በኢትዮጵያ የጦር ወንጀል ማስረጃዎች እንዲጠፉ እየተደረገ መሆኑን የዓይን እማኞች ተናገሩ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
- ፀሐፊ, ሉሲ ካሳ
- የሥራ ድርሻ, ጋዜጠኛ
በምዕራብ ትግራይ ውስጥ የተፈጸመ የዘር ማጽዳትን ለመሸፈን በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች አስክሬን እየተቃጠለ እንደሆነ የዓይን እማኞች ተናገሩ።
ከ15 የዓይን እማኞች ጋር በተደረገ ቃለ ምልልስ በተገኘው መረጃ መሠረት፣ የዘር ማጽዳት መከናወኑን ለመሸፈን ሆነ ተብሎ፣ በተደራጀ ሁኔታ፣ ማስረጃዎችን ለማጥፋት ሲባል የሰዎች አስክሬን እየተቃጠለ ይገኛል ተብሏል።
የትግራይ ተወላጆች በጦርነቱ ወቅት ተለይተው ጥቃት እየደረሰባቸው እንደሚገኝ የሚጠቁሙ በርካታ ሪፖርቶች እየወጡ ባለበት ወቅት ነው የአስክሬኖች መቃጠል ክስ የተሰማው።
የቀድሞው የዓለም አቀፉ ወንጀል ፍርድ ቤት ዐቃቤ ሕግ የነበሩት ፋቱ ቤንሱዳ የሚመሩት የተባበሩት መንግሥታት ገለልተኛ የመርማሪዎች ቡድን እንደሚሰማራ በሚጠበቅበት ወቅትም ነው ይህ ክስ የመጣው።
የምዕራብ ትግራይ አጎራባች የሆነው የአማራ ክልል የፀጥታ ኃይሎች በቁጥጥራቸው ስር ባደረጓቸው የምዕራብ ትግራይ አካባቢዎች፣ የፀጥታ ኃይሎቹ አዳዲስ የጅምላ ግድያ መቃብሮችን እየቆፈሩ እንደሆነ ተነግሯል።
መቃብሮቹን ቆፍረው፣ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን አስክሬን እንዳወጡና አስክሬኖቹን አቃጥለው አመዱን ከአካባቢው እያስወጡ እንደሆነ የዓይን እማኞች በስልክ በተደረገ ቃለ ምልልስ ገልጸዋል።
ባለሥልጣናት የጅምላ ግድያ መቃብሮች መቆፈራቸውን አምነዋል። ሆኖም ግን መቃብሮቹ የትግራይ ኃይሎች ብሔርን መሠረት ያደረገ የጅምላ ግድያ ባለፉት ዓመታት ስለመፈጸማቸው ማስረጃ ናቸው ብለዋል።
የጎንደር ዩኒቨርስቲ አጥኚዎች የጅምላ መቃብሮች እንዳገኙና እነዚህ መቃብሮች ከህወሓት ጋር የተያያዙ እንደሆኑ አስታውቀዋል።
የጦርነቱ ተሳታፊ ኃይሎች በአጠቃላይ የጅምላ ግድያ በመፈጸም ይወነጀላሉ።
የሰብአዊ መብት ተሟጋቾቹ አምነስቲ ኢንተርናሽናል እና ሂውማን ራይትስ ዋች በቅርቡ ባወጡት ሪፖርት፣ የአማራ ክልል ባለሥልጣናትና የደኅንነት አባሎች በአካባቢው የሚኖሩ የትግራይ ተወላጆች ላይ የዘር ማጽዳት መፈጸማቸውን ጠቁመዋል።
ያለፈው ኅዳር የተባበሩት መንግሥታት የሰብአዊ መብቶች ምክር ቤት፣ ሁሉንም የጦርነቱ ተሳታፊ ኃይሎች የሚመረምር ገለልተኛ ቡድን ለማቋቋም ውሳኔ አሳልፏል።
የኢትዮጵያ መንግሥት ውሳኔውን አጣጥሎ፣ ትብብር እንደማያደርግ ገልጿል። የተመድ ውሳኔ "ፖለቲካዊ ጫና ለማሳደር ያለመ ነው" ሲልም መንግሥት ተቃውሞውን አስታውቋል።
ለምርመራ ቡድኑ የሚውል ገንዘብ እንዳይሰባሰብ ለማድረግ መጋቢት ላይ ኢትዮጵያ ያደረገችው ጥረት አልተሳካም። ሩሲያ እና ቻይና የኢትዮጵያን ፌደራል መንግሥትን ደግፈው ገንዘቡ እንዳይሰበሰብ ጥረዋል።

የፎቶው ባለመብት, Reuters
"አስክሬኖች ተቃጥለዋል"
ለገለልተኛ መርማሪ ቡድኑ ገንዘብ በተፈቀደ በሦስተኛው ቀን፣ በምዕራብ ትግራይ የተፈጸሙ ወንጀሎችን ለመሸፈን ማስረጃ የማስወገድ ዘመቻ እንደተጀመረ የዓይን እማኞች ይናገራሉ።
በሁመራ የሚኖሩ የወልቃይት ተወላጅ "በሁመራ ከተማ ከሚገኘው ሐምሌ ሐሙሽተ ትምህርት ቤት ጀርባ ባለው አካባቢ 200 የትግራይ ተወላጆች በጅምላ ተቀብረዋል። እነዚህ ጦርነቱ ከተጀመረ በኋላ በነበሩት የመጀመሪያዎቹ ወራት የተገደሉ ንጹሃን ናቸው" ሲሉ ተናግረዋል።
በውጊያው ወቅት ከአካባቢው ሸሽተው የወጡ የትግራይ ተወላጆች አሉ። በግዳጅ ማቆያ የሚገኙም አሉ።
እዚያው የቀሩ የወልቃይት ተወላጆች ስለ ክስተቱ የዓይን እማኝ ምስክር ሰጥተዋል።
"ሚያዝያ 4 [እአአ] የአማራ ሚሊሻዎች እና ፋኖ አስክሬኖቹን ቆፍረው አወጡ። እንጨት ሰብስነው ከዚህ ቀደም ዓይተን የማናውቀው ነገር አፈሰሱና የሰበሰቡትን አስክሬኖቹን አቃጠሉ። ከዚያ አስክሬኖቹ አመድ ሆኑ።"
የእኚህ ዓይን እማኝ ምስክርነት ሌሎች የዓይን እማኞች ስለ ክስተቱ ከተናገሩት ጋር ተመሳሳይ ነው።
የአማራ ሚሊሻ እና ፋኖ በሌላ የሑመራ አካባቢ የተቀበሩ ሰዎችን አስክሬኖች እንዳወደሙ የዓይን እማኞቹ ተናግረዋል።
አንድ ሌላ የዓይን እማኝ "አስክሬኖቹ በግዳጅ ማቆያ ውስጥ የነበሩ የንጹሃን ሰዎች ናቸው። ከሁመራ የግብርና ተቋም ጀርባ በ100 የሚቆጠሩ ሰዎች በጅምላ ነበር የተቀበሩት" ብለዋል።
"አስክሬኖቹን ወደ ተቋሙ አስገብተው በእንጨትና በማናውቀው ኬሚካል አቃጠሏቸው። ይህን ሲያደርጉ ፊታቸውን በጭንብል ሸፍነውና ጓንት አጥልቀው ነበር።"
በምዕራብ ትግራይ የሚገኘው አደባይ ከተማ ውስጥም የሰዎችን አስክሬን በማቃጠል መረጃ የመሸሸግ ድርጊት እንደተፈጸመ የዓይን እማኞች ተናግረዋል።
አንድ የከተማዋ ነዋሪ "ሚያዝያ 10 [እአአ] የአማራ ሚሊሻዎች በአቡነ አረጋዊ ቤተ ክርስቲያን አራት የጅምላ መቃብሮችን ቆፍረዋል። 150 አስክሬኖች ነበሩ። ሰዎቹ የተገደሉት ነሐሴ ላይ በተፈጸመው የዘር ማጽዳት ነው። አስክሬናቸውን በመኪና ጭነው ወስደዋል። ወደየት እንደወሰዷቸው ግን አናውቅም" በማለት ገልጸዋል።
የዓይን እማኞች እንደሚሉት፣ በዚያው ቀን በአደባይ ከተማ ከሚገኝ የመንግሥት ቢሮ ጀርባ ያለ የጅምላ መቃብር ተቆፍሯል።
በዚህ የጅምላ መቃብር እአአ በጥቅምት 2021 39 ሰዎች መቀበራቸው ተነግሯል። ሰዎቹ አዲ ጎሹ በተባለ ከተማ የታገቱና ለማምለጥ ሲሞክሩ የተያዙ መሆናቸውም ተገልጿል።
አስክሬኖቹ በጭነት መኪና እንደተወሰዱና የት እንደደረሱ ግን እንደማይታወቅ የዓይን እማኞች ተናግረዋል።
በአከር በተባለ በቲርካን እና ራውያን መካከል የሚገኝ ከተማ ውስጥም ተመሳሳይ ድርጊት እንደተፈጸመ የዓይን እማኞች ምስክርነት ሰጥተዋል።
አንድ ነዋሪ "አስክሬኖቹ በበአከር ታስረው የነበሩ የ70 ንጹሃን ሰዎች ናቸው። የተገደሉት ከዘጠኝ ወራት በፊት ነው" ብለዋል።
"ሚያዝያ 11 [እአአ] የአማራ ሚሊሻዎች አስክሬናቸውን ቆፍረው አውጥተው በአማራ ክልል ወደሚገኘው ሳንጃ ከተማ ወስደዋቸዋል።"
የዓይን እማኞቹ እንደሚሉት፣ አስክሬኖችን በማቃጠል ማስረጃ ማስወገድ የተጀመረው እአአ ሚያዝያ 4 ሲሆን፣ ይህም በጎንደር ዩኒቨርስቲ ባለሙያዎች ክትትል እየተደረገ ነው የተከናወነው።
"ከጎንደር ዩኒቨርስቲ ባለሙያዎች መጥተው ከጎበኙ በኋላ ነው የተጀመረው። ሲመጡ በነጭ ጄሪካን የተሞላ ኬሚካል ጭነው ነበር። ባለሙያዎቹ ለጥቂት ቀናት በከተማው ቆይተው የአማራ ሚሊሻዎች እንዴት አስክሬን ማስወገድ እንደሚችሉ አሳይተዋቸዋል። ከዚያም ተመለሱ" ሲሉ አንድ የዓይን እማኝ አስረድተዋል።
ሦስት ነዋሪዎች፣ የሚሊሻ አባላት የጎንደር ዩኒቨርስቲ በጉዳዩ እጁ እንዳለበት በግልጽ ሲናገሩ መስማታቸውን ተናግረዋል።
ስለ ግድያው መረጃ አይገኝም ብለው በድርጊታቸው ሲኩራሩ መስማታቸውንም አክለዋል።
ዩኒቨርስቲው ስለ ክሱ ምላሽ እንዲሰጥ ቢጠየቅም አስተያየት አልሰጡም።
ባለፈው ወር በመንግሥት የሚተዳደረው የቴሌቭዥን ጣቢያ ያስተላለፈው ዘገባ፣ ጎንደር ዩኒቨርስቲ 12 የጅምላ መቃብሮች ላይ ምርምር እያደረገ እንደሆነ ገልጿል።
እነዚህ የጅምላ መቃብሮች፣ ህወሓት በዘር ጭፍጨፋ እጁ እንዳለበት ጠቋሚ መሆናቸውም ተዘግቧል።
የሰዎችን አስክሬን ኬሚካል በመጠቀም ማስወገድ እንደሚቻል ባለሙያዎች ይናገራሉ።
በዩኒቨርስቲ ኮሌጅ ኦፍ ለንደን የኢንኦርጋኒክ ኬምስትሪ ፕሮፌሰር የሆኑት አንድርያ ሴላ እንደሚሉት፣ በከፍተኛ ሙቀት የሰዎችን አስክሬን አመድ ማድረግ (ክሪሜሽን) ይቻላል።
በጀርመን አርደብሊውቲኤች አቺን ዩኒቨርስቲ የኬሚካል ምህንድስና ዶክር ገብረኪዳን ገብረሥላሴ እንደሚገልጹት፣ የፎረንሲክ ማስረጃን በኬሚካል ማስወገጃ መንገድ አለ።
"እነዚህ ኬሚካሎች የፎረንሲክ ማስረጃ ያጠፋሉ። ግን ከአመድ ውስጥ የተወሰነ ማስረጃ ማግኘት ይቻላል። ሁሉንም ማስረጃ ማስወገድ አስቸጋሪ ነው።"
የጠቅላይ ሚኒስትር ቢሮ ስለጉዳዩ ማብራሪያ እንዲሰጥ ቢጠየቅም ምላሽ አልተገኘም።
ሆኖም ግን ከፍተኛ የአማራ አመራርና የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤው አገኘሁ ተሻገር፣ ማስረጃ ሆነ ተብሎ፣ በስልት እየተወገደ ነው የሚለውን ክስ አጣጥለዋል።
የመቃብር ቁፋሮ እየተደረገ እንደሆነ ግን አምነዋል። በመቃብር ቁፋሮው የተገኙት አስክሬኖች ባለፉት 40 ዓመታት የተገደሉ የአማራ ተወላጆች እንደሆኑ ተናግረዋል።
አቶ አገኘሁ "ህወሓት አገሪቱን እየመራ ስለነበር እነዚህ የጅምላ መቃብሮች ቆፍሮ አስክሬኖቹን ለዓለም ማሳየት አልተቻለም ነበር" ብለዋል። በምዕራብ ትግራይ የዘር ማጽዳት ተካሂዷል የሚለውን ውንጀላ እንዲሁም የአምነስቲ ኢንተርናሽናል እና የሂውማን ራይትስ ዋችን ሪፖርት አጣጥለዋል።
"ሐሰት ናቸው። መሬት ላይ ያለውን እውነታ ያላገናዘቡ ሪፖርቶች ናቸው" ሰሉም ምላሽ ሰጥተዋል።












