ቱርክ አውሮፕላኔን ተኩሳ ጣለችብኝ ስትል አርሜኒያ ከሰሰች

የአዘርባጃን ወታደሮች

የፎቶው ባለመብት, EPA

አርሜኒያና አዘርባጃን ወደለየለት ጦርነት እየገቡ ይመስላሉ። ወደ ግጭት ከገቡ ዛሬ አራተኛ ቀናቸውን ይዘዋል።

አርሜኒያ ከሰዓታት በፊት በሰጠችው መግለጫ ተዋጊ አውሮፕላኔን ቱርክ ተኩሳ ጥላብኛለች ብላለች። ቱርክ በዚህ ጦርነት ውስጥ ያለማወላወል ለአዘርባጃን ድጋፍ እየሰጠች ይገኛል።

አርሜኒያና አዘርባጃን ወደ ግጭት የገቡት ናጎርኖ-ካራባ በተባለ ክልል የይገባኛል ጥያቄ ምክንያት ነው።

አርሜኒያ ሶቪየት ሰራሹ SU-25 ተዋጊ አውሮፕላኗ ውስጥ የነበረው አብራሪ በዚህ ጥቃት እንደተገደለባት አምናለች።

ቱርክ በበኩሏ ይህ ሐሰት ነው ብላለች።

ግጭቱ እንደ አዲስ ከተቀሰቀሰ ጀምሮ ባለፉት ሦስት ቀናት ብቻ ከመቶ ሰዎች በላይ ተገድለዋል።

ይህ ናጎርኖ-ካራባ የተሰኘው ክልል የአዘርባጃን እንደሆነ ነው የዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ የሚያውቀው። የተባበሩት መንግሥታትም ይህንኑ ያረጋግጣል። ሆኖም አካባቢውን የሚገዙት በብሔር አርሜኒያዊያን የሆኑት ናቸው።

ሁለቱ የቀድሞ ሶቭየት ኅብረት አገራት እንደ አውሮጳዊያኑ ከ1988 ጀምሮ ለ6 ዓመታት ጦርነት አድርገዋል። በዚህ ጦርነት 30ሺ ሰዎች ተገድለዋል። አንድ ሚሊዮን ሰዎች ተፈናቅለዋል።

አሁን ጦርነቱ ከሁለቱ አገራት ባሻገር እንዳይሄድ ስጋት አለ።

ቱርክ አዘርባጃንን በግልጽ እየደገፈች ሲሆን ሩሲያ በአርሜኒያ የጦር ሰፈር አላት። ሆኖም ግን ከአዘርባጃን ጋር ወዳጅ አገር ናት። ለዚህም ይሆናል በጦርነቱ በቀጥታ ከመሳተፍ ይልቅ ሩሲያ አገራቱ የጦር አቁም ስምምነት እንዲያደርጉ እየሞከረች ያለችው።

ናጎርኖ ካራባህ ምንድነው?

ይህ ስፍራ ተራራማ ክልል ነው። ስፋቱ 4ሺህ 400 ስኳየር ኪሎ ሜትር ነው። በአመዛኙ ክርስቲያን አርመኖችና ሙስሊም የቱርክ ዘርያ ያላቸው ሰዎች ይኖሩበታል።

በሶቭየት ኅብረት ጊዜ የአዘርባጃን ግዛት ሆኖ ነገር ግን ራስ ገዝ አስተዳደር ነበር። በዓለም ማኅበረሰብ ዘንድ የአዘርባጃን ግዛት እንደሆነ ቢታወቅም ነዋሪዎቹ ግን የአርመን ዝርያ ያላቸው ዜጎች ናቸው። የራስ ገዝ አስተዳደሩ በተባበሩት መንግሥታት ብቻም ሳይሆን በአርሜኒያም እውቅና የተሰጠው አይደለም።

አሁን ፈረንሳይ፣ አሜሪካና ሩሲያ የተኩስ አቁም እንዲካሄድ እየወተወቱ ይገኛሉ።