ዛሬ በሚካሄደው የ5ሺህ ሜትር ፍጻሜ ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ተጠባቂ ናቸው

ሲፈን ሃሰን፣ ሄለን ኦቢሪ እና ጉዳፍ ፀጋይ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, የ5ሺህ ሜትር ተጠባቂ አትሌቶች መካከል [ከግራ ወደ ቀኝ] ሲፈን ሃሰን፣ ሄለን ኦቢሪ እና ጉዳፍ ፀጋይ

ዛሬ ከሰዓት በሚካሄዱ ሁለት የፍጻሜ ውድድሮች ኢትዮጵያውያን አትሌቶች የሜዳሊያ ሰንጠረዥ ውስጥ ይገባሉ ተብሎ ይጠበቃል።

ከሰዓት 9፡40 ላይ የሚጀምረው የሴቶች 5ሺ ሜትር የፍጻሜ ውድድር በጉጉት የሚጠበቅ ነው። በዚህ የፍጻሜ ውድድር ጉዳፍ ጸጋይ፣ እጅጋየሁ ታዬ እና ሰንበሬ ተፈሪ ተጠባቂ ናቸው። ትውልደ ኢትዮጵያዊቷ ሲፋን ሐሰን ደግሞ ዋነኛ ተፎካካሪ ነች።

ጉዳፍ ፀጋይ በዚህ ዓመት የካቲት ወር ላይ በፈረንሳይ በተካሄደ የ1ሺህ 500 ሜትር የቤት ውስጥ ውድድር ክብረ ወሰን ማሻሻል ችላለች።

ሰንበሬ ተፈሪ ደግሞ በአውሮፓውያኑ 2015 ላይ ቻይና ቤጂንግ በተካሄደው የ5ሺ ሜትር ውድድር ሁለተኛ ሆና መጨረስ ችላለች።

ሌላኛዋ ኢትዮጵያዊት አትሌት እጅጋየሁ ታዬ በበኩሏ ከዚህ በፊት በኦሎምፒክ ተሳትፋ የማታውቅ ሲሆን በ2018ቱ የታዳጊዎች የዓለም ሻምፒዮና ሁለተኛ ሆና አጠናቃለች።

በዚህ ምድብ ኬንያውያኑ ሄለን ኦቢሪ እና አግነስ ቲሮፕ እንዲሁም ለኔዘርላንድስ የምትሮጠው ሲፋን ሐሰን ቀንደኛ ተፎካካሪዎች እንደሚሆኑ ይጠበቃል።

ከሴቶች የፍጻሜ ውድድር ቀደም ብሎ ደግሞ የወንዶች 3ሺህ ሜትር መሰናክል የፍጻሜ ውድድር ከቀኑ 9፡15 ላይ ይጀምራል።

ከቀናት በፊት በተካሄደው ማጣሪያ ግርማ ላሜቻ እና ዋለ ጌትነት ለፍጻሜ ማለፋቸውን ያረጋገጡ ሲሆን የሜዳሊያ ዝርዝር ውስጥ እንደሚገቡ ይጠበቃል።

ዋሌ ጌትነት በዳይመንድ ሊግ ውድድር በ3 ሺ ሜትር መሰናክል ማሸነፍ የቻለ የመጀመሪያው ኢትዮጵያዊ ሲሆን በኦሎምፒክ ሲሳተፍም የመጀመሪያው ነው።

እሁድ ሌሊት ከ9፡35 ጀምሮ በተካሄደ የሴቶች 1500 ሜትር ማጣሪያ ደግሞ ከሶስቱ ኢትዮጵያውያን አትሌቶች መካከል ሁለቱ ወደ ቀጣዩ ዙር ማለፋቸውን አረጋግጠዋል።

አትሌቶቹም ፍሬወይኒ ኃይሉ እና ለምለም ኃይሉ ናቸው። ሌላኛዋ አትሌት ድርቤ ወልተጂ ደግሞ 12ኛ ሆኗ በማጠናቀቋ ማጣሪያውን ሳታልፍ ቀርታለች።

በ3ሺ ሜትር የሴቶች መሰናክል ውድድር በተለያየ ምደብ ተደልድለው ውድድራቸውን ካደረጉት ሶስት ኢትዮጵያውያን አትሌቶች መካከል ሁለቱ ማጣሪያውን ማለፍ ችለዋል።

አትሌቶቹም መቅደስ አበበ እና ዘርፌ ወንድማገኝ ሲሆኑ አትሌት ሎሚ ሙለታ ደግሞ 10ኛ ሆና በማጠናቀቋ ማጣሪያውን ሳታልፍ ቀርታለች።

ማጣሪያውን ያለፉት ሁለቱ አትሌቶችም የፊታችን ረቡዕ በሚካሄደው የፍፃሜ ውድድር ላይ ኢትዮጵያን ወክለው ይወዳደራሉ።