አሜሪካዊው ኮሜድያን ቢል ኮዝቢ በፆታዊ ትንኮሳ ውንጀላ ወደ ዘብጥያ ወረዱ

ቢል ኮዝቢ

የፎቶው ባለመብት, Gilbert Carrasquillo

በፔንሲይልቫኒያ የሚገኝ ዳኛ ታዋቂው አሜሪካዊውን ኮሜዲያን ቢል ኮዝቢን በተወነጀሉባቸው ወሲባዊ ትንኮሳዎች ከ3-10 ዓመት ፈርደውባቸዋል።

የ81 ዓመቱ የእድሜ ባለፀጋ ቢልኮዝቢ ከዚህም በተጨማሪ ወሲባዊ ተንኳሽ በሚል የተመዘገቡ ሲሆን እስከ ህይወታቸው መጨረሻም ድረስ ምክርን በመቀበል አገልግሎት እንዲያልፉም ተወስኖባቸዋል።

ተዋናዩ ምንም አይነት አስተያየት ከመስጠት ተቆጥበዋል።

በሚያዝያ ወርም በአውሮፓውያኑ 2004 አንድሪያ ኮንስታንድ የተባለች ሴትን ማደንዘዣ በመጠቀም ወሲባዊ ጥቃት በመፈፀም ፍርድ ቤቱ ጥፋተኛ ሆነው አግኝተዋቸዋል።

ቢል ኮዝቢ የዋስ መብት እንዲከበርላቸው ቢጠይቁም ውድቅ ተደርጎባቸዋል።

በአውሮፓውያኖቹ 1980 ከፍተኛ ዝናን ያተረፉት ተዋናዩ ኮዝቢ ሾው በሚለው የቲቪ ፕሮግራም አድናቆት ተችሯቸዋል።

በኒውዮርክ ብሩክሊን ኑሯቸውን ስላደረጉ አንድ የቤተሰብ ታሪክ የሚተርከው ይህ ፊልም ቢልኮዝቢም የአባት ገፀ-ባህርይን ወክለውም ይጫወታሉ።

በቲቪ ፕሮግራማቸውም ባገኙት ዝና "አሜሪካዊ አባት" የሚል ቅፅል ስምም አግኝተው ነበር።

"ይህ ከፍተኛ ወንጀል ነው" ያሉት ዳኛ ስቲቨል ኦኒል ፍርዱንም ካስተላለፉ በኋላም "ሁሉም ነገር ወደ አንተ ተመልሷል። ቀኑም ደረሰ፤ ጊዜውም አሁን ነው" ብለዋል።

በባለፈው አመት በቴምፕል ዩኒቨርስቲ አስተዳደር የምትሰራ አንዲት ሴት እንደ ታላቅ ሰው ታየው የነበረው ቢል ኮዝቢ ከጥቂት አመታት በፊት አደንዛዥ እንክብል ሰጥቶ ጥቃት ስለሰጣትም የደረሰባትን ወሲባዊ ትንኮሳን መከላከል አልቻለችም።

ለናሽናል ፖስት በሰጠችውም መግለጫ " የወሲባዊው ትንኮሳ ያደረሰብኝን ጉዳት ለማወቅ ምን አይነት ሰው እንደነበርኩ መረዳት ያስፈልጋል" ብላለች።

በህይወቷ ከፍተኛ ቦታን እደርሳለሁ ብላ አልማ የነበረ ሲሆን በትምህርቷም ሆነ በአትሌቲክስ ስልጠና ላቅ ወዳለ ደረጃ እደርሳለሁ ብላ አልማ ነበር።

ከወሲባዊው ትንኮሳ በኋላ ሁሉ ነገር ብዥ ብሎባት የነበረ ሲሆን እፍረቱ፣ ራሷን መጠራጠር፣ ብቸኝነቱ ውዝግብና ሌሎችም ቀውሶች እንደደረሱባት ትናገራለች።

መብላት አቁማ እንደነበር፣ እንዲሁም መተኛትና ከማህበረሰቡም ጋር መቀላቀል አቁማ ነበር።

"ቢል ኮዝቢ ውበቴን፣ ጤናየንና የወጣትነቴን መንፈሴን ወስዶ ሰባብሮታል" ብላለች።