"ሙሰኛ አይደለሁም" የቀድሞው የደቡብ አፍሪካ ፕሬዚዳንት ጃኮብ ዙማ ልጅ

የዙማ ልጅና ጃኮብ ዙማ

የፎቶው ባለመብት, Foto24

የቀድሞው የደቡብ አፍሪካ ፕሬዚዳንት ጃኮብ ዙማ ልጅ "ሙሰኛ አይደለሁም" እያለ ነው።

ዱዱዜን ዙማ ይህንን ያለው በአባቱና በሱ ጉዳይ ላይ የተወነጀሉበትን የሙስና ሂደቶችን እያጣራ ላለው ኮሚቴ ነው።

እንደ አባቱ ዙማ ዱዱዜንም የቀረበበትን የሙስና ጉዳዮች ውንጀላ ናቸው በማለት አጣጣጥሏል።

"እንደ ወንጀለኛ ነው እየታየሁ ያለሁት፤ የሙስና መመሰያ ሆኛለሁ። የሃገሪቷን ትሪሊዮን አንጡራ ሃብት እንደመዘበርኩ ተደርጎ ነው እየቀረበ ያለው፤ ይህ ግን ከእውነታ የራቀ ነው" ብሏል።

አክሎም " ለህዝቡ ማለት የምፈልገው እኔ ሙሰኛ አይደለሁም። ከማንም ገንዘብ ወስጄ አላውቅም የመውሰድም እቅዱ የለኝም" ብሏል።

በአባቱ የፖለቲካ ፍትጊያዎችም ተጠቂ እንደሆነ ገልጿል።

"ከዚህ ቀደምም ብየዋለሁ፤ አሁንም ደግሜ እናገረዋለሁ። በሚያሳዝን ሁኔታ በፖለቲካው ማዕበል ውስጥ ተይዣለሁ" ብሏል።

የሙስና ጉዳዩን እየመሩ ያሉት ዳኛ ሬይመንድ ዞንዶ በበኩላቸው የሚፈለገው እውነቱን ብቻ ነው ብለዋል።

"ሁሉንም ጉዳዮች እያየናቸው ነው፤ እያጣራንም ነው። በመረጃ ተመስርተን ነው የምንሄደው፤ የምንፈልገው እውነቱን ነው፤ ፤ሌላ የተደበቀ አላማ የለንም" ብለዋል።

አጣሪ ቡድኑ የቀድሞው ፕሬዚዳንት ጃኮብ ዙማ በስልጣን ላይ በነበሩበት ወቅት ፈፀሟቸው የተባሉ የሙስና ተግባራትን በመመርመር ላይ ነው።

ውንጀላዎቹ ጃኮብ ዙማ በስልጣን በነበሩበት ወቅት ከጉፕታ ቤተሰብ ጉቦ በመቀበል የመንግሥት ካቢኔዎች ላይ ተፅእኖ በመፍጠርና የመንግሥት ጨረታዎችን ያለአግባብ ሰጥተዋል የሚለው አንዱ ነው።

የቀድሞው ፕሬዚዳንትም ይሁን የጉፕታ ቤተሰብ በጭራሽ በማለት ክደዋል።