በኢትዮጵያ በኮሮናቫይረስ የተያዙ ተጨማሪ ሦስት ሰዎች ተገኙ

የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ሚንስትር ዶ/ር ሊያ ታደሰ

የፎቶው ባለመብት, EBC

የምስሉ መግለጫ, በኢትዮጵያ በኮሮናቫይረስ የተያዙ ሰዎች በሦስት ጨምሮ ዘጠኝ መድረሱን የጤና ጥበቃ ሜኒስቴርና የኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲቲዩት አስታውቀዋል

በኢትዮጵያ በኮሮናቫይረስ የተያዙ ሰዎች ቁጥር በሦስት ጨምሮ ዘጠኝ መድረሱን የጤና ጥበቃ ሜኒስቴርና የኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲቲዩት አስታወቁ።

በአገሪቱ ውስጥ በቫይረሱ መያዙ የተረጋገጠው የመጀመሪያ ግለሰብ የዛሬ ሳምንት መጋቢት 04/2012 ዓ.ም ይፋ ከተደረገ በኋላ በሽታው የተገኘባቸው ሰዎች ቁጥር አሁን ዘጠኝ ደርሷል።

በሽታው ከተገኘባቸው ከአዲሶቹ ሦስት ሰዎች መካከል አንደኛው የ44 ዓመት ዕድሜ ያላቸው ጃፓናዊ፣ ሌላው የ39 ዓመት ኦስትሪያዊ፣ እንዲሁም ሦስተኛዋ የ85 ዓመት ዕድሜ ባለጸጋ ኢትዮጵያዊት መሆናቸው ተገልጿል።

አዲስ በበሽታው መያዛቸው ከተረጋገጡት ሦስት ሰዎች ውስጥ ጃፓናዊው ግለሰብ በኢትዮጵያ ውስጥ መጀመሪያ በበሽታው መያዛቸው ከተረጋገጠው ጃፓናዊ ጋር ንክኪ የነበራቸው ሲኾኑ፣ የ85 ዓመቷ ኢትዮጵያዊት ደግሞ ከሁለት ሳምንት በፊት ከውጪ ሀገር ወደ ኢትዮጵያ የገቡ ናቸው።

ዘጠነኛው በበሽታው መያዙ የተረጋገጠው ግለሰብ ደግሞ ኦስትሪያዊ ዜግነት ያለው ሲሆን ከቀናት በፊት ከስዊትዘርላንድ ወደ አዲስ አበባ መምጣቱ ተገልጿል።

ግለሰቡ እራሱን ለይቶ ካቆየ በኋላ የበሽታው ምልክቶች ስለታየበት ወደ ለይቶ ማቆያ እንዲገባ መደረጉንና በተደረገለት ምርመራ ቫይረሱ ሊገኝበት መቻሉ ተገልጿል።

እስካሁን በሽታው እንዳለባቸው ከተረጋገጡት ሰዎች አራቱ ጃፓናዊያን፣ ሶስቱ ኢትዮጵያዊያን፣ አንዷ እንግሊዛዊት እና አንዱ ኦስትሪያዊ ናቸው።

የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር እንዳመለከተው ቀደም ሲል በበሽታው መያዛቸው ተረጋግጦ በህክምና ላይ ከሚገኙት ስድስት ሰዎች መካከል አራቱ ከበሽታው ማገገማቸውን ሁለቱ ድግሞ እያገገሙ እንደሆነ አመልክቷል።

በዓለም አቀፍ ደረጃ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር 250,000 የደረሰ ሲሆን የሞቱት ደግሞ 9,900 መሆናቸው ተነግሯል።

ኢትዮጵያ የቫይረሱን ወረርሽኝ ለመከላከል ትምህርት ቤቶችን ለሁለት ሳምንታት መዝጋቷና ህዝባዊ ስብሰባዎችን መከልከሏ ይታወሳል።

ኮሮና