ህንድ ውስጥ 14 ሰዎች በሃይማኖታዊ ሥርዓት ላይ ሳሉ ድንኳን ወድቆባቸው ሞቱ

የድንኳኑ ፍርስራሽ

የፎቶው ባለመብት, AFP

ትናንት እሁድ በህንዷ ራጅስታን ግዛት ውስጥ ከባድ ዝናብና ንፋስ አንድ ግዙፍ የድንኳን መጠለያን በማፍረሱ ቢያንስ 14 ሰዎች ሲሞቱ ከ50 የሚበልጡት ደግሞ ቆስለዋል።

ሮይተርስ እንደዘገበው ከሞቱት መካከል አንዳንዶቹ ድንኳኑ ሲወድቅ በጥሶ በጣላቸው የኤሌክትሪክ ገመዶች ምክንያት በኤሌክትሪክ ተይዘው ሲሆን ሌሎቹ ደግሞ ድንኳኑ ወድቆባቸው ነው የሞቱት።

የሃገሪቱ አንድ ጋዜጣ እንደዘገበው 300 የሚሆኑ ሰዎች ለሃይማኖታዊ ሥነ ሥርዓት በድንኳኑ ውስጥ ተሰብስበው ነበር።

አደጋው የደረሰው ራጅስታን በምትባለው የህንድ ግዛት ውስጥ በምትገኝ ባርመር በተባለች አካባቢ ውስጥ ነው።

የግዛቲቱ የአደጋ መቆጣጠርና እርዳታ ሚኒስትር ብሃንዋር ላል ሚግዋል የአየሩ ሁኔታ ዝናባማ መሆኑ ሲታወቅ የኤሌክትሪክ ኃይል ለምን እንዲቋረጥ እንደልተደረገ የሥነ ሥርዓቱ አዘጋጆችን ጠይቀዋል።

የህንድ ጠቅላይ ሚኒስትር ናሬንድራ ሞዲ በትዊተር ባስተላለፉት መልዕክት አደጋው መጥፎ አጋጣሚ መሆኑን አስፍረው ሃዘናቸውን ገልጸዋል።

ስለተፈጠረው አደጋ ዝርዝር ለማወቅ ምርመራ እየተደረገ ነው።