ኩረጃን እንደ 'መልካም ተግባር' የሚረዱት ተማሪዎች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የ2013 ዓ.ም የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና ውዝግቦችን ያስተናገደ ነበር። ከውዝግቡ ባሻገር ደግሞ የመጀመሪያው ዙር የሲቪክስ የፈተና ውጤት ለዩኒቨርስቲ መግቢያ መወዳደሪያነት እንዳያገለግል ተወስኗል።
ለዚህም የተሰጠው ምክንያት "የመጀመሪያው ዙር የሲቪክስ ፈተና በሁሉም ትምህርት ቤቶች በሚባል ደረጃ የውጤት መመሳሰልና ግሽበት" መታየቱ ነው ይላል።
ይህ የውጤት መመሳሰል ከኩረጃ ጋር በተያያዘ የመጣ ሲሆን ኤጀንሲው በብሔራዊ ፈተና ወቅት ጥሰት ፈጽመዋል ያላቸውን 141 ተማሪዎች ከውጤት መሰረዝ ጀምሮ በየደረጃው የተለያየ አስተዳደራዊ እርምጃ መወሰዱንም አስታውቆ ነበር።
ኩረጃ በአገር አቀፍ ፈተናዎች ብቻ ሳይሆን በዕለት ተዕለት የትምህርት ስርዓት ወቅት የሚያጋጥም መሆኑን የትምህርት ባለሙያዎች ይናገራሉ።
ቢቢሲ ለዚህ ጽሑፍ ሲል ያነጋገራቸው ተማሪዎችም ቢሆን በፈተና ወቅት የምዘና ወረቀቶች ተሰርቀው እንደሚወጡ እና በቴሌግራም በሰፊው እንደሚሰራጩ ያላቸውን ልምድ በመጥቀስ ተናግረዋል።
ትምህርት ሚኒስቴርም ቢሆን የአገር አቀፍ ፈተናው በቴክኖሎጂ ተደግፎ በኦንላይን ሥርዓት ታግዞ ካልተሰጠ የምዘናው ሥርዓት አደጋ ውስጥ መሆኑን በአንድ ወቅት ገልጾ ነበር።
ኩረጃን እንደ መልካም ተግባር የሚረዱት ተማሪዎች
ወንድይፍራው ደጀኔ (ዶ/ር) በድሬ ዳዋ ዩኒቨርስቲ በኢዱኬሽን ትምህርት ክፍል መምህር ናቸው። በሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች መካከል ስላለ ኩረጃ ጥናት አድርገዋል።
ከዚህ ቀደምም በድሬ ዳዋ ዩኒቨርስቲ የሚማሩ ተማሪዎች ስለኩረጃ ያላቸው አመለካከት ምን ይመስላል? የሚለውን ጥናት ሰርተው እንደነበር ይናገራሉ።
በዚህ ጥናታቸውም ተማሪዎች ኩረጃን 'ጉዳት የሚያስከትል ነው' ብለው እንደማያምኑ መረዳታቸውን ከቢቢሲ ጋር በነበራቸው ቆይታ አስረድተዋል።
ማስኮረጅን "ጓደኛን እንደመርዳት አድርገው ስለሚያስቡ እንደመልካም ተግባር" እንደሚረዱት ይናገራሉ።
ወንድይፍራው (ዶ/ር) እንደሚናገሩት ከሆነ ኩረጃ በትምህርት ስርዓት ውስጥ የእለት ተዕለት ተግባር እንደሆነ በጥናታቸው ወቅት መገንዘባቸውን ያስረዳሉ።
ተማሪዎች ለመኮረጃቸው አልያም ለማስኮረጃቸው የሚያቀርቡት ምክንያት የተለያየ ቢሆንም በቀዳሚነት የሚያነሱት ግን ወደ ቀጣዩ ክፍል ለማለፍ፣ ሰውን ለመርዳት፣ መምህሩ በሚገባ ስለማያስተምር የሚል እንደሆነም ጨምረው ገልፀዋል።
እንደ ወንድይፍራው (ዶ/ር) ገለፃ በግልም ሆነ በመንግሥት ትምህርት ቤቶች የሚማሩ ተማሪዎች በኩረጃ ረገድ ልዩነት የሌለው ተሳትፎ ያደርጋሉ።
ኩረጃ ምንድን ነው?
በኢትዮጵያ ከቴክኖሎጂ መርቀቅ ጋር ተያይዞ የሚታዩ ኩረጃዎችን ለማስቀረትም በብሔራዊ ፈተና ወቅት የበይነ መረብ አገልግሎት እንዲቋረጥ የተደረገበት ጊዜም ሩቅ አይደለም።
ይህ ብቻም ሳይሆን የፈተና ወረቀቶች እንደገና የተፃፉበትና የተዘጋጁበት ጊዜም አይዘነጋም።
ከዚህ ቀደም ቢቢሲ በሰራው አንድ ዘገባም በአማራ ክልል ተማሪዎች ለኩረጃ ይመቻቸው ዘንድ ከጎበዝ ተማሪዎች ጋር በማመሳሰል ስማቸውን በፍርድ ቤት አስለውጠዋል።
ኩረጃ፤ በአገር አቀፍ ደረጃ የትምህርት ሥርዓቱን የሚፈታተን ማነቆ እንደሆነ እኚሁ ምሁር ይስማማሉ።
ኩረጃ በአንድ የፈተና ክፍል ውስጥ ብቻ የሚካሄድ ሳይሆን በዕለት ተዕለት ትምህርት ስርዓት ውስጥ የሚዳብር መሆኑን ጨምረው ያስረዳሉ።
የራስ ያልሆነን ስራ እንደራስ አድርጎ ማቅረብ፣ ትክክለኛ ምክንያት ባለመስጠት መምህሩን ማሳሳት እና የማይገባውን ውጤት ለማግኘት የሚደረግ ጥረት፣ ያልተገባ ውጤት ለማግኘት መምህርን ማታለል በአጠቃላይ ኩረጃ ነው ይላሉ ወንድይፍራው (ዶ/ር)።
ጓደኛ እንዲኮርጅ መርዳት፣ በግል የተሰጠ ምዘናን ወይንም የቤት ሥራ በቡድን መስራት ሁሉ በኩረጃ ስር እንደሚጠቃለሉ ጨምረው ይገልጻሉ።
በትምህርት ቤት ሕይወታቸው ቢያንስ አንድ ጊዜ በኩረጃ ላይ የተሳተፉ ግለሰቦች በርካታ መሆናቸውን በተለያዩ አገራት የተሰሩ ጥናቶች ያሳያሉ።
ተማሪዎች የሚኮርጁት ለፈተናው ወይንም ደግሞ ምዘናው በቂ የስነልቦና ዝግጅት ሳይኖራቸው ሲቀር መሆኑን ይናገራሉ።
ተማሪዎች በተገቢው መጠን ራሳቸውን ካለመዘጋጀት ውጪ፣ ትምህርትን በአግባቡ አለመከታተል፣ ኩረጃ አሉታዊ ተጽዕኖ እንደሌለው ግንዛቤ መያዝ ወደ ኩረጃ የሚገፉ ሌሎች ምክንያቶች ናቸው ይላሉ።
ከዚህም በተጨማሪ ወንድይፍራው (ዶ/ር) እንደሚሉት የወላጆች 'ልጆቼ ተምረው፣ ሕይወቴን ይለውጡኛል' የሚለው ገለጻ ልጆች ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ ያሳርፋል።
ይህ ቤተሰብ የሚያደርገው ጫና ተማሪዎችን ለማበረታታት የተደረገ ነገር ቢሆንም ለኩረጃ እንደሚገፋም ያስረዳሉ።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በራሱ ጥረት ወላጆቹ ወዳሰቡለት ስኬት መድረስ ያልቻለ ተማሪም የወላጆቹን ጫና ለመሸሽ ጎበዝ የሚባሉ ተማሪዎችን በመደገፍ ጥሩ ውጤት ለማስመዝገብ ይሞክራል በማለት ሃሳባቸውን ያጠናክራሉ።
ኩረጃ ከክፍል ክፍል ሲኬድ እያደገ የሚሄድ ብቻ ሳይሆን፣ በሕይወት ውስጥ ዘላቂ የሆነ ተጽዕኖ እንዳለውም ጨምረው ገልፀዋል።
"ጥናቶች እንደሚያመለክቱት በትምህርት ዓለም የነበረን የኩረጃ ሕይወት ወደ ሥራ ዓለም ስንገባም ያንኑ የመተግበር እድሉ ከፍተኛ እንደሆነ እና ተያያዥነት እንዳለው ነው፤ አንድ የሁለተኛ ደረጃ ተማሪ በኩረጃ ታግዞ ወደ ከፍተኛ ተቋም ሲገባ፣ እዚያም በኩረጃ ታግዞ ቢመረቅ በስራው ዓለም መደለያ ለመቀበል አያቅማማም።"
ተማሪዎች በጓደኞቻቸው ዘንድ ሰነፍ ሆኖ ላለመታየት፣ በውጤት አንሶ ላለመገኘት፣ ወደ ኩረጃ እንደሚገቡም አክለው ተናግረዋል።
ኩረጃን የሚፀየፍ ተማሪ የለም?
በዓለማችን ላይ ከ1940ዎቹ ጀምሮ የተረደረጉ ጥናቶች እንደሚያሳዩት ኩረጃ በመላው ዓለም እያደገ እና ስልቱን እየቀየረ የመጣ ተግባር ነው።
በ1940ዎቹ የኩረጃ መጠን 42 በመቶ ሲሆን አሁን 92 በመቶ ደርሷል። አሁን ደግሞ ከመቶ ተማሪ ዘጠና ሁለቱ ኩረጃ ላይ መሳተፋቸውን ጥናቶች ያሳያሉ።
ኩረጃ ከጊዜ ወደ ጊዜ መልኩን እየቀየረ መምጣቱን ተማሪዎች ይናገራሉ። በፈተና ወቅት መልስ በቁራጭ ወረቀት ጽፎ መቀባበል አሁን አይታሰብም።
ተንቀሳቃሽ ስልክን ተጠቅሞ መልዕክት በመጠቀም መኮራረጅ የዘመኑ ገፀበረከት ነው።
ወንድይፍራው (ዶ/ር) በሰሩት ጥናት ተማሪዎች አብዛኛውን ጊዜ የሚያጠፉት 'እንዴት አድርጌ እኮርጃለሁ' የሚለው ላይ እንደሆነ ያስረዳሉ።
ተማሪዎች በተለይ የፈተና ወቅት ሲደርስ፣ የአገር አቀፍ እና ክልላዊ ፈተናዎች ባሉባቸው ክፍሎች (8ኛ እና 12ኛ) የኩረጃ ስልት በአግባቡ እስከመንደፍ ይደርሳሉ።
ወንድይፍራው(ዶ/ር) ጥናታቸውን በመጥቀስ ለኩረጃ በክፍል ውስጥ አንድ ጎበዝ የሚባል ተማሪ ካለ በቂ ነው ይላሉ።
ተማሪዎቹ ወደ መፈተኛ ክፍል ከመግባታቸው በፊት፣ ለኩረጃ ሲዘጋጁ ኔትወርክ ፈጥረው፣ የመጀመሪያው እቅድ ባይሳካ በሚል ሁለት እና ሶስት እቅዶችን ነድፈው መሆኑንም ጠቅሰዋል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ከዚህ በተጨማሪ የነደፉት ስልት በፈተና የመጀመሪያ ቀን ካልሰራ፣ ለቀጣዩ ፈተና ቀን ሌላ ስልት ነድፈው እንደሚመጡም ይናገራሉ።
ከዚህ የሞባይል ቴክኖሎጂን ተጠቅመው በሚያደርጉት ኩረጃም ከትምህርት ቤት ውጪ ያሉ ግለሰቦችን እንደሚያካትቱ ጨምረው ያስረዳሉ።
አንዳንድ ትምህርት ቤቶች በቀጥታም ባይሆን በተዘዋዋሪ ተማሪዎችቻቸውን የመደገፍ ነገር ማስተዋላቸውን የሚናገሩት ወንድይፍራው (ዶ/ር) ፣ በትምህርት ቤቶች መካከል ያለው ውድድር ለዚህ አስተዋጽኦ ማድረጉን ይጠቅሳሉ።
ለፈተና ስርቆት እና ኩረጃ መስፋፋት እገዛ የሚያደርገው ቴክኖሎጂ ብቻ ሳይሆን የመምህራን እና የትምህርት ቤቱ አስተዳደሮች ቁርጠኛ አለመሆን ጭምር መሆኑንም አክለው ገልፀዋል።
በኩረጃ ሲሳተፉ የተገኙ ተማሪዎች ላይ የሚወሰዱ እርምጃዎች ምን ያህል ፈጣን እና አስተማሪ ናቸው? ሲሉ የሚጠይቁት ምሁሩ፣ የተወሰደ እርምጃ ቢኖር እንኳ ለተማሪዎች በፍጥነት አለመንገር ለኩረጃ መስፋፋት አስተዋጽኦ ያደርጋል ሲሉ ሃሳባቸውን ያጠናክራሉ።
ኩረጃን ማስቀረት ይቻላል?
ኩረጃን ማጥፋት ሳይሆን መቀነስ ይቻላል የሚሉት ወንድይፍራው (ዶ/ር) ከመጀመሪያ ደረጃ ጀምሮ ተማሪዎች ስለታማኝነት እየተማሩ መምጣት እንዳለባቸው ይመክራሉ።
ታዳጊዎች ከታች ክፍል ጀምሮ መኮረጅ አስፀያፊ መሆኑን እየነገሩ ማሳደግ በኋላ በከፍተኛ ትምህርት ተቋምም ሆነ በሁለተኛ ደረጃ ላይ በስነምግባር የታነፀ ትውልድ እንዲኖር ይረዳል።
ከሥርዓተ ትምህርት አንጻርም ስለኩረጃ፣ ስለታማኝነት በየትምህርት ዓይነቶቹ ላይ ማካተት እንደሚያስፈልግ ያስረዳሉ።
መምህራንም ቢሆኑ ኃላፊነት ተሰምቷቸው በትክክል ተማሪዎቻቸውን መመዘን የሚያስችል ፈተና ማዘጋጀት ይጠበቅባቸዋል ሲሉ ይመክራሉ።
ፈተና በሚሰጥበት ክፍል ውስጥም ቢሆን መምህሩ በአግባቡ መፈተን መቻሉ ኩረጃን ለመቀነስ የራሱ አስተዋጽኦ አለው ሲሉ ያስቀምጣሉ።
የትምህርት አስተዳደሮችም ቢሆኑ ለተማሪዎች በሚያወጧቸው መመሪያዎችን እና መተዳደሪያ ደንቦችን በአመቱ መጀመሪያ ላይ ለተማሪዎቹ በሚገባ ማስተዋወቅ እንደሚያስፍልጋቸው ይገልጻሉ።
የወጡ መመሪያና ደንቦችን ተከትሎም ለሚፈፀሙ ጥፋቶች የተቀመጡ ተገቢ ቅጣቶችን ሳይዘገዩ ተፈጻሚ ማድረግ ወሳኝ መሆኑን ያብራራሉ።
ተማሪው ያጠፋውን ጥፋትን እና ቅጣቱን ለማገናኘት እንዲችል፣ ሲኮርጅ እንደተያዘ ወድያውኑ እርምጃ መውሰድ ለትምህርት ቤቱ ተማሪዎችም ወዲያውኑ ማሳወቅ እንደሚገባ ይናገራሉ።
















