ህንድ፡ የአስገድዶ መደፈር ጉዳዩዋን ለመከታተል ፍርድ ቤት የሄደችው ወጣት በእሳት ተቃጠለች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የአስገድዶ መደፈር ጥቃት እንደደረሰባት ገልጻ ጉዳይዋን በፍርድ ቤት ስትከታተል የነበረችው የ23 ዓመቷ ህንዳዊት ወጣት በመንገድ ላይ በእሳት መቃጠሏ ተሰምቷል።
በሰሜናዊ ህንድ ኡታር ፕራዴሽ በምትባለው ግዛት ውስጥ የምትኖረው ወጣት ባለፈው መጋቢት ወር ነበር ሁለት ወንዶች አስገድዶ የመድፈር ጥቃት አድርሰውብኛ ብላ ክስ የመሰረተችው።
ጉዳይዋን ለመከታተል ወደ ፍርድ ቤት በመሄድ ላይ እያለች ጥቃት ፈጻሚዎች በእሳት እንድትቃጠል በማድረግ ወጣቷ ላይ ከፍተኛ ጉዳት ደርሶባት በሞትና በህይወት መካከል እንደምትገኝ ተገልጿል።
ፖሊስም ከጥቃቱ በኋላ ወጣቷን መንገድ ላይ ጠብቀው በእሳት አቃጥለዋል ተብለው የተጠረጠሩ አምስት ግልሰቦችን በቁጥጥር ስር ማዋሉን የገለጸ ሲሆን፤ ከተጠርጣሪዎቹ መካከል አንደኛው በአስገድዶ መድፈር ክስ የቀረበበት ግለሰብ ነው ብሏል።
የአካባቢው መገናኛ ብዙሃ እንደዘገቡት ወጣቷ ወደ ፍርድ ቤት ለመሄድ ባቡር ልትሳፈር ስትል ነው ተጠርጠሪዎቹ እየገተቱ ወደ አንድ የሰብል ማሳ ወስደው በእሳት ያቃጠሏት።
ይህ አሳዛኝ ዜና ሲሰማ ብዙ ህንዳውያን ቁጣቸውን የገለጹ ሲሆን ባለፈውም ሳምንት በተመሳሳይ በደቡባ ህንድ የምትኖር አንዲት የ27 ዓመት ወጣት ተገዳ ከተደፈረች በኋላ በእሳት መቃጠሏም ተነግሯል።
በህንድ በፈረንጆቹ 2012 አንዲት ሴት የህዝብ ማመላለሻ ውስጥ ተገደድዳ ከተደፈረች በኋላ አስገድዶ መድፈርና ሴቶች ላይ የሚፈጸም ጥቃት ከፍተኛ ትኩረት እያገኙ ቢመጡም ወንጀሎቹ ግን እየቀነሱ አልመጡም።
በመንግሥት የወንጀል መረጃ መሰረት እ.አ.አ. በ2017 ህንድ ውስጥ ፖሊስ 33 ሺህ 658 የአስገድዶ መድፈር ክሶችን ተቀብሏል፤ ይህ ደግሞ በእያንዳንዱ ቀን 92 ሴቶች ተገደው ይደፈራሉ ማለት ነው።












