በአንድ ጀንበር ከእውቅ ባለፀጎች በላይ ቢሊየነር የሆነው የሎተሪ እድለኛ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
እድለኛው በዩናትድ ኪንግደም ታሪክ 184 ሚሊዮን ፓዎንድ (ከ11 ቢሊየን ብር በላይ ) በሎተሪ እጣ አሸነፈ።
በስም ያልተጠቀሰው ይህ ግለሰብ ዩሮሚሊዮንስ የተባለውን ሎተሪ ጃክፖት አሸንፎ ነው የ184 ሚሊዮን ፓዎንድ ባለቤት የሆነው።
ትናንት ይፋ የሆነው የአሸናፊ ቁጥር 3, 25, 27, 28 እና 29 - እንዲሁም 4 እና 9 የእድል ቁጥር ሆነዋል።
ዩሮሚሊዮንስ ሎተሪ እአአ 2004 ላይ ከተዋወቀ ወዲህ እስካሁን ድረስ 15 እድለኞች ከ100 ሚሊዮን ፓዎንድ በላይ አሸናፊ ሆነዋል።
ይህ የሎተሪ እጣ አሸናፊ እንደ ሙዚቀኛዋ አዴል እና ቦክሰኛው አንቶኒ ጆስዋ ካሉ እውቅ ባለጸጎች በላይ በአንድ ለሊት ባለሃብት ሆኗል።
የእጣው አሸናፊ ገንዘቡን ከተቀበለ በኋላ ማንነቱን ይፋ ማድረግ ወይም አለማድረግ የሚለውን የሚወስን ይሆናል።
እአአ 2011 ላይ 161 ሚሊዮን ፓዎንድ ያሸነፉት ኮሊን እና ክሪስ ዌይር ማንነታቸውን ይፋ አድርገው ነበር።
ዌይር በሻነፉት የሎተሪ ገንዘብ የሚደግፉትን የእግር ኳስ ክለብ የመግዛት ውጥን እንዳላቸው ገልጸው ነበር።
እአአ 2019 ላይ 115 ሚሊዮን ፓዎንድ ያሸነፉት ፍራንሰስ ኮኖሊይ እና ባለቤቷ ፓትሪክ እስካሁን ድረስ በሎተሪ እጣ ከፍተኛውን ገንዘብ ያሸነፉ ጥንዶች ሆነው ቆይተው ነበር። ጥንዶቹ ከወር በፊት በሎተሪ እጣ ካገኙት ገንዘብ አብዛኛውን ሌሎችን ለመርዳታ አሳልፈው መስጠታቸውን አስታውቀዋል።












