ኤለን መስክ ያስወነጨፋት ሮኬት ከጨረቃ ጋር ልትጋጭ ነው

ስፔስ ኤክስ ሮኬት

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የኤለን መስክ ሕዋ ምርምር ተቋም ያስወነጨፋት አንዲት ሮኬት ከጨረቃ ጋር ተጋጭታ ልትፈነዳ እንደምትችል ተሰምቷል።

ፋልከን 9 የተሰኘችው ሮኬት ወደ ሕዋ የተወነጨፈችው በፈረንጆቹ 2015 ሲሆን ነገር ግን የያዘችው ነዳጅ በመገባደዱ ምክንያት ተልዕኮዋን ጨርሳ ወደ ምድር ከመመለስ ይልቅ ሕዋ ላይ ስትዋልል ነበር።

ጠፈርተኛው ጆናታን ማክዶዌል፤ ከጨረቃ ጋር የተጋጨች የመጀመሪያዋ ከቁጥጥር ውጭ የሆነች ሮኬት ትሆናለች ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ሮኬቷ ከጨረቃ ጋር መጋጨቷ ያለው ፋይዳ ይህን ያህል የሚባል አይደለም።

ከሰባት ዓመታት በፊት ሥራዋን ጨርሳ ሕዋ ላይ የተረሳችው ሮኬት ከ1.6 ኪሎ ሜትር በላይ ርቀት አዳርሳለች።

ስፔስኤክስ የተባለው የኤለን መስክ የሕዋ ምርምር ተቋም ወደፊት ሰዎች በሌሎች ፕላኔቶች ላይ እንዲኖሩ ማመቻቸት የሚል ዓላማ አለው።

ሮኬቷ ከ2015 ጀምሮ በተለያዩ የምድር፣ የጨረቃና የፀሐይ የስበት ኅይሎች አቅጣጫዋን እየቀያየረች ቆይታለች ይላሉ ጠፈርተኛው።

"የስበት ሕግን ተከትላ ከጥቅም ውጭ ሆና ነበር ማለት ይቻላል።"

ይህች ሮኬት ብቻ ሳትሆን ለተልዕኮ ተስወንጭፈው ዕቅዳቸውን ያሳኩ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሮኬቶች ሕዋ ላይ እየዋለሉ ይገኘሉ።

"ባለፈው አስር ዓመት ከቁጥጥራችን ውጭ የሆኑ ቢያንስ 50 ትላልቅ ሮኬቶች አሉ። ከዚህ በፊትም ሳናውቀው ተፈጥሮ ሊሆን ይችላል። ይሄኛው የመጀመሪያው የታወቀ ክስተት ይሆናል ማለት ነው" ይላሉ ማክዶዌል።

የፋልከን 9 ወደ ጨረቃ መገስገስ ሊታወቅ የቻለው ጋዜጠኛ ኤሪክ በርገርና የዳታ ተንታኙ ቢል ጌሪ ባደረጉት ክትትል ነው።

ሮኬቷ፤ በሚቀጥለው የፈረንጆቹ ወርሃ መጋቢት አራት ከጨረቃ ጋር እንደምትጋጭ ተገምቷል።

"4 ቶን የምትመዝን ከኋላ ሞተር ያዘለች ብረት ማለት ናት። ይህን ያህል ክብደት ይዛ በሰዓት ከ8 ሺህ በላይ ኪሎ ሜትር በላይ እየተጓዘች ስትጋጭ የሚፈጠረው ነገር አስደሳች አይሆንም" ሲሉ ያክላሉ።

ሮኬቷ ከተጋጨች በኋላ የጨረቃ መልክዓ ምድር ላይ አነስ ያለ ሰው ሰራሽ ጉደጓድ ትፈጥራለች።

ሶፍትዌር ተጠቅሞ ለምድር የቀረቡ ሕዋ ላይ ያሉ ቁሶችን የሚከታተለው ቢል ጌሪ ሮኬት መጋቢት 4 ከጨረቃ እንደምትጋጭ ገምቷል።

በፈረንጆቹ 2009 ፕሮፌሰር ማክዶዌልና ሌሎች ጠፈርተኞች መሰል ነገር ቢፈጠር ምን ሊከሰት ይችላል የሚለውን ሐሳብ በቤተ ሙከራ አዳብረውታል።

ይህ ማለት ሮኬቷ ከጨረቃ ጋር ስትጋጭ ሳይንቲስቶች ብዙም የሚማሩት አዲስ ነገር የለም ማለት ነው ይላሉ ፕሮፌሰሩ።

አክለው አሁን ምንም እንኳ ሕዋ ላይ እየዋለሉ ያሉ ቁሶች እየሄዱ ሲጋጩ ችግር ባይፈጥሩም ወደፊት ግን አደጋ ሊሆኑ ይችላሉ ይላሉ።

ሮኬቷ ከጨረቃ ጋር እስክትጋጭ ባለው ጊዜ የስበት ህግን ተከትላ ሕዋ ላይ ትንሳፈፋለች።