የየመን ተዋጊ ኃይሎች ለሁለት ወራት ተኩስ ለማቆም ተስማሙ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የተባበሩት መንግሥታት በየመን በጦርነት ተሳታፊ የሆኑ ተዋጊዎች ለሁለት ወራት የሚቆይ የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ መድረሳቸውን አስታውቀ።
ከእአአ 2016 ወዲህ በመላው የመን ተፈጻሚ የሚሆን የተኩስ አቁም ስምምንት ሲደረስ ይህ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው።
የየመኑ የእርስ በእስርስ ጦርነት በአገሪቱ ከፍተኛ የሆነ ሰብዓዊ እና ቁሳዊ ኪሳራ አስከትሏል። ተመድ በዚህ ጦርነት ምክንያት ወደ 400ሺህ የሚጠጉ ሰዎችን ሳይሞቱ አይቀርም ይላል።
ከእነዚህ መካከል 60 በመቶ የሚሆኑት በረሃብ፣ በመሠረታዊ የሕክምና አገልግሎት እጦት እና በንጹህ ውሃ አቅርቦት እጥረት ለሞት የተዳረጉ ናቸው።
ይህ በመላ አገሪቱ ተፈጻሚ ይሆናል የተባለው የተኩስ አቁም ስምምነት በሳኡዲ መራሹ ኃይል እና በኢራን በሚደገፉት የሁቲ አማጺያን መካከል የተደረሰ ነው።
የተኩስ አቁሙ ስምምነት ተፈጻሚ መሆን የጀመረው በእስልምና እምነት ተካታዮች የረመዳን ጾም ወር በመጀመሪያ ቀን ነው።
የአሜሪካው ፕሬዝደንት ጆ ባይደን በተባበሩት መንግሥታት አደራዳሪነተ የተደረሰው የተኩስ አቁም ስምምነት ለየመናውያን እረፍት ነው ብለዋል።
"ይህ መልካም እርምጃ ቢሆንም በቂ ግን አይደለም። የተኩስ አቁም ስምምነቱ መከበር አለበት። ከዚህ በፊት ተናግሬዋለሁ ይህን ጦርነት ማስቆም አለብን።" ብለዋል ባይደን።
የተባበሩት መንግሥታት ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉተሬዝ በበኩላቸው የተኩስ አቁም ስምምነቱ በአስቸኳይ ተግባራዊ እንዲደረግ ጠይቀዋል።
የተኩስ አቁም ስምምነቱ ይፋ የተገደረው በሪያድ የሰላም ንግግር ከተደረገ በኋላ ሲሆን፤ የተመድ ልዩ መልዕክተኛ ሃንስ ግሩንበርግ ተዋጊ ኃይሎች የአየር፣ የመድር እና የባህር ወታደራዊ እንቅስቃሴዎችን በየመን እና በድንበር አካባቢዎች ለማቆም ተስማምተዋል ብለዋል።
መርከቦች በሁቲ አማጺያን ቁጥጥር ሥር ወደምትገኝ አል-ሁዳይዳህ ወደብ መግባት እንዲችሉ እንዲሁም የመንገደኞች አውሮፕላን በሁቲ አማጺያን ስር በምትገኘው የየመን መዲና ሰነዓ እንዲያርፉ የተኩስ አቁም ስምምነቱ ላይ ተመልክቷል።
ሳኡዲ መራሹ ኃይል የየመን ይፋዊ መንግሥት በመደገፍ ከሁቲ አማጺያን ጋር ባለፉት 7 ዓመታት ሲዋጋ ቆይቷል።
የሁቲ አማጺያን በበኩላቸው ሰው አልባ አውሮፕላኖችን እና ሚሳኤሎችን በመጠቀም ሳኡዲ አረቢያን እና የተባበሩት አረብ ኤሜሬቶችን ሲያጠቁ ቆይተዋል።












