የአሜሪካዋ ሴናተር በስልጣን ላይ ሆነው ልጅ በመውለድ የመጀመሪያዋ ሆኑ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የአሜሪካዋ ሴናተር ታሚ ደክወርዝ በስልጣን ላይ ሆነው ሴት ልጅ በመውለድ የመጀመሪያዋ ሴናተር ሆነዋል።
የዲሞክራት ፓርቲ አባል ሜይል ፐርል ቦውልስቤይ በትዊተር ገፁ እንዳሰፈረው ጨቅላዋም በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ነርስ ሆና ባገለገለችው የታላቅ አክስቷ ስም እንደተሰየመች ነው።
ሴናተሯም በትዊተር ገፃቸው ቤተሰባቸውን እንዲሁም የህክምና ቡድኑን አመስግነዋል።
ሜይል የተባለችው ሁለተኛዋ ሴት ልጃቸው በዋሽንግተን ዲሲ ሆስፒታል ሰኞ ተወልዳለች።
ደክወርዝ የቀድሞ አየር ኃይል ፓይለት ሆነው ያገለገሉ ሲሆን በአውሮፓውያኑም 2004 ኢራቅ ውስጥ በደረሰ ግጭት ሁለት እግሯቻቸው ተቆርጠዋል።
ሴት የአካል ጉዳተኛ ሆነው ሴናተርም በመሆንም ከዚህ ቀደም ታሪክ ሰርተዋል።
ከዚህ ቀደም በፌዴራል ቢሮ ተመርጠው የልጅ እናት ከሆኑት መካከል ደክወርዝን 10ኛዋ ሴት እንደሚያደርጋቸው የአሜሪካ ሚዲያ ዘግቧል።
"ወላጅነት የሴቶች ጉዳይ ብቻ አይደለም። ሴት ሆነ ወንድ ወላጆችን የሚያሳትፍ ኢኮኖሚያዊ ጉዳይ ነው" በማለት በመግለጫቸው አብራርተዋል።
"እናትነትና ሴናተርነት የሚያስፈልገውን የስራ ጫና እሸከማለሁ። እንደሚሰራ እናት የኔ ጉዳይ የመጀመሪያ አይደለም፤ የተለየሁ አይደለሁም። ልጆቼም ስራየን ጠንክሬ እንድሰራና በዓለም ላይ ላሉ ጠንክረው ለሚሰሩ ቤተሰቦችም እንድቆም ያደርጉኛል" ብለዋል።
በባለፈው ወር የሁለቱም ፓርቲ ሴናተሮች ልጃቸውን ለመቀበል ዝግጅት አድርገው እንደነበር የቺካጎው ሰን ታይምስ ጋዜጣ ዘግቧል።

የፎቶው ባለመብት, Reuters
በጥር ወር ላይ ደክወርዝ ለሚዲያ እንደተናገሩት የሁለተኛ ልጃቸው እርግዝና ፈታኝ እንደነበረም ተናግረዋል።
ከታይላንዳዊ እናት የተወለዱት ደክወርዝ በኮንግረስም ለመመረጥ የመጀመሪያዋ እስያዊ ዝርያ ያላቸው አሜሪካዊ ናቸው።
በዚህ ዓመት ደክወርዝ አዳዲስ እናቶችን የሚጠቅም አዳዲስ ህጎችን ረቂቅ ያቀረቡ ሲሆን ከነዚህም አየር ማረፊያዎች ለሴቶች ጡት ማጥቢያ እንዲሁም ማለቢያ ቦታዎችን ማመቻቸት የሚለው ይገኝበታል።
ከዚህም በተጨማሪ በወታደርነት ዘርፍ እያገለገሉ ያሉ ባለሙያዎች በጉዲፈቻ ካመጧቸው ልጆች የመተዋወቂያ ጊዜ እንዲያገኙ እንዲሁም በዩኒቨርሲቲ ካምፓሶች ውስጥ የልጆች መንከባከቢያ አገልግሎት አቅርቦት እንዲኖር ፖሊሲዎች እንዲሻሻሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።












