ከፕሬዘዳንቱ ጋር 'ፊት በመለዋወጥ' ተይዞ የነበረው ቀልደኛ ተለቀቀ

የፎቶው ባለመብት, Idris Sultan/ Twitter
ፎቶውን ከታንዛንያው ፕሬዘዳንት ጆን ማጉፉሊ ጋር በመለዋወጡ ተይዞ የነበረው ቀልደኛ (ኮሜድያን) ኢድሪስ ሱልጣን በዋስ ተለቀቀ።
ታንዛንያዊው ኮማኪ ዘና ብሎ ከተነሳው ፎቶ ላይ የፊት ገጽታውን ቆርጦ በመውሰድ፤ ፕሬዘዳንቱ ኮስተር ብለው የሚያሳይ ፎቶግራፍ ላይ አስቀምጦታል። የፕሬዘዳንቱን ፊት ቆርጦም በሱ ፎቶ ላይ በሚታየው ፊቱ ተክቶታል።
ኮሜድያኑ፤ እሱና ፕሬዘዳንቱ ፊት ተለዋውጠው የሚያሳየውን ፎቶ በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ማጋራቱን ተከትሎ ለምርመራ ወደ ፖሊስ ጣቢያ ተወስዶ ነበር።
የኢድሪስ ጠበቃ ኢሊያ ሪዮባ፤ በአገሪቱ የመረጃ ደህንነት ሕግ መሰረት እንደተያዘ ገልጸዋል። በሕጉ ሰዎችን ማስመሰል የተከለከለ ነው። ቀኝ ዘመም የመብት ተሟጋቾች ሕጉ የመናገር ነጻነትን ይገድባል ሲሉ ተችተዋል።
ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ከአምስት ሚሊዮን በላይ ተከታዮች ያሉት ኢድሪስ ፎቶውን ሲለቅ "ፕሬዘዳንቱ ልደታቸውን በሰላም እንዲያከብሩ ከእኔ ጋር ሚና ተለዋውጠዋል" ሲል በስዋሂሊ ጽፏል።
ይህ ጽሑፍ በX. የቀረበ ይዘት ይዟል። ገጹ ቴክኖሎጂዎች ወይም ኩኪዎች ሊኖረው ስለሚችል ገጹ ከመከፈቱ በፊት የእርስዎን ፍቃድ እንጠይቃለን። ፍቃድዎን ከመስጠትዎ በፊት የX ኩኪ ፖሊሲ እና የ ማንበብ ይፈልጉ ይሆናል። ይዘቱን ለማንበብ ‘እቀበላለሁ ቀጥል’ የሚለውን ይምረጡ።
የ X ይዘት መጨረሻ
ፎቶውን ከለጠፈ በኋላ የዳሬ ሰላም ፖሊስ ኮሚሽነር ፖል ማኮንዳ "ሥራው ምን ድረስ የተገደበ እንደሆነ አያውቅም" ብለዋል።
ፕሬዘዳንቱ 60ኛ ዓመት ልደታቸውን ያከበሩት ባለፈው ማክሰኞ ሲሆን፤ ቀልደኛው ለምርመራ ወደ ፖሊስ ጣቢያ ተወስዶ የነበረው እሮብ ነበር።












