ፕሬዝዳንት ትራምፕ ጨረቃ ላይ ማዕድን ቁፋሮ እንዲጀመር ለምን ፈለጉ? መብቱስ አላቸው?

ፕሬዝደንት ትራምፕ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ ሃገራቸው ጨረቃ ላይ ማዕድን ቁፋሮ እንድትጀምር አጥበቀው ይፈልጋሉ።

እሱ ብቻ አልበቃቸውም አሜሪካ ጨረቃም ሆነ ከፕላኔታችን መሬት ውጭ ያለ ሥፍራ ላይ ማዕድን እንድትቆፍር ሙሉ መብት የሚሰጣት ሙሉ ሥልጣን ያዘለ ወረቀት ላይ ፊርማቸውን አኑረዋል።

ወረቀቱ ላይ የሰፈረ አንድ አንቀፅ እንዲህ ይላል፡ «አሜሪካ በውጭው ዓለም [ከፕላኔታችን ምድር ውጭ ያለው መሆኑ ነው] ያለ ጥሬ ሃብት የጋር ነው ብላ አታስብም። ማዕድን ለማውጣትም ከዓለም አቀፉ ማሕበረሰብ ጋር ስምምነት መድረስ አይጠበቅባትም።»

ሰውዬው ጨረቃ ላይ ወጥተው ማዕድን ቁፋሮ ለመጀመር ለምን ፈለጉ? ብዙዎችን ሰቅዞ የያዘ ጥያቄ ሆኗል።

ሕይወትን ማራዘም

ሳራህ ክሩዳስ እንደሚሉት ጨረቃ ላይ ቁፋሮ መጀመር ሰዎች ወደ ሌሎች ፕላኔቶች ለመጓዝ ያላቸውን ተስፋ የሚያለመልም ነው - በተለይ ደግሞ ወደ ማርስ።

ሳራህ የሕዋ ጥናት ጋዜጠኛ ናቸው። ጨረቃ ትንሽ ቆይቶ ሰዎች ነዳጅ የሚቀዱባት መሆኗ አይቀርም ሲሉ ይተንብያሉ። ነዳጅ ሲባል የመኪና ወይ የባጃጅ አይደለም፤ ለሮኬት ማስወንጨፊያ የሚረዳ እንጂ።

ጨረቃ ሃይድሮጅንና ኦክስጅን የሞላባት ሥፋራ ናት። እኒህ ንጥረ ነገሮች ደግሞ ለሮኬት ግንባታ ትልቅ ግልጋሎት አላቸው። ሮኬቶች በቂ ነዳጅ አላቸው ማለት ደግሞ ወደ ሌሎች ፕላኔቶች ለመጓዝ አይገዳቸውም ማለት ነው።

ጨፈቃ ላይ ማዕድን ማውጣት

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ጨረቃ ከዚህም በላይ ሃብት አላት ይላሉ በዘርፉ ጥርስ ነቅለናል የሚሉ ባለሙያዎች ይናገራሉ።

ፕሮፌሰር ቤንጃሚን ሳቫኮ፤ በአየር ንብረት ለውጥ ሳቢያ ዓለም ወደ ታዳሽ ኃይል እያመራች ነውና የጨረቃ ጥሬ ሃብት ያስፈልገናል ባይ ናቸው። ሰሴክስ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ የኤነርጂ ፖሊሲ ፕሮፌሰሩ ቤንጃሚን ከጨረቃ ላይ በሚገኝ ሃብት በፀሐይ ኃይል የሚሠሩ መኪናዎችን ማምረት ይቻላል ይላሉ።

«ለምሳሌ ሊቲየም ወይም ኮባልትን እንውሰድ። እኒህን ማዕድናት የምታገኙት ቻይና፣ ሩስያ ወይም ኮንጎ ነው። በብዛት ማግኘት ደግሞ እግጅ አዳጋች ነው።»

ቢሆንም ይላሉ ፕሮፌሰሩ . . . ቢሆንም ከጨረቃ ላይ የሚገኘው ጥሬ ሃብት የዓለምን ችግር በአንድ ጊዜ ይቀርፋል ማለት አይደለም።

የአሜሪካ - ቻይና ውጥረት

ፕሬዝደንት ትራምፕ ጨረቃን ካልቆፈርን ያሉት ምናልባት ሃገራቸው እንደ ቻይና ካሉ ጋር ስትነፃፀር ያላት ጥሬ ሃብት አነስ ያለ ስለሆነ ይሆናል የሚሉ መላ ምቶች አሉ።

ቻይና የምታወጣቸውን ማዕድናት በየክፍለ ዓለማቱ ትቸበችባለች። ሩስያም ብትሆን አሜሪካን ጥላት ሄዳለች። ትራምፕ ቻይና ያልደረሰችበትን ሥፋራ ለመድረስ የሚጣጣሩት ለዚህ ይሆናል።

ትራምፕ በትረ ሥልጣኑን ከጨበጡ ወዲህ ከቻይና ጋር ዓይንና ናጫ ሆነዋል። ቀላል የማይባል ውጥረት ይስተዋላል።

ፕሮፌሰር ቤንጃሚን እንደሚሉት ትራምፕ ያላቸውን ጉልበት ማሳያው ጨረቃ ላይ ሄድ ማዕድን መቆፈር ነው።

ሕጉ ምን ይላል?

ትራምፕ ትዕዛዝ ያስተላለፉበት ወረቀት 'መሬታዊ ሕግ' አይገታንም ሲል በግልፅ አስቀምጧል። የሰው ልጅ ያወጣቸው ሕግጋት ከመሬት ውጭ ምን ያህል ተፈፃሚ ይሆናል የሚለውም ግልፅ አይደለም።

ሳራህ እንደሚሉት ማንም ሃገር ጨረቃ የኔ ናት አላለም። ነገር ግን ወደ ጨረቃ ተጉዘ ማዕድን ያወጣ የኔ ነው የማለት መብት እንዳለው ይታሰባል።

ባለሙያዎች የሰው ልጅ ምድርን እንዳልሆነች አድርጓታል። አሁን የቀረው ከመሬት ውጭ ያለው ነው ይላሉ።

በእኛ ዕድሜ የሚሆን ይሆን?

እንደ ሳራህ ከሆነ 'ቴክኖሎጂው አለ'። አልፎም የግል ድርጅቶች መሣተፍ ስለመጀመሩ ካሰብነው በላይ በፍጥነት ሊከናወን ይችላል።

«በፊት በፊት መንግሥታት ብቻ ነበሩ ይህን ማድረግ የሚችሉት። አሁን ግን የግል ኩባንያዎችና ግለሰቦች ፍላጎት ማሳየት መጀመራቸው የተሻለ ቴክኖሎጂና የገንዘብ አቅም እንዲኖር ያደርጋል።»

«ጨረቃና ውቅያኖስ ላይ የሚደረግ ማዕድን ቁፋሮ፣ እንዲሁም ማርስን መጎብኘት በእኛ ሕይወት ዘመን የምናያቸው ናቸው» የሚል እምነት አላቸው ጋዜጠኛዋ።