በርካታ ሃገራት ዜጎቻቸው ዩክሬንን ጥለው እንዲወጡ ማስጠንቀቂያ ሰጡ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
ምዕራባዊያን ሩሲያ ጥቃት ልትሰነዝር ነው ማለታቸውን ተከትሎ በርካታ ሃገራት ዜጎቻቸው ዩክሬንን ጥለው እንዲወጡ ማስጠንቀቂያ ሰጥተዋል።
አሜሪካ፣ ዩኬ እና ጀርመን ዜጎቻቸው ኪዬቭን ለቀው እንዲወጡ ካሳሰቡ መካከል ናቸው።
ሞስኮ 100 ሺህ የሚገመት ወታደር ዩክሬን ድንበር ላይ ብታሰልፍም ዘልቄ የመግባት ሐሳብ የለኝም ስትል አስተባብላለች።
የአሜሪካው ፕሬዝደንት ጆ ባይደን የሩሲያው ፕሬዝደንት ቭላድሚር ፑቲንን በስልክ አግኝተው ወረራው ጦስ አለው ሲሉ አንዳስጠነቀቋቸው ተሰምቷል።
የዩክሬኑ ፕሬዝደንት ቮሎድሚር ዜሌንስኪ ወረራ አለ እየተባለ የሚነዛው ወሬ ሰዎችን ያስደነግጣል። ይህ ደግሞ ጠላት የሚፈልገው ነው ብለዋል።
ዋይት ኃውስ ወረራው በየትኛውም ጊዜ ሊፈፀም ይችላል የሚል ማስጠንቀቂያ የሰጠ ሲሆን ከአየር ላይ በሚጣል ቦምብ ሊጀምር እንደሚችልም ጠቁሟል።
አስፈላጊ ካልሆነ ሁሉም የአሜሪካ ኤምባሲ ሠራተኞች ዋና ከተማዋ ኪዬቭን ጥለው እንዲወጡ የታዘዙ ሲሆን የቆንስላ አገልግሎት ደግሞ ከዛሬ ሰንበት ጀምሮ ይቋረጣል።
ነገር ግን የአደጋ ጊዜ ሥራዎችን ለማቀላጠፍ አነስተኛ የቆንስላ ፅ/ቤት ልቪቭ አንደሚከፈት አሜሪካ ተናግራለች።
ካናዳም እንዲሁም የኤምባሲ ሠራተኞቿን ልቪቭ ወደተሰኘው ከፖላንድ ጋር ወደምትዋሰነው የድንበር ከተማ ያሸሸች ሲሆን በዩክሬን የዩኬ አምባሰደር ሜሊንዳ ሲመንስ ደግሞ ወሳኝ ቡድኑ ኪዬቭ እንደሚቆይ ገልጠዋል።
ሩሲያ በበኩሏ ከኪዬቭ አሊያም ከሶስተኛ ሃገር ትንኮሳ ሊኖር ስለሚችል ዩክሬን ያሉ ዲፕሊማቶቿን ልትቀንስ እንደምትችል ጠቁማለች።
አሜሪካ፤ የዩክሬን ወታደሮችን ሲያሰለጥኑ የነበሩ 150 ወታደሮችን አስወጥታለች።
የኔዘርላንድስ አየር መንገድ የሆነው ኬኤልኤም ደግሞ ወደ ዩክሬን መብረሬን አቁሜያለሁ ብሏል።
ፕሬዝደንት ዜሌንስኪ ምዕራባዊያን ስለወረራው ጠብሰቅ ያለ ማስረጃ ያላቸው እንደሁ ገና አላየሁም ብለዋል።
"እኔ እንደሚመስለኝ መገናኛ ብዙሃን ስለጦርነቱ በጣም ብዙ መረጃ አላቸው" ብለዋል ፕሬዝደንቱ።
"ያለውን አደጋ እንረዳለን። እርስዎ ወይም የሚያውቁት ሰው መቶ በመቶ አስተማማኝ የሆነ መረጃ ስለሩሲያ ወረራ ካለዎ እባክዎ ያጋሩን።"
አውስትራሊያ፣ ጣልያን፣ እስራኤል፣ ኔዘርላንድስና ጃፓን ዜጎቻቸው ዩክሬንን ጥለው በአስቸኳይ እንዲወጡ ካዘዙ ሃገራት መካከል ናቸው።
አንዳንድ ሃገራት ዲፕሎማቶችና ቤተሰቦቻቸውን ከዩክሬን አስወጥተዋል።
ፕሬዝደንት ባይደን ለፕሬዝደንት ፑቲን ባስተላለፉት መልዕክት ወረራው "ፈጣንና ከባድ ዋጋ ሩሲያን ያስከፍላታል" ብለዋል ሲል ዋይት ኃውስ ዘግቧል።
"ዩናይትድ ስቴትስ ለዲፕሎማሲ ዝግጁ የሆነችውን ያክል ለሌለችም እርምጃዎች ዝግጁ ናት" ማለታቸውንም አክሏል።
የፈረንሳዩ ፕሬዝደንት ኢማኑዔል ማኽሮን ቅዳሜ ዕለት ከፑቲን ጋር ባደረጉት የስልክ ልውውጥ "ከልብ የመነጭ ውይይት ከጦርነት ጡዘት ጋር የሚነፃፀር አይደለም" ሲሉ እንደነገሯቸው የፈረንሳይ ኤምባሲ ፅፏል።












