ፈረንሳያዊው ደራሲ የአምሳ አመት ሴቶችን ለፍቅር ዕድሜያቸው "የገፋ' ነው ማለቱ ቁጣን ቀስቅሷል

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ፈረንሳያዊው ደራሲ አምሳ አመት ወይም ከዚያ በላይ ዕድሜ ያሉ ሴቶችን ለማፍቀር እንደሚከብደው መግለፁን ተከትሎ ከፍተኛ ትችቶችን እያስተናገደ ነው።
ራሱ የ50 አመት እድሜ ባለፀጋ መሆኑ ደግሞ አግራሞትን ፈጥሯል።
ክሌር ለተባለው መፅሄት በሰጠው ቃለ መጠይቅ በዚህ እድሜ ክልል ያሉ ሴቶች "አዛውንትና በዕድሜያቸው የገፉ ናቸው" ብሏል።
"በዕድሜያቸው አነስ ያሉ ሴቶችን እመርጣለሁ። የ25 አመት ሴት ሰውነት የሚያስደምም ሲሆን፤ በአንፃራዊው 50 አመት የሞላቸው ሴቶች ሰውነት አይደለም" ብሏል።
አስተያየቱም በማህበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚዎች ዘንድ ቁጣን ቀስቅሷል።
ማሪና ፎይስ የተባለች የፈረንሳይ ኮሜድያን በትዊተር ገጿ ላይ እንዳሰፈረችው አሁን ወደ 49ኛ አመቷ ልትሸጋጋር ስለሆነ ከደራሲው ጋር ግንኙነት ለመመስረት ያሉኝ "አንድ አመት ከአስራ ቀናት ነው" በማለት በፌዝ ሸንቆጥ አድርጋዋለች።
ሌላኛው የትዊተር ተጠቃሚ በበኩሉ ከአምሳ አመት በላይ እድሜ ያላቸው ሴቶች "በእፎይታ እየተነፈሱ" ነው በማለት አስተያቱን ችሮታል።
ሌላ አስተያየት ሰጪ በበኩሉ "ከአምሳ አመት በታች ያሉ ሴቶችስ የማይታዩህ ሁኔታ ሊፈጠር አይችልም" ወይ በማለት ቀልዷል።
ከዚህም በተጨማሪ ከአምሳ አመት እድሜ በላይ ያሉ ሴቶችም አስተያየቱን በመቃወም ፎቷቸውን አጋርተዋል።
ኮሎምቤ ሽኔክ የተባለች ጋዜጠኛ በበኩሏ በኋላ በሰረዘችው ፎቶ ላይ "የ52 አመት ሴት መቀመጫ ይህንን ይመስላል። ይህንን ነው ያጣኸው ነፈዝ" በማለት አስተያየቷን ሰጥታለች።
ሌሎች ደግሞ አምሳና ከአምሳ አመት በላይ የሆኑ የሆሊውድ ተዋንያን እነ ሀሊ ቤሪ፣ ጄኔፈር አኒስተንን ፎቶ በመለጠፍ የደራሲው አስተያየት ስህተት እንደሆነ ለማሳየት ሞክረዋል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
አን ሩማኖፍ የተባለች ሌላኛዋ ፈረንሳያዊ ኮሜዲያን አውሮፓ 1 በታባለ ሬድዮ ጣቢያ " ፍቅር በሁለት ሰዎች መካከል ያለ ጥልቅ ግንኙነት እንጂ ሰውነት ብቻ አይደለም። አንድ ቀን ይህንን እንደሚረዳው ተስፋ አደርጋለሁ" ብላለች።
ሞይክስ በፅሁፎቹ ሽልማትን ያሸነፈ ደራሲ ሲሆን በአስተያየቶቹ ውዝግብን በማስነሳት ይታወቃል።
በዛው መፅሄት ላይ ከእስያ የመጡ ሴቶችን በተለይም ከኮሪያ፣ ከቻይናና ከጃፓን እንደሚመርጥ መናገሩም ከፍተኛ ወቀሳን ፈጥሮበታል።
የተቀሰቀሰውንም ቁጣ ተከትሎ ስለሚመርጣቸው ሴቶች ኃላፊነት እንደማይወስድ ገልፆም " የምወደውን እወዳለሁ። በምርጫየ ላይ ሰዎች መግባት የለባቸውም" ያለ ሲሆን እሱም ይህን ያህል ቆንጆ የሚባል እንዳልሆነ በቀልድ መልኩ ጣል አድርጓል።
"የአምሳ አመት ሴቶች እኔን አያዩኝም። ቀኑን ሙሉ በመፃፍና በማንበብ ጊዜውን የሚያሳልፍ ያልተረጋጋ ሰው ምን ያደርግላቸዋል? ጊዜያቸውን በጠቃሚ ጉዳዮች የሚያሳልፉ ይመስለኛል። ከኔ ጋር መሆን ቀላል አይደለም" ብሏል።












