በአማራ ክልል እየተካሄደ ያለው ዘመቻ "ሕግ ማስከበር" ወይስ "ፋኖን እና የመንግሥት ተቺዎችን ማሳደድ?"

ከሰሞኑ የአማራ ክልል መንግሥት እያካሄድኩት ነው ባለው ሕግ የማስከበር ዘመቻ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ታስረዋል።
ይህንንም ተከትሎ በክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች ግጭቶች ተከስተው የሰዎች ሕይወት መጥፋቱና የአካል ጉዳት መድረሱ ተገልጿል።
ቢቢሲ ያናገራቸውና ግጭት ተከስቶባቸው የነበሩ አካባቢዎች ነዋሪዎች እንደሚሉት ግጭቱ በክልሉ፣ በፌደራል የፀጥታ ኃይሎች በፋኖ አባላት መካከል ነው ይላሉ።
ሌሎች ነዋሪዎች ደግሞ መንግሥት በፋኖ ስም ይንቀሳቀሳሉ ያላቸውንና በሕገ ወጥ ተግባራት ላይ ተሰማርተዋል ያላቸውን ግለሰቦች በቁጥጥር ሥር ለማዋል በሚያደርገው ጥረት ከፀጥታ ኃይል ጋር ግጭት መፈጠሩን ተናግረዋል።
መንግሥት እያካሄድኩት ነው ባለው ዘመቻ በርካታ ሰዎች መታሰራቸውን ተከትሎ ከሳምንት በፊት በምሥራቅ ጎጃም ዞን፣ ሞጣ ከተማ በፀጥታ ኃይሎችና ለተቃውሞ በወጡ ወጣቶች መካከል በተፈጠረ ግጭት ቢያንስ ስድስት ሰዎች መገደላቸውንና ከ13 በላይ ሰዎች ጉዳት እንደደረሰባቸው ቢቢሲ ከአካባቢው ነዋሪዎችና ከሆስፒታል ባገኘው መረጃ መረዳት ችሏል።
ከባሕር ዳር በቅርብ ርቀት ላይ በምትገኘው መርዓዊ ከተማም እስሩን በመቃወም በተካሄደ ሰልፍ ላይ በተወሰደ እርምጃ ቢያንስ 12 ሰዎች መገደላቸውንና የቆሰሉ መኖራቸውን በአሜሪካ የአማራ ማኅበር በፌስቡክ ገጹ ባጋራው የቪዲዮ ላይ ገልጿል።
በሌላም በኩል በሰሜን ወሎ ዞን፣ ወልዲያ ከተማ በተፈጠረ ግጭት ቢያንስ አራት ሰዎች መገደላቸውንና የቆሰሉ መኖራቸውን ነዋሪዎች ለቢቢሲ ተናግረዋል።
በአሜሪካ የአማራ ማኅበር በበኩሉ በወልዲያ ሰባት ሰላማዊ ሰዎች ስለመገደላቸውና ከ10 በላይ ሰዎች ስለመቁሰላቸው መረጃው አለኝ ብሏል።
ነዋሪዎቹ እንዳሉት በከተማዋ ግጭቱ የተፈጠረው የከተማው ወጣቶች ታስረዋል ያሏቸውን "የፋኖ አመራሮች" ለማስፈታት ወደ ፖሊስ ጣቢያ ካመሩ በኋላ ነው።
በአዲስ አበባ እና በተለያዩ የአማራ ክልል አካባቢዎች መምህራንን ጨምሮ በርካታ ሰዎች ታስረዋል።
የአማራ ክልል የሰላምና ፀጥታ ቢሮ በክልሉ 4 ሺህ 552 ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን ግንቦት 15/ 2014 ዓ.ም በሰጠው መግለጫ አስታውቋል።
መንግሥት እያካሄድኩት ነው ባለው "የሕግ ማስከበር ዘመቻ" ተጠርጥረው ከተያዙት ውስጥ በነፍስ ማጥፋት ወንጀል የተከሰሱና በሕግ ጥላ ሥር ማድረግ ሳይቻል የቆዩ፣ ከማረሚያ ቤት ያመለጡ፣ ወንጀለኞች ሆነው በሌሉበት የተፈረደባቸው፣ በጽንፈኞችና የክልሉ ጠላቶች ተልዕኮ የተሰጣቸው እንዲሁም ፀጉረ ልውጦችና በመንግሥት መዋቅር ውስጥ ሆነው ለወንጀል ተባባሪ የሆኑ እንደሚገኙበት ጠቅሷል።
ይሁን እንጂ መንግሥት እያካሄደ ያለውን የጅምላ እስር ተፎካካሪ ፓርቲዎችና የሰብዓዊ መብት ተቋማት ኮንነውታል።
የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ግንቦት 14/2014 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ፣ የፌደራል መንግሥትና የፀጥታ ኃይሎች "በተቀናጀ መንገድ የሕግ የበላይነትን ማስከበር በሚል ባለፉት ቀናት መውሰድ በጀመሩት እርምጃ" ጋዜጠኞችንና የማኅበረሰብ አንቂዎችን ጨምሮ በርካታ ሰዎች ታስረዋል" ሲል ድርጊቱ ያለ ፍርድ ቤት ትዕዛዝ መፈፀሙን ኮንኗል።
የጋዜጠኞች መብት ተሟጋቹ ተቋም፣ ሲፒጄም የኢትዮጵያ ባለሥልጣናት በቅርቡ የታሰሩ ጋዜጠኞችና የሚዲያ ባለሙያዎች እንዲፈቱና ትንኮሳው እንዲቆም ጠይቋል።
የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ ( አብን)፣ እናት እና ባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ፓርቲዎችም በዚሁ ዘመቻ አባላቶቻቸው እንደታሰሩባቸው ገልጸው፣ እስሩ በሕግ አግባብ እንዲከናወን አሳስበዋል።
በአማራ ክልል የሚካሄደው "ሕግ ማስከበር" ወይስ "ፋኖን ማሳደድ?"
ለደኅንነታቸው ሲባል ስማቸው እንዲገለጽ ያልፈለጉ የሞጣ ከተማ ነዋሪ፣ ባለፈው ሳምንት በከተማዋ ለሰዎች መገደልና መቁሰል ምክንያት የሆነው ግጭት የተፈጠረው "መንግሥት ፋኖን ለማሳደድ በመሞከሩ ነው" ይላሉ።
ቀደም ብሎ ታስረው የነበሩ ፋኖዎች እንዲፈቱ ለመጠየቅ በተደረገ የተቃውሞ ሰልፍ ላይ ቢያንስ ስድስት ሰዎች መገደላቸውና ቢያንስ 13 ሰዎች መጎዳታቸውን ነዋሪው ተናግረዋል። ለተሻለ ሕክምና ወደ ባሕር ዳር የተላኩ በመኖራቸው ቁጥሩ ከዚህም ሊበልጥ ይችላል ብለዋል ነዋሪው።
"በከተማዋ የታሰሩት ወጣቶች በማኅበረሰቡ ላይ ያደረሱት ነገር የለም፤ ሕገ ወጥ ድርጊት ላይም አልተሳተፉም። የአካባቢውን ፀጥታ በማስጠበቅ፣ ሌሎችንም ወጣቶች በማነጽ ሚና የነበራቸው እንዲሁም 'በህልውናው ዘመቻ' ላይ ተሳትፎ የነበራቸው ናቸው" ብለዋል።
በመሆኑም መንግሥት የታሰሩት ወጣቶች በምን ወንጀል ተጠርጥረው እንደታሰሩ በይፋ ባለመግለጹ የአካባቢው ማኅበረሰብ "ልጆቹን አትንኩ!" በሚል መቃወሙን ነዋሪው ተናግረዋል።
ነዋሪው መንግሥት የጅምላ እስር እየፈፀመ ያለውም "ኢ-መደበኛ አደረጃጀት በሚል ስም ነው" ብለዋል።
በሞጣ ከተማ ከአንድ ወር ገደማ በፊትም በተፈጠረ ተመሳሳይ ግጭት የሰዎች ሕይዎት ማለፉን ያስታወሱት ነዋሪው፣ እስሩም በድብቅ ስለሚፈፀም የታሰሩት ወደ የት እንደተወሰዱ ቤተሰቦቻቸው መረጃ እንደሌላቸውም አክለዋል።
ለደኅንነቱ ሲባል ስሙን የማንጠቅሰው የወልዲያ ከተማ ነዋሪ ግን "መንግሥት ፋኖን እያሳደደ ነው" የሚለው ሀሳብ በከተማዋ ፋኖዎች በአደባባይ ሰልጥነው፣ ተመርቀው ወደ ግንባር ሲሸኙ ከሚያየው ሁኔታ ጋር እንደሚጋጭበት ተናግሯል።
"መንግሥት ፋኖን እያሳደደ አይደለም፤ በውስጥ የተደራጀ ሌላ ነገር ያለ ይመስለኛል" ሲልም ጥርጣሬውን ገልጿል።
ባለፈው ሳምንት የተመረቁ ፋኖዎች በአደባባይ ተጨብጭቦላቸው ወደ ግንባር መሸኘታቸውን የተናገረው ነዋሪው፣ "በደፈናው መንግሥት ፋኖን እያሳደደ ነው ለማለት እቸገራለሁ" ብሏል።
"በክልሉ ሆነ በፌደራል መንግሥቱ እምነት ያጣ እና ከፋኖ ተለይቻለሁ የሚል ቡድን አለ። ይህ ቡድን መከላከያውንም ልዩ ኃይሉንም አያምንም" በማለትም ምንም እንኳን እርሱም መንግሥትን እንዳያምን የሚያደርጉት በርካታ ችግሮች ቢኖሩትም "እነርሱ ግን ይህንን በተግባር ያሳያሉ። ለመንግሥትም ታዛዥ አይደሉም" ሲል ያስረዳል።
ዘመቻውን ተከትሎ በከተማዋ ፍተሻዎች እንደነበሩና በርካታ የፀጥታ አካላትም በብዛት ይታዩ እንደነበርም ነዋሪው ለቢቢሲ ተናግሯል።
የሰሜን ወሎ ዞን መቀመጫ በሆነችውና ጦርነቱን ተከትሎ በህወሓት ኃይሎች ለአምስት ወራት ተይዛ በነበረችው ወልዲያ ከተማ፣ በተለያዩ ጊዜያት ፋኖዎች በአደባባይ ሲሰለጥኑና ሲመረቁ የሚያሳዩ ተንቀሳቃሽ ምስሎች በማኅበራዊ ሚዲያዎች ተጋርተዋል።
ሌላኛው ያነጋገርናቸው የከተማዋ ነዋሪም ከአንድ ሳምንት በፊት "መንግሥት የሚያካሂደው ዘመቻ ያልተዋጠላቸው ወገኖች ፋኖን እንዲሁም የአማራን ሠራዊት ለመበተን ነው" ሲሉ ተቃውሞ ማካሄዳቸውን ገልጸው፣ መንገድ መዝጋት፣ የፖሊስ መኪና መደብደብ እና ወደ ፖሊስ ጣቢያ በመሄድ ታስረዋል ያሏቸውን የፋኖ አመራሮች ለማስፈታት ሙከራ ሲያደርጉ ግጭት መከሰቱን አስታውሰዋል።
እኚህ ነዋሪ እንደሚሉት ከሆነ በከተማዋ በመንግሥት ሥርዓት አንገባም እና የጦር መሣሪያ አናስመዘግብም ያሉ ለብቻቸው የሚሰለጥኑ ወጣቶች አሉ።
በአሜሪካ የአማራ ማኅበር የአድቮኬሲ ዳይሬክተር የሆኑት አቶ ሆነ ማንደፍሮ ግን በአዲስ አበባ እና በክልሉ በመንግሥት እየተካሄደ ያለው ዘመቻ፣ "የዐቢይን አስተዳደር የሚቃወምን ኃይል የማጥፋት እንቅስቃሴ ነው" ሲሉ ከሰዋል።
ዳሬክተሩ ለዚህ ገለጻቸው በጦርነቱ ወቅት ህወሓትን በመዋጋት ከፍተኛ ሚና የነበራቸው የቀድሞ የአማራ ልዩ ኃይል አዛዥ ብርጋዴር ጄኔራል ተፈራ ማሞ እና ምክትላቸው የነበሩን ምክትል ኮሚሽነር ቢሰጥ ጌታቸውን ጨምሮ፣ የዩኒቨርስቲ መምህራን፣ በተለያዩ ወረዳዎች የሚገኙ የጽህፈት ቤት ኃላፊዎች፣ የሚዲያ ኮሜንታተሮች፣ ጋዜጠኞች፣ የተፎካካሪ ፓርቲ አባላትና በተለይ በአማራ ሕዝብ ዘንድ ተሰሚነት ያላቸው ግለሰቦች መታሰራቸውን ዋቢ አድርገዋል።
እነዚህ ግለሰቦች መንግሥት የአማራን ሕዝብ ከጥቃት መከላከል አለመቻሉንና ከህወሓት ጋር በድብቅ ድርድር መጀመሩን የሚተቹ መሆናቸውንም ዳይሬክተሩ አክለዋል።
ባሳለፍነው ጥር ወር ላይ የህወሓት መሪ ደብረጽዮን ገ/ሚካኤል (ዶ/ር) በህወሃትና በኢትዮጵያ መንግሥት መካከል ቀጥተኛ ያልሆነ ንግግር እየተደረገ መሆኑን ለቢቢሲ ተናግረው ነበር።
ደብረጽዮን ገብረሚካኤል (ዶ/ር) ይህ እየተደረገ ያለው ቀጥተኛ ያልሆነ ንግግር የተወሰነ ውጤት እያሳየ መሆኑንም ጨምረው መግለጻቸው ይታወሳል።
እየተካሄደ ነው ስለተባለው ቀጥተኛ ያልሆነ ውይይትን በተመለከተ ከኢትዮጵያ መንግሥት በኩል በግልጽ የተባለ ነገር የለም።
መንግሥት በተለያዩ ጊዜያት 'ኢ-መደበኛ አደረጃጀት' ሲል የሚጠራቸውን ቡድኖች በሕገ ወጥ የመሣሪያ እና የገንዘብ ዝውውር ይከሳል።
በቅርቡም የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዶ/ር ለገሰ ቱሉ በሰጡት መግለጫ፣ ክልሉን ሰላም ለመንሳት የሚንቀሳቀሱ ኃይሎችን መንግሥት እንደማይታገስ አስታውቀው ነበር።
መንግሥት በሕገ ወጥ ድርጊት የሚከሳቸው እና "ኢ- መደበኛ አደረጃጀት" የሚላቸው 'ፋኖዎች' መኖራቸውን ያንሳንላቸው አቶ ሆነ ማንደፍሮ፣ "በማንኛውም ማኅበረሰብ ውስጥ ወንጀለኞች ሊኖሩ ይችላሉ። እንዲህ ዓይነት ወንጀል የሚፈጽሙ ካሉ በይፋ መገለጽ አለበት። ከ5 ሺህ በላይ ሰው ታስሮ ወንጀለኞች ማለትም አስቸጋሪ ነው። አብዛኞቹ የታሰሩትም ለሕዝብ ሲታገሉ የነበሩ ሰዎች ናቸው" ሲሉ የመንግሥትን ክስ አጣጥለውታል።
በመሆኑም መንግሥት እያካሄደ ያለው ዘመቻ "በፋኖ ስም የሚሰሩ ወንጀለኞች" የሚል ስም በመስጠት "ፋኖን የማጥቃት ሙከራ" እንደሆነ እንደሚያምኑ ተናግረዋል።
በአማራ ክልል መንግሥት እየተወሰደ ያለውን ዘመቻ ተከትሎ ከ5 ሺህ በላይ ሰዎች መታሰራቸውንና ዘመቻው በመቀጠሉም ቁጥሩ ከዚህም በላይ ሊሆን እንደሚችል አቶ ሆነ ስጋታቸውን ገልጸዋል።
እየተካሄደ ያለውን እስር በተመለከተ ተፎካካሪ ፓርቲዎች ምን አሉ?
የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ ( አብን) ግንቦት 17/2014 ዓ.ም. በይፋዊ የፌስቡክ ገጹ ባወጣው መግለጫ፣ መንግሥት በሕግ ማስከበር ዘመቻው እያከናወነ ያለው እስር አሳስቦኛል ብሏል።
"ለብልሹ አሰራርና ለዘፈቀደ ውሳኔ የተጋለጠ" ሲል በተቸው ዘመቻም እስካሁን ከአራት ሺህ የሚበልጡ ነዋሪዎች እንደታሰሩ ገልጿል።
ከገዥው ፓርቲ የፖለቲካ እና የሃሳብ ልዩነት ያላቸውን ግለሰቦች የማሳደድ ሁኔታን መመልከቱን የገለጸው ፓርቲው፣ የፓርቲዬ አመራሮች እና አባላትም ታስረውብኛል ብሏል።
የክልሉ መንግሥት እያካሄደ ያለውን ዘመቻ በሕጋዊ መንገድ እንዲያከናውንም ፓርቲው ጠይቋል።
የቀድሞ የአብን አመራር የነበሩት ዶ/ር ደሳለኝ ጫኔ በተለያዩ የአማራ ክልል ዞኖች ከ19 በላይ የአብን አባላት እንደታሰሩ በመግለጽ ስም ዝርዝራቸውን በፌስቡክ ገጻቸው አስፍረዋል።
ፓርቲው በመግለጫው በጅምላ እየተካሄደ ያለው እስር እንዲቆም፣ በፖለቲካ አመለካከት ልዩነት የታሰሩ ግለሰቦች ያለ ቅድመ ሁኔታ እንዲፈቱ እንዲሁም የጦርነት ስጋት ባለበት ወቅት የአመጽ ጥሪ የሚያደርጉ አካላት ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ አሳስቧል።
ባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ፓርቲም ግንቦት 15/2014 ዓ.ም ባወጣው መግለጫ ከ12 የማያንሱ አባላቱና የአዲስ አበባ ወጣቶች እንደታሰሩበት ገልጿል።
ለእስር ከተዳረጉት መካከል ሃሳባቸውን በነጻ የሚገልጹ ወታደራዊ አዛዦች፣ ጋዜጠኞች፣ የታሪክና የፖለቲካ ምሁራን እንደሚገኙበት ፓርቲው ጠቅሷል።
መንግሥት እያካሄደ ነው የሚለውን "እስርና አፈና "ያወገዘው ፓርቲው፣ መንግሥት ከዚህ ድርጊቱ እንዲቆጠብና ያለ ሕግ አግባብ የታሰሩ ግለሰቦች በአስቸኳይ እንዲፈቱ ጠይቋል።
ከዚህም ባሻገር መንግሥት በፋኖ ላይ ከፍቶታል ያለውን "የክህደት ዘመቻ" እንዲቆም አሳስቧል።
እናት ፓርቲም ግንቦት 16/2014 ዓ.ም. በፌስቡክ ገጹ ባወጣው መግለጫ፣ በመንግሥት እየተካሄደ ነው ያለው አፈና "ፖለቲካዊና አምባገነናዊ ሥርዓትን ለማዋለድ የሚደረግ ነው" ሲል ኮንኖታል።
አራት አባላቱ እንደታሰሩበት የገለጸው ፓርቲው፣ ግለሰቦቹ በመንግሥት ተጠርጥረው ቢያዙ እንኳን ቤተሰቦቻቸው የት እንዳሉ በማያውቁበት፣ ፍርድ ቤት ባልቀረቡበትና ሕጋዊ ሥርዓትን ባልተከተለ ሁኔታ "መንግሥት እንደ አሸባሪ ቡድን ሰዎችን መሰወር ያቁም" ሲል ጠይቋል።
በአዲስ አበባም እንዲሁ ከ300 በላይ ሰዎች በሕገ ወጥ እንቅስቃሴዎች ተጠርጥረው በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ፖሊስ ያስታወቀ ሲሆን፣ በተጨማሪም ከዚህ ሕግ የማስከበር ዘመቻ ጋር ተያይዞ እስካለፈው ሳምንት ማብቂያ ድረስ ከ18 በላይ ጋዜጠኞች በፀጥታ ተይዘው መታሰራቸው ተዘግቧል።
የአማራ ክልል መንግሥት "የሕግ ማስከበር ዘመቻ" መጀመሩን ያስታወቀው ባለፈው ሳምንት ክልሉ በግለሰቦች እጅ የሚገኝ የጦር መሣሪያ ምዝገባ ሊካሄድ መሆኑን የክልሉ የሰላምና የጸጥታ ቢሮ ማስታወቁን ተከትሎ ነበር።
በተለይም በበርካታ አካባቢዎች በስፋት በተደራጀው "ፋኖ በተባለው መደበኛ ያልሆነ ታጣቂ ቡድን ስም ሕገ ወጥ እንቅስቃሴ በሚያደርጉ ግለሰቦችና ቡድኖች" ላይ እርምጃ እንደሚወሰድ መግለጹም ይታወሳል።












