ናሳ ከጨረቃ ላይ የአፈር ናሙና ለሚያመጣለት ኩባንያ 1 ዶላር ብቻ ሊከፍል ነው

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ናሳ የአፈርና የዓለት ናሙና ከጨረቃ ላይ ለሚያመጣልኝ ኩባንያ ጠቀም ያለ ገንዘብ እከፍላለሁ ባለው መሰረት በርካታ ግዙፍ ኩባንያዎች ተወዳድረው ነበር።
ጨረታውን ያሸነፈው ኩባንያ ተለይቷል። ይህን ግዙፍና ውስብስብ ሥራ ሲያጠናቅቅ የሚከፈለው ግን አንድ ዶላር ብቻ ነው።
በዚህ በርካቶች በተሳተፉበት ውድድር ዝቅተኛ ዋጋ በማቅረብ ያሸነፈው "ሉናር አውትፖስት" የተባለ ኩባንያ ነው።
ይህ ኩባንያ ለአሜሪካው የሕዋ ኤጀንሲ ሥራውን ለመሥራት በ1 ዶላር ዋጋ ነው ስምምነት የተፈራረመው።
ናሳ ከዚህ ስምምነት ጋር ሌሎች አራት ተመሳሳይ ኮንትራቶችን ያስፈረመ ሲሆን አራቱም እጅግ ዝቅ ባለ ዋጋ የተሰጡ ኮንትራቶች ናቸው ተብሏል።
ዓላማውም በዝቅተኛ ዋጋ ጨረቃ ላይ ያሉ ነገሮችን ናሙና ማስቀለቀም ነው ተብሏል።
ከአራቱ ጨረታዎች አንዱን ያሸነፈው ሌላኛው ኩባንያ መቀመጫውን ካሊፎርኒያ ያደረገው "ማስተን ስፔስ ሲስተም" ሲሆን ሦስተኛው ኩባንያ ደግሞ ቶክዮ የሚገኘው "አይስፔስ" ነው።
ናሳ ለነዚህ ኩባንያዎች አገልግሎት ለእያንዳዳቸው አንድ አንድ ዶላር ይከፍላቸዋል። ሥራቸው የሚሆነው ጨረቃ ሄደው ከ50 እስከ 500 ግራም የሚመዝኑ ሪጎሊስ ወይም የጨረቃ አፈር (ዐለቶችን) ጭኖ ማምጣት ነው።
የጨረቃ ዐለቶች በቢሊዮን ዓመታት ዕድሜ ያላቸው ናቸው።
"እነዚህ ኩባንያዎች የጨረቃ አፈር ናሙና ለቅሞ ማምጣት ብቻ ሳይሆን ያን ስለማድረጋቸው በቪዲዮ የተደገፉ መረጃዎችን ማቅረብ አለባቸው" ብለዋል የናሳ ቃል አቀባይ።
ይህ ሥራ የሚከናወነው በ2023 እንደ ፈረንጆቹ አቆጣጠር ነው።
መቀመጫውን ኮሎራዶ ያደረገው ሉናር አውትፖስት የሮቦት ድርጅት ሲሆን ከደቡባዊ የጨረቃ ዋልታ አፈር ሰብስቦ ለማምጣት የአንድ ዶላር ኮንትራት ማሸነፉ እጅጉኑ አስደስቶታል።
ይህ ድርጅት በዚህ ሥራ ለመሰማራት ዋና ዓላማው ገንዘብ አይደለም።
ኩባንያዎቹ ይህንን ሥራ ካሳኩ በኋላ በርከት ያሉ ሳይንሳዊ ትርፎችን ያገኛሉ። አንዱ ተስፋቸው ከጨረቃ ወለል የሚገኙ ማዕድናትን እንዲያወጡ ዕድል ስለሚሰጣቸው ነው።
ይህ ነው በ1 ዶላር ክፍያ እንዲህ ዓይነት ውስብስብ ኮንትራት ውስጥ ለመግባት የሚያበረታታቸው።
ኩባንያው አሁን "ብሉ ኦሪጅን" ከተባለ ሌላ ግዙፍ ኩባንያ ጋር እየተነጋገረ ነው። ንግግሩ ያተኮረው ወደ ጨረቃ የሚያሳፍር የሕዋ ታክሲ ለመኮናተር በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ነው።
"ብሉ ኦሪጅን" የምድራችን የናጠጠው ቁጥር አንድ ሀብታም የአማዞኑ ጄፍ ቤዞስ ኩባንያ ነው። ዋና ሥራው ሰዎችን ህዋ አሳፍሮ መመለስ ነው።
ከናሳ ጋር ርካሽ የሥራ ውል ካደረጉት ድርጅቶች መካከል የጃፓኑ "አይስፔስ" ይገኝበታል።
አይስፔስ በሰሜን ምሥራቅ ዋልታ በ2020 ዓ ም ለሚሰበስበው የጨረቃ ዐለት 5ሺ ዶላር ቁርጥ ክፍያ ያገኛል።
የሐዋ ጉዳዮች ተንታኝ ሲኒየድ ኦ ሱሊቫን እንደሚሉት ለዚህ የሥራ ሥምምነት 1 ዶላር ቀላል ገንዘብ አይደለም።
ምክንያቱም ይላሉ ተንታኙ፤ ኩባንያዎቹ በዚህ የሥራ ውል ስምምነት የሚገቡት ገንዘቡን ብለው አይደለም። ወደፊት የሚፈጥርላቸውን ዕድል ታሳቢ በማድረግ ነው። ይህ ኮንትራት ገዢና ሻጭ ከመሬት ውጭ ባለ ነገር ላይ እየተፈራረሙ እንደሆነ መዘንጋት የለበትም ብለዋል።
የሚደንቀው አንድ ዶላር መከፈሉ ብቻ አይደለም።
ኩባንያው ከጨረቃ የአፈር ናሙና ለማምጣት 1 ዶላሩ የሚከፈለው በሦስት ዙር መሆኑ ነው።
መጀመርያ ውሉን ሲያስር የአንድ ዶላር 10 በመቶ ይከፈለዋል፤ ይሄ ተከፍሎታል። ቀጥሎ ደግሞ መንኩራኩር ተሳፍሮ ሲሄድ ነው። ሦስተኛውና ትልቁ ክፍያ ናሙናዎቹን ከጨረቃ ጭኖ አምጥቶ ሲያስረክብ ነው። ያን ጊዜ የአንድ ዶላር 80 ከመቶ ይከፈለዋል።
"አዎ ይህ ቀልድ ሊመስል ይችላል፤ 1 ዶላር የሚከፈለው በአንድ ጊዜ አይደለም። በ3 ዙር ነው። መጀመርያ $0.10, ከዚያ ደግሞ $0.10, በመጨረሻም $0.80 ክፍያ ይፈጸማል ብለዋል" ቃል አቀባዩ ሳይረስ።
ይህ ስምምነት የተፈረመው ቻይና የጨረቃ ናሙና ለማምጣት መንኩራኩር በላከች ማግስት ነው።
የቻይናው ቼንጅ5 የጨረቃ መንኩራኩር አሁን በዚህ ሰዓት ናሙናዎቹን ጭኖ ወደመሬት በመምጣት ላይ ይገኛል።












