የአል ጀዚራ ጋዜጠኛ ዌስት ባንክ ውስጥ በእስራኤል ጦር ተገደለች

ጋዜጠኛ ሽሪን አቡ

የፎቶው ባለመብት, Al Jazeera

የምስሉ መግለጫ, ጋዜጠኛ ሼሪን አቡ አቅላ የእስራኤል እና ፍልስጤም ግጭትን ላለፉት 15 ዓመታት ስትዘግብ ቆይታለች

ትውልደ ፍልስጤማዊ እና የአሜሪካ ዜግነት ያላት የዓለም አቀፉ የመገናኛ ብዙኃን ተቋም፣ አል ጀዚራ ጋዜጠኛ በወረራ በተያዘው ዌስት ባንክ ጄኒን ውስጥ በእስራኤል ኃይሎች ተተኩሶባት ተገለደለች።

መቀመጫውን ኳታር ያደረገው የዜና ተቋም አል ጀዚራ፣ የ51 ዓመቷ ዘጋቢው ሼሪን አቡ አቅላ በእስራኤል ወታደሮች "ሆን ተብሎ በጭካኔ" ተገድላለች ብሏል። ከእሷ በተጨማሪም ሌላ ባልደረባዋ በጥይት ተመቶ ቆስሏል።

የአስራኤል ጦር ሠራዊት ግን ጋዜጠኞችን ኢላማ አላደረኩም ሲል የቀረበበትን ክስ አስተባብሏል።

የአስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር እንዳሉት የተኩስ ልውውጥ በሚደረግበት ጊዜ ጋዜጠኞቹ በፍልስጥኤም ታጣቂዎች ተተኩሶባቸው ሳይመቱ አልቀሩም ብለዋል።

የፍልስጥኤም ፕሬዝዳንት ድርጊቱን "የግድያ ወንጀል" በማለት የእስራኤል መንግሥትን ተጠያቂ አድርገዋል።

የእስራኤል ጦር ጄናኒ ተብላ በምትጠራው ከተማ "በሽብር የተጠረጠሩ" ሰዎች ለመያዝ ዛሬ ወታደራዊ ዘመቻ ማካሄዱን ገልጿል።

"በእርምጃው ወቅት በርካታ ፍልጤማውያን ታጣቂዎች ተኩስ ከፍተዋል እንዲሁም ተቀጣጣይ ነገሮቹን ወደ ወታደሮች ወርውረዋል። ወታደሮቹም ወደ ታጣቂዎቹ ተኩስ በመክፈት ምላሽ የሰጡ ሲሆን የተመቱ አሉ" ብሏል።

የፍልስጤም ጤና ሚንስትር አቡ አክሌህ ጋዜጠኛ ሼሪን በዘገባ ሥራ ላይ ሳለች ጭንቅላቷን በጥይት መመታቷን ተናግረው፣ ከባድ ጉዳት ደርሶባት ወደ ሆስፒታል መወሰዷን ገልጸዋል።

ከሼሪን በተጨማሪ ፍልስጤማዊው አሊ ሳሙዲ የተባለ ጋዜጠኛ ጀርባው ላይ በጥይት የተመታ ሲሆን፣ ሆስፒታል ከደረሰ በኋላ ያለበት ሁኔታ ለሕይወቱ አስጊ አይደለም ብለዋል ሚኒስትሩ።

"የእስራኤል ጦር ኦፕሬሽንን ለመቅረጽ ነበር የሄድነው። በድንገት እንድንሄድ ወይም ቀረጻ እንድናቆም ሳይነግሩን ተኮሱብን" ማለቱን አል ጀዚራ ዘግቧል።

"የመጀመሪያው ጥይት እኔን መታኝ። ሁለተኛው ጥይት ሼሪንን መታት።"

አል ጀዚራ የጋዜጠኛዋን ሞት "ግልጽ ግድያ ነው" ብሎታል ባወጣው መግለጫ ላይ። "ዓለም አቀፍ ሕግጋትን በመተላለፍ የእስራኤል ወራሪ ኃይል . . . ጭካኔ በተሞላበት ሁኔታ የፕሬስ ልብስ ለብሳ የጋዜጠኝነት ሥራዋን እያከናወነች የነበረችውን ዘጋቢ ዒላማ አድርጓል" ብሏል።

አል ጀዚራ ዓለም አቀፉ ማኅብረሰብ ጋዜጠኛዋን 'ሆነ ተብሎ ዒላማ በማድረግ እና በመግደል' የእስራኤል መንግሥትን እንዲሁም የእስራኤል ጦርን ተጠያቂ እንዲያደርግ ጥሪ አቅርቧል።

የፍልስጤሙ መሪው ፕሬዝደንት ሞሐሙድ አባስ በጋዜጠኞቹ ላይ የተፈጸመውን ጥቃት አጥብቀው አውግዘዋል።

የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ናፍታሊ ቤኔት የአገሪቱ ጦር ሆነ ብሎ ጋዜጠኞቹን ዒላማ አድርጓል መባሉን "መሠረተ ቢስ ወንጀላ ነው" ሲሉ አጣጥለውታል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ አሁን ባለን መረጃ መሠረት በዘፈቀደ ሲተኩሱ የነበሩ የፍልስጤም ታጣቂዎች ለጋዜጠኛዋ ሞት ምክንያት ሊሆኑ ይችላሉ ብለዋል።

የእስራኤል እና ፍልስጤም ግጭትን ላለፉት 15 ዓመታት ስትዘግብ የቆየችው ጋዜጠኛዋ በመካከለኛው ምሥራቅ በስፋት ትታዋቃለች።

የአል ጀዚራ ጋዜጠኛ ኒዳ ኢብራሂም ሕይወቷ ያለፈው ጋዜጠኛ "እጅግ በጣም የተከበረች" ስትል ገልጻት፤ የሕልፈቷ ዜና "አብራዋት ለሚሰሩት ጋዜጠኞች ከፍተኛ ድንጋጤን የፈጠረ ነው" ብላለች።