ሊቨርፑል ከሪያል ማድሪድ በነበረው ጨዋታ የተፈጠሩ ክስተቶች እንዲመረመሩ ጠየቀ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ሊቨርፑል ከሪያል ማድሪድ ጋር ያደረጉትን የቻምፒየንስ ሊግ የፍፃሜ ጨዋታን እንዲዘገይ ያደረገውና ደጋፊዎች ያጋጠሟቸው "ተቀባይነት የሌላቸው ጉዳዮች" ላይ ምርመራ እንዲደረግ ጠየቀ።
የአውሮፓ እግር ኳስ ማኅበራት ኅብረት የደህንንት ምክንያቶችን ጠቅሶ ጨዋታውን እንዲዘገይ ያደረገው ሲሆን በዚህም ጨዋታው ከ30 ደቂቃ በላይ መዘግየት አጋጥሞታል።
በፈረንሳይዋ መዲና ፓሪስ ስታድ ዴ ፍራንስ ስታዲየም የተደረገው የቻምፒዮንስ ሊግ የፍጻሜ ጨዋታ እስከ ምሽቱ አራት ተኩል ድረስ ያልተጀመረ ሲሆን በዚህ ጨዋታም ሪያል ማድሪድ ሊቨርፑልን 1 ለ0 ረትቷል።
ጥቂት ደጋፊዎችም በግንብ አጥሮች ላይ ለመውጣት ሲሞክሩ ፖሊሶች አስለቃሽ ጭስ ተኩሰዋል።
ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ደጋፊዎች በተጨናነቁ ሰልፎች ወደ ስታዲየሙ ለመግባት ሲሞክሩ የሚያሳዩ ምስሎችም መውጣት ጀምረዋል።
በርካቶች ጨዋታው ከመጀመሩ ከሰዓታት በፊት ወደ ስታዲየሙ እንደደረሱ ቢናገሩም ወደ ስታዲየሙ ግቢ እንዳይገቡ መከልከላቸውን ተናግረዋል።
"የሊቨርፑል ደጋፊዎች ወደ ስታድ ዴ ፍራንስ ስታዲየም ለመግባት ሲሞክሩ ባጋጠሟቸው ጉዳዮች እንዲሁም የጸጥታው ብልሽት በደጋፊዎቻችን ላይ የፈጠረው እክል በጣም አሳዝኖናል" ሲል የአንፊልድ ክለብ መግለጫ አውጥቷል።
"ይህ በአውሮፓ እግር ኳስ ታላቅ ውድድር ነው እና ደጋፊዎች ዛሬ ማምሻውን ያየናቸው ትዕይንቶች ሊያጋጥማቸው አይገባም። የእነዚህ ተቀባይነት የሌላቸው ጉዳዮች መንስኤዎች ላይ መደበኛ ምርመራ እንዲደረግ በይፋ ጠይቀናል" ብሏል።
የአውሮፓ እግር ኳስ አስተዳዳሪ አካል ዩኤፋ በበኩሉ "በእነዚህ በተፈጠሩት ክስተቶች ለተጎዱት እናዝናለን። የተፈጠሩትንም ጉዳዮች ከፈረንሳይ ፖሊስ እና ባለስልጣናት እንዲሁም ከፈረንሳይ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ጋር በጋራ እንመረምራለን" ብሏል።
ሆኖም ጨዋታው ከመጀመሩ በፊት በሊቨርፑል ደጋፊዎች መግቢያ በኩል ሃሰተኛ ትኬቶችን የያዙ በሺዎች የሚቆጠሩ ደጋፊዎች ለማለፍ ሲሞክሩ ቲኬቱ ባለመስራቱ መታገዳቸውንም ገልጿል።
በዚህም ወደ ስታዲየሙ ለመግባት የሚሞክሩ በርካታ ደጋፊዎች ላይ መጨናነቅ መፍጠሩንና እውነተኛ ቲኬት የያዙ ደጋፊዎች ወደ ስታዲየሙ እንዲገቡ ለማድረግ በነበረውም ሙከራ ጨዋታው በ35 ደቂቃ መዘግየቱን አስታውቋል።
ጨዋታው ከተጀመረም በኋላ ከስታዲየም ውጭ የነበሩ ደጋፊዎች ቁጥር መበራከቱ የቀጠለ ሲሆን ፖሊሶች አስለቃሽ ጭስ በመጠቀም ከስታዲየሙ እንዲርቁም አድርገዋቸዋል ብሏል።
የፈረንሳይ ፖሊስ በበኩሉ ሃሰተኛ ትኬቶችን የያዙ ደጋፊዎች በግድ ወደ ስታዲየሙ ለመግባት እንደሞከሩና "ፖሊስ በሰጠው ፈጣን ምላሽ ሁኔታው እንደተረጋጋ" ገልጿል።












