የታገቱ የካማሺ ዞን የማረሚያ ቤት ኃላፊዎችን ለማስለቀቅ እየተሞከረ እንደሆነ ተገለጸ

ቤኒሻንጉል ጉሙዝ

በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል የካማሺ ዞን የማረሚያ ቤት አዛዥ ተወካይን ጨምሮ ሦስት የጸጥታ አካላት በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ወለጋ ዞን በታጣቂዎች መታገታቸውን የክልሉ ኮሚሽን ለቢቢሲ ገለጸ።

ታጋቾቹን ለማስለቀቅም የኦሮሚያና የቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልሎች ጥረት መጀመራቸውን አስታውቀዋል።

የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ፖሊስ ምክትል ኮሚሽነር ምስጋናው እንጅፋታ ለቢቢሲ እንደገለጹት በማረሚያ ቤት ኃላፊዎቹ ላይ እገታው የተፈጸመው ባለፈው ሳምንት ሐሙስ መጋቢት 22፣ 2014 ዓ.ም ከአሶሳ ከተማ ወደ ካማሺ ዞን እየሄዱ ባሉበት ወቅት መንገድ ላይ ነው።

ሦስቱ ታጋቾች የት እንዳሉና በምን ምክንያት እንደታገቱ ሙሉ መረጃ ባይኖርም እስከ ትላንት በስቲያ ድረስ በሕይወት እንዳሉ መረጃ እንዳላቸው ምክትል ኮሚሽነሩ ተናግረዋል።

"በሌላ ስልክ አስደውለው በሕይወት እንዳሉና "አታስቡ" የሚል መልዕክትም ለቤተሰብ ማስተላለፋቸውን'" ምክትል ኮሚሽነሩ ለቢቢሲ ገልጸዋል።

በአሁኑ ወቅት ከኦሮሚያ ክልል ጋር እየተነጋገሩ እንደሆነና የክልሉም አባ ገዳዎች፣ የአገር ሽማግሌዎችና የሃይማኖት አባቶች ግለሰቦቹን ለማስለቀቅ ጥረት እያደረጉ ነው ብለዋል።

በካማሺ ዞን በኩልም የሃይማኖት አባቶችና የአገር ሽማግሌዎች ወደ ስፍራው አምርተው ቀጥታ ግንኙነት በማድረግ በውይይት ሰዎቹ እንዲለቀቁ ለማድረግም እቅድ እንዳለ አስታውቀዋል።

ከካማሺ ዞን በኩል የሚወከሉት እኚሁ የአገር ሽማግሌዎችና የሃይማኖት አባቶች ከዛሬ ጀምሮ ወደ ስፍራው እንደሚያመሩም አስታውቀዋል።

አጋቾቹ እነማን እንደሆኑ ከቢቢሲ ለቀረበላቸው ጥያቄ ምክትል ኮሚሽነር ምስጋናው ሲመልሱ " እስካሁን በግልፅ የደረስንበት ነገር የለም፤ ነገር ግን በመረጃ ደረጃ በአካባቢው ታጣቂው የኦነግ ሸኔ ኃይል በስፋት ይንቀሳቀሳል። የተለያዩ ግድያዎችንም እዛው መንገድ ላይ በተደጋጋሚ ይፈፅሙ ነበር። ጥርጣሬያችንም ኦነግ ሸኔ ነው የሚል ነው" ብለዋል።

በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል ካማሺና መተከል ዞኖችን ጨምሮ በተለያዩ ዞኖች ከዚህ ቀደም በታጣቂዎች በተደጋጋሚ በሚፈጸሙ ጥቃቶች ምክንያት በርካታ ሰዎች ለሞትና ለመፈናቀል ሲዳረጉ መቆየታቸው ይታወሳል።

የክልሉ መንግሥት እነዚህንም ጥቃቶች በመፈጸም ታጣቂውን የጉሙዝ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄን ተጠያቂ ሲያደርግ ቆይቷል።

ከዚህ ቀደም የቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልላዊ መንግሥትና ታጣቂው የጉሙዝ ሕዝብ ዴሞከራሲያዊ ንቅናቄ (ጉሕዴን) ቡድን በክልሉ በተደጋጋሚ በንፁሃን ላይ የሚፈጸሙ ጥቃቶችን ለማስቆም የመግባቢያ ሰነድ መፈራረማቸው ይታወሳል።