የሰብዓዊ እርዳታ ከወራት በኋላ በየብስ ወደ ትግራይ መደረሱ ተገለጸ

የፎቶው ባለመብት, WFP
ከታህሳስ 2014 ዓ.ም. አጋማሽ ወዲህ ለመጀመሪያ ጊዜ የሰብዓዊ እርዳታ በየብስ ትግራይ መድረሱን የዓለም ምግብ ፕሮግራም አስታወቀ።
ትናንት መጋቢት 23/2014 ከሰዓት በኋላ የሰብዓዊ እርዳታ የጫኑ 13 ተሸከርካሪዎች በሰላም የትግራይ መዲና መቀለ መድረሳቸውን የዓለም ምግብ ፕሮግራም አስታውቋል።
የዓለም ምግብ ፕሮግራም ተጨማሪ የሰብዓዊ እርዳታ የጫኑ መኪኖች ዛሬ ንጋት መቀለ እንደሚደርሱ ገልጿል።
የህወሓት ቃል አቀባይ ጌታቸው ረዳ፤ 20 መኪኖች ህወሓት ተቆጣጥሮ የሚገኝበት ስፍራ መግባታቸውን እና ወደ መቀለ እየተጓዙ እንደሆነ ትናንት አመሻሽ በትዊተር ገጻቸው ላይ አስፍረው ነበር።
ቃል አቀባዩ የሰብዓዊ እርዳታ የጫኑት መኪኖች ከወራት በኋላ ትግራይ መድረስ መቻላቸው አንድ በጎ እርምጃ ቢሆንም ዋናው ጉዳይ "ምን ያክል መኪኖች ተፈቀደላቸው ሳይሆን፤ ድጋፍ ለሚያስፈልጋቸው ያልተገደበ የሰብዓዊ እርዳታ እንዲኖር የሚያስችል ስርዓት አለ ወይ የሚለው ነው" ብለዋል።
በትግራይ በሚሊዮን የሚቆጠር ሕዝብ አስቸኳይ የሰብዓዊ እርዳታ እንደሚሻ የእርዳታ ድርጅቶች ሲገልጹ ቆይተዋል።
በሳለፍነው ሳምንት የፌደራሉ መንግሥት የሰብዓዊ እርዳታ ለማድረስ ሲል ግጭት ለማቆም መወሰኑን ተከትሎ ህወሓት ተመሳሳይ እርምጃ ወስዷል።
ምንም እንኳ ሁለቱ ተዋጊ ኃይሎች ለሰብዓዊነት ሲባል ግጭት ለማቆም ቢስማሙም ለቀናት እርዳታ ትግራይ ሳይደርስ ቆይቷል። ለዚህም ህወሓት እና የፌደራሉ መንግሥት አንዱ ሌላኛውን ተጠያቂ ሲያደርጉ ነበር።
የዓለም ምግብ ፕሮግራም በበኩሉ ከወራት በኋላ ይህ የሰብዓዊ እርዳታ ትግራይ ማድረሱን "እጅግ አስፈላጊ የሆነ መልካም እርምጃ ነው" ብሎታል።
ይህ ጽሑፍ በX. የቀረበ ይዘት ይዟል። ገጹ ቴክኖሎጂዎች ወይም ኩኪዎች ሊኖረው ስለሚችል ገጹ ከመከፈቱ በፊት የእርስዎን ፍቃድ እንጠይቃለን። ፍቃድዎን ከመስጠትዎ በፊት የX ኩኪ ፖሊሲ እና የ ማንበብ ይፈልጉ ይሆናል። ይዘቱን ለማንበብ ‘እቀበላለሁ ቀጥል’ የሚለውን ይምረጡ።
የ X ይዘት መጨረሻ
እርዳታ የጫኑት መኪኖች የደኅንነት ስጋት ሳያጋጥማቸው ትግራይ መድረስ በመቻላቸው የዓለም ምግብ ፕሮግራም እና አጋሮቹ የፌደራሉን እና የአፋር ክልል መንግሥት እንዲሁም የአፋር ማሕብረሰብ አባላትን አመስግነዋል።
የሰብዓዊ እርዳታ ለሚያስፈልጋቸው 5 ሚሊዮን ሰዎች ለመድረስ የእርዳታ መጠኑን እና ፍጥነቱን በመጨመር የአቅርቦት ስራውን ማስቀጠል አለብን ብሏል የዓለም ምግብ ፕሮግራም።












