ኮንጎ፡ የነፃነት ታጋዩ ፓትሪስ ሉሙምባ ጥርስ ለቤተሰቦቹ እንዲሰጥ ተወሰነ

ፓትሪስ ሉሙምባ ከትግል አጋሮቹ ጋር

የፎቶው ባለመብት, AFP

የኮንጎ የነጻነት አባት ፓትሪስ ሉሙምባ ጥርስ ለቤተሰቦቹ እንዲሰጥ የቤልጂየም ፍርድ ቤት ወሰነ።

ውሳኔውን የፓትሪስ ሉሙምባ የወንድም ልጅ ዤን ዣኪዌስ ሉሙምባ "መልካም እርምጃ ነው" በማለት ተቀብለውታል።

" ሉሙምባ አልቅሰን ያልቀበርነው ጀግና ነው፤ ውሳኔው [በቤልጂየም ፍርድ ቤት የተሰጠው] እውነታውን ለማወቅ ጥሩ ጅምር ነው. . . እዚያ የምንደርስበት መንገድ ይኖራል" ብሏል ዤን ዣኪዌስ።

ዤን እንደሚለው ከሆነ ከፓትሪስ ሉሙምባ ጋር አብረው የተገደሉ ሁለት ሰዎች፣ ጆሴፍ ኦኪቶ እና ማውሪስ ምፖሎ " እነርሱም የኮንጎ ጀግኖች ናቸው" በማለት ግለሰቦቹ እንዴት እንደተሰዉ እውነታው ግልጽ መሆንና መነገር አለበት ሲል ተናግሯል።

የቤልጂየም ፍርድ ቤት ከፓትሪስ ሉሙምባ አስከሬን ላይ የተወሰደው ጥርስ ለልጃቸው ጁሊያና እንዲመለስ ወስኗል።

ልጃቸው ጁሊያና ለቤልጂየም ንጉሥ ጥርሱ እንዲሰጣት የሚጠይቅ ደብዳቤ ጽፋ ነበር።

ኮንጎ ከቤልጂየም ነፃነቷን እኤአ በ1960 ካገኘች በኋላ የመጀመሪያው ጠቅላይ ሚኒስትር የነበሩት ሉሙምባ በ1961 በተገንጣይ አማፂያን ታግተው ተገድለዋል።

የቤልጂየም መንግሥት በግድያው ላይ እጁ እንደነበረበት ገልፆ በ2002 በይፋ ይቅርታ ጠይቋል።

በግድያው የእንግሊዝ እና የአሜሪካ የስለላ ተቋማት መሳተፋቸው ይታመናል።

የሉሙምባ ጥርስ በቤልጂየም ፖሊስ መወሰዱ ይታመናል ሲል የፈረንሳዩ የዜና ወኪል የዘገበ ሲሆን አክሎም፣ በኋላም በቤልጂየም ባለስልጣናት በቁጥጥር ስር ውሏል ብሏል።