደመስሳለሁ የሚለውን ሁኔታውን አቁሞ በሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል እንደተጀመረው የሰላም አካሄድ እንዲከተልም ጥሪ አቅርቧል።
"መንግስት 'ሸኔን ማጥፋት' ከሚለው ውጤት አልባ የዘመቻ አዙሪት ወጥቶ በሰሜኑ ያገራችን ክፍል እንደጀመረው ሁሉ በኦሮሚያ ክልል ያለውን አለመግባባትም ተመሳሳይ በሆነ ሰላማዊ አካሄድ እንዲፈታ በድጋሜ ጥሪ እናደርጋለን፡፡" በማለት አስፍሯል።
ስራ አስፈፃሚው ኮሚቴ ሚያዝያ 1፣ 2014 ዓ.ም ባደረገው ስብሰባ በተጨማሪ ያነሳው ሃሳብ ከአማራ ክልል የመጡ ያላቸው ታጣቂዎች በኦሮሚያ ክልል እየፈጠሩት ያለውን የጸጥታ ችግር አስመልክቶ ነው።
እነዚህ ታጣቂዎች ወደ ኦሮሚያ ክልል በመግባት " የመሬት ወረራና የግዛት ማስፋፋት እየፈጸሙ እንዲሁም ሰላማዊ ሰዎችን እየገደሉ፣ አርሷአደሮችን ከመሬታቸው በማፈናቀል የኦሮሚያ ክልልን ወደማያባራ የግጭት ቀጠና እየለወጡት ነው" ብሏል።
"የጦር ዘመቻና የመሬት ወራራ" እየተፈጸመ እንደሆነ ያሰፈረው ይህ መግለጫ ይህም ሁኔታ በምስራቅ ወለጋ፤ሆሮ ጉድሩ ወለጋ፤ሰሜን ሸዋ፤ ምዕራብ ሸዋና በምስራቅ ሸዋ ዞኖች፤ በተቀናጀ አኳኋን እየተካሔደ እንደሆነ መረዳቱንም ጠቅሷል።
ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴው በተጨማሪ አገሪቱ የተፈጠረው የዋጋ ግሽበትና የኑሮ ውድነትን አንስቶ በመወያየት መንስዔውም የርስ በርስ ጦርነቱ እንደሆነና መፍትሄው "ሀገሪቱን በሁሉም አቅጣጫ እያመሰ ያለውን የርስ በርስ ጦርነት ወደሚያስቆም ውይይትና ድርድር ፊትን ማዞር ብቻ ነው" ብሏል።
ጦርነቱ የውስጥና የውጪ ንግድ እንዲቀዛቀዝ፣ የግብርናና ፋብሪካዎች ምርታማነት እንዲቀንስ፣ የውጪ ኢንቨስትመንት እንዲዳከም እንዲሁም በማዕቀቡ ምክንያት በእርዳታና በብድር ወደ አገር ይገባ የነበረ ገንዘብ እንዲቀንስ ወይም እንዲቋረጥ በማድረጉ የአገሪቱ ምጣኔ ኃብት ላይ ከፍተኛ ጫና አሳርፏል ይላል የኦፌኮ መግለጫ
በአጠቃላይ በአገሪቱ እየተከሰቱ ያሉ የጸጥታ ችግሮችም ሆነ የኑሮ ውድነቱን ችግር ለመፍታት በተለያዩ ስፍራዎች ያሉ ግጭቶችን ማስቆምና የፖለቲካ ልዩነቶችን በምክክር መፍታት አስፈላጊ ነው ሲል አሳስቧል።
"መንግሥትም ሆነ ማንኛውም ታጥቆ የሚንቀሳቀስ ኃይል ወደምክክር መድረክ በመመለስ፤ የኢኮኖሚ ውድቀት፤ በህዝብ ላይ የተጫነውን መከራ፤ እንዲሁም አገሪቱን ከብተና እንዲያድኑ ጥሪ እናስተላልፋለን፡፡" በማለት መግለጫው አስፍሯል።












