'በስምምነት' እግሩ በመጋዝ የተቆረጠው አውስትራሊያዊ ሕይወቱ አለፈ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በሰሜን ምሥራቅ አውስትራሊያ 'በስምምነት' እግሩ በመጋዝ የተቆረጠው አውስትራሊያዊ አዛውንት ሕይወቱ ማለፉን ፖሊስ አስታወቀ።
እንደፖሊስ መረጃ ከሆነ ሟች እና የ36 ዓመቱ ተጠርጣሪ እግር የሚቆርጥበት ሁኔታን በተመለከተ አንዳች አይነት ስምምነትና 'ቅድመ ዝግጅት' ነበራቸው።
የ66 ዓመቱን አዛውንት እግር በባትሪ ኃይል በሚሰራ መጋዝ ቆርጧል የተባለው ግለሰብ በፖሊስ ቁጥጥር ሥር ከዋለ በኋላ በግድያ ወንጀል ክስ ተመስርቶበታል።
እንደ ፖሊስ ከሆነ ሁለቱ ግለሰቦች ቀድሞ የሚተዋወቁ ሲሆን፤ ሟቹ እግሩ በመጋዝ ሲቆረጥ እራሱን ለመከላከል ያደረገው ጥረት የለም።
መርማሪ ፖሊስ ጋሪ ሃንተር "ፖሊስ ሆኜ በሠራሁባቸው 34 ዓመታት ውስጥ እንዲህ አይነት ሁኔታ አጋጥሞኝ አያውቅም" ሲሉ ለአውስትራሊያ መገናኛ ብዙኃን ተናግረዋል።
መርማሪው ፖሊስ ድርጊቱን "አሳዛኝ" በማለት ገልጸው የሟች እግር ለምን እንደተቆረጠ እስካሁን ግልጽ አይደለም ብለዋል።
ፖሊስ ክስተቱን በተመለከተ ዝርዝር መረጃ ከመስጠት ተቆጥቧል።
የ66 ዓመቱ ግለሰብ እና በግድያ ወንጀል ክስ የተመሰረተበት የ36 ዓመት ተጠርጣሪ ቅዳሜ ማለዳ በሰሜን ኩዊንስላንድ በምትገኘው በኢንስፌይል መናፈሻ ስፍራ ተገኝተው ነበር።
ቀድሞውኑ ይተዋወቁ የነበሩት ሁለቱ ሰዎች፤ አብረው በመኪና ወደ ፓርኩ አቅንተው ለ20 ደቂቃዎች ያክል ዛፍ ስር ተቀምጠው ከቆዩ በኋላ የ36 ዓመቱ ግለሰብ የሌላኛውን እግር በመጋዝ ከጉልበቱ በታች ቆርጦታል ብሏል ፖሊስ።
ተጠርጣሪው እግሩ የተቆረጠውን ግለሰብ መኪና ውስጥ ተመልሶ እንዲገባ ከረዳው በኋላ ከአካባቢው በእግሯ ተሰውሯል።
መንገደኛ የተጎዳውን ሰው ተመልክቶ ለድንገተኛ አደጋ አገልግሎት ቢደውልም የ66 ዓመቱ አዛውንት ብዙም ሳይቆዩ ሕይወታቸው አልፏል።
ተጠርጣሪው ዛሬ ፍርድ ቤት ይቀርባል።












