ከጠፋ በርካታ ዓመታት የሆናቸው 54 ህንዳውያን ወታደሮች ጉዳይ አሁንም አነጋጋሪ ነው

የጠፉት 54 ህንዳዊያን ወታደሮች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ሕንድ የጠፏት 54 ወታደሮች ሚስጥር አልፈታት ብሏታል።

እነዚህ ሕንዳዊያን ወታደሮች የጠፉት ከበርካታ ዓመታት በፊት ሕንድ ከፓኪስታን ጋር በነበራት ጦርነት ወቅት ነው። በነዚህ ዓመታት ወታደሮች የት እንደገቡ መንግሥትም ቤተሰብም በየፊናው ፈልጓቸዋል። ውጤቱ ግን ተመሳሳይ ነው፤ የት እንዳሉ አይታወቅም።

በርካቶች እንደሚስማሙት ምናልባትም ህንድ ከፓኪስታን ጋር በነበራት ጦርነት የጠላቷ መጥመድ ውስጥ ሳይገቡ እንዳልቀሩ የሚነገርላቸው እነዚህ ወታደሮች በተለምዶ "የጠፉት 54ቱ ወታደሮች" የት እንደገቡ ማወቅ ህንድ ውስጥ የማይፈታ ሚስጥር ሆኖ ቆይቷል።

ህንድና ፓኪስታን በ1947/48 እና በ1965 (እ.አ.አ) ሁለት ጊዜ ጦርነት ውስጥ ገብተዋል። በ1971 ደግሞ በ13 ቀናት ጦርነት በፓኪስታን ምስራቃዊ ክፍል የነበሩትን ተገንጣዮች ሕንድ በመደገፍ አዲስ የዓለም አገር ከፓኪስታን ተገንጥላ እንድትተዋወቅ አድርጋለች፤ ባንግላዲሽ።

ሕንድ እነዚህ 54 ወታደሮቿ ታዲያ በሁለተኛው የጦርነት ወቅት (1965) በፓኪስታን ተማርከው እስር ቤት ውስጥ እንዳሉ ታምናለች። ነገር ግን ከ40 ዓመታት በላይ የት እንዳሉ የሚያመላክት መረጃ ሊገኝ አልቻለም።

የጠፉት 54 ህንዳዊያን ወታደሮች

የፎቶው ባለመብት, AFP

ባለፈው ሐምሌ ወር ላይ የናሬንድራ ሞዲ መንግሥት ፓኪስታን ውስጥ የጠፉትን 54 ወታደሮች ጨምሮ በድምሩ 83 ወታደሮች ታግተው እንደሚገኙ ተናግሯል።

ቻንድራ ሱታ ዶግራ የተባለች ታዋቂ የህንድ ጋዜጠኛ በርካታ ሰነዶችን በማፈላለግ የጠፉትን ወታደሮች በተመለከተ መገኛቸው የት እንደሆነ ለማወቅ ምርምር ስታደርግ ቆይታለች። በርካታ ሰነዶችን አገላብጣም ይህንን የሚያትት ዳጎስ ያለ መጽሃፍም አሳትማለች። ጋዜጠኛዋ ያሳተመችው የምርምር መጽሐፍ የነዚህን ወታደሮች ሚስጥር ይፈታል ተብሎ ተስፋ ተጥሎበታል።

ጋዜጠኛዋ በምርምሯ 15ቱ መሞታቸውን ትገልጻለች። "ለምን መንግሥት ማመን እንዳልፈለገ ባይገባኝም በህይወት አሉ ከሚላቸው 54 የጠፉ ወታደሮች መካከል 15ቱ ስለመሞታቸው የህንድ መንግሥት መረጃ አለው" ብላለች ቻንድራ።

የጠፉት 54 ህንዳዊያን ወታደሮች ቤተሰብ

የፎቶው ባለመብት, AFP

ይህም ሆኖ ግን አወዛጋቢ ነገሮች ብዙ ናቸው። ለአብነት በ1965 ጦርነቱ ተጠናቆ፤ በዓመቱ የአንደኛውን ቤተሰቦች ወታደሩ ልጃቸው መሰዋቱን መንግሥት አርድቷቸዋል። በ1974 ግን ከ8 አመት በኋላ ማለት ነው በፓኪስታን ታስረው የነበሩ ወታደሮች ሲመለሱ ሞቷል የተባለው ወታደር ፓኪስታን ውስጥ በህይወት መኖሩን የመሰከሩት። እንደዚያም ሆኖ ግን ከዚያ በኋላ የተፈጠረ ነገር የለም።

በ1971 ሁለቱ አገራት ጦርነቱን ሲያጠናቅቁ ህንድ 93 ሺህ ወታደሮችን ስትልክ ፓኪስታን ደግሞ 600 ምርኮዎችን ብቻ ለህንድ አስረክባለች። ከዚያ በኋላ ባሉት በርካታ ዓመታት የሚመጡ የህንድ ጠቅላይ ሚንስትሮች ከፓኪስታን ጋር ድርድር አድርገዋል። ድርድሩ ግን እነዚህ የት እንዳሉ የማይታወቁ ወታደሮችን ከቤተሰቦቻቸው ጋር ሊያገናኝ አልቻለም።

በ1983 እና በ2007 የጠፉ ወታደር ቤተሰቦች ፎቷቸውን ይዘው ፓኪስታን ውስጥ ሂደው እስር ቤቶቹን ሁሉ ቢያስሱም 'አየሁ' የሚል አላገኙም። ነገር ግን በ2007 በነበረው ፍለጋቸው የጠፉት ወታደሮች በህይወት መኖራቸውን የሚያረጋግጥ ፍንጭ ቢያገኙም የፓኪስታን የአገር ውስጥ ሚንስቴር ማረጋገጫ ባለመስጠቱ ፍለጋው ከሽፏል።

የጠፉት 54 ህንዳዊያን ወታደሮች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ፍለጋው በየጊዜው ተስፋን እያበራና እያጨለመ ላለፉት አርባ ዓመታት ቀጥሏል። በቅርቡ የወጣው የቻንድራ መጽሐፍ ደግሞ 15 ወታደሮች መሞታቸውን በማርዳት የተስፋውን ጭላንጭል አደብዝዞታል።

ይህም ሆኖ ግን መጽሃፉ ቢያንስ ቀሪዎቹ በሕይወት ስለመኖራቸው ፍንጭ ስለሚሰጥ የተረፉትን በህይወት ለማግኘት ቤተሰቦች ድጋሜ ሌላ ተስፋ እየሰነቁ ነው። እንቆቅልሹ መቼ ይፈታ ይሆን? ይህ ጥያቄ ባለፉት ከአርባ በላይ ዓመታት ያልተፈታ ምናልባትም በቅርቡ የማይፈታ ነው።