ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ ፍርድ ቤት ቀረበ

ተመስገን ደሳለኝ

የፎቶው ባለመብት, Tariku Desalegn facebook

ሐሙስ ዕለት በፀጥታ ኃይሎች በቁጥጥር ስር የዋለው ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ ሁከትና ብጥብጥ በማነሳሳት ተጠርጥሮ በዛሬው ዕለት ግንቦት 19/2014 ዓ.ም ፍርድ ቤት መቅረቡን ጠበቃው ሔኖክ አክሊሉ ለቢቢሲ ገለጹ።

በፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ የጊዜ ቀጠሮ ችሎት በዛሬው ውሎው ፖሊስ ጋዜጠኛ ተመስገንን ገንዘብ ተከፍሎት በተለያዩ ሚዲያዎች እየቀረበ ሁከትና ብጥብጥ በማነሳሳት መጠርጠሩን ተናግሯል።

በተለይም ጋዜጠኛው "የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት በሕዝቡ ዘንድ አመኔታ እንዲያጣ" አድርጓል የሚል ክስ ፖሊስ አቅርቦ ምርመራውን ለማጠናቀቅ 14 ቀናት እንዲፈቀድለት ፍርድ ቤቱን ጠይቋል።

ጠበቃ ሄኖክም በምላሹ ማንኛውም ወንጀለኛ ወይም ወንጀል ሰርቷል ተብሎ የተጠረጠረ ሰው በሚዳኝበት የሥነ ሥርዓት ሕግ መሰረት ደንበኛቸው ሊዳኝ እንደማይገባና ጉዳዩ አገሪቷ ጋዜጠኞችን በምትዳኝበት የመገናኛ ብዙኃን አዋጅ ወይም በሚዲያ አዋጅ መሰረት መታየት አለበት የሚል የመከራከሪያ ሃሳብ ማቅረባቸውን ተናግረዋል።

ተመስገን ጋዜጠኛ እንዲሁም በአገሪቱ ሕግ የተመሰረተ የሚዲያ ባለቤት እንደመሆኑ "በዘፈቀደ በየትኛውም ሕግ መዳኘት የለበትም" ሲሉም ለፍርድ ቤቱ ማስረዳታቸውን አስረድተዋል።

በተጨማሪም ጋዜጠኛ ተመስገን ከተጠረጠረበት ጉዳይ ጋር በተያያዘ ሊታሰር እንደማይገባ፣ "ፖሊስ ትዕዛዝ እየተቀበለ በሃሳብ የተለየን ጋዜጠኛ ወደ ፍርድ ቤት ማምጣቱ ተገቢነት የሌለው ነው ሲሉ" የሃሳብ ነፃነትና የሃሳብ ብዝሃነት በአንድ ሥርዓት ውስጥ ሊኖር የሚገባ ነው ሲሉ ለፍርድ ቤቱ መናገራቸውን ገልጸዋል።

ጋዜጠኛው ሃሳቡን በጽሁፉ መግለፁንና ይህ ጽሁፍም ሁከትና ብጥብጥ የሚያስነሳ አይደለም ከማለት በተጨማሪ፣ ጋዜጠኞ ተመስገን ከዚህ ቀደምም የሚታወቀው በሃሳብ ከመሞገት ባለፈ የሁከትና የአመፅን ጥሪ የሚያደርግ አይደለም ሲሉ የመከራከሪያ ሃሳብ አቅርበው ፍርድ ቤቱ በዋስ ይልቀቃቸው በሚልም ጠይቀዋል።

ፖሊስ ሊያከናውናቸው የሚገቡ የምርመራ ተግባራት የጋዜጠኛውን በእስር መቆየት አያስፈልግም ሲሉ ለፍርድ ቤቱ የዋስትና መብቱ እንዲከበር መጠያቃቸውን ገልጸዋል።

በተጨማሪ ከመከላከያ ሠራዊት ጋር በተገናኘ የተነሳበት ክስ፣ መከላከያ ጋዜጠኛ ተመስገንን ስሜን አጉድፏል ባላለበት ሁኔታ "ፖሊስ ሰበብ በመፈለግ ሊያስረው ካልሆነ" ተገቢ አይደለም ብለዋል።

በሚዲያው አሰራር መስረት ቅሬታ ያለባቸው ተቋማት ለሚዲያዎች በደብዳቤ ተገልጾ ተቋሙ ይቅርታና ማስተባበያ እንደሚያወጣ የሚሰራበት ሕጋዊ አሰራር አንዳለና በተጨማሪም መከላከያ ሠራዊትም ቢሆን ችግሮች ካሉበት በሃሳብ እንደሚሞገት ጠበቃው ለፍርድ ቤቱ ተናግረዋል።

የጋዜጠኛ ተመስገን የዋስትና ጥያቄ እንዲሁም በየትኛው ከጋዜጠኝነቱ ጋር ተያይዘው በተነሱ ክርክሮች ላይ ፍርድ ቤቱ ብይን መስጠት ያስፈልገኛል ሲል ለሰኞ ለግንቦት 22/2014 ዓ.ም. ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል።

የፍትህ መጽሔት ማኔጂንግ ዳይሬክተር የሆነው ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ ግንቦት 18/2014 ዓ.ም. ከሥራ ቦታው በሁለት መኪና ተጭነው በመጡ የፀጥታ ኃይሎች ተይዞ ወደ አዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን መወሰዱ ይታወሳል።

የጋዜጠኛው ቤት እንዲሁም ቢሮው በፖሊስ የተፈተሸ ሲሆን፣ በተለያየ ጊዜ የታተሙ የፍትህ መጽሔቶች፣ ሃርድ ዲስኮችና ሌሎች ፖሊስ ለምርመራ ያስፈልገኛል የሚላቸውን ሰነዶች መውሰዳቸውን ጠበቃ ሄኖክ አስረድተዋል።

ከቀናት በፊት ተመስገን በፀጥታ ኃይሎች ተይዟል የሚል መረጃ መሰራጨቱን ተከትሎ ቢቢሲ ለጋዜጠኛው ጥያቄ አቅርቦ ነበር።

ጋዜጠኛው በቁጥጥር ስር እንደሚውል መረጃው እንዳለው ገልጾ ነበር።