የዓለማችን ባለጸጋ ኤለን መስክ በዚህ ዓመት 11 ቢሊዮን ዶላር ግብር እከፍላለሁ አለ

የፎቶው ባለመብት, Pool
የዓለማችን ባለጸጋ ኤለን መስክ በያዝነው ዓመት 11 ቢሊዮን ዶላር እንደሚከፍል በትዊተር ገጹ አስፍሯል።
የቴስላ ኤሌክትሪክ መኪና እና የስፔስ ኤክስ የሕዋ ታክሲ ፈጣሪና ባለቤት ኤለን መስክ በቅርቡ ምን ያህል ግብር እንደሚከፍል በርካቶች በማኅበራዊ ሚዲያ መጠየቃቸውን ተከትሎ መነጋገሪያ ርዕስ ሆኖ ነበር።
በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ላይ የዲሞክራቲክ ፓርቲ የምክር ቤት አባሏ ኤልዛቤት ዋረን ኤለን መስክ "የሕዝቡን ሃብት ምንም ሳይሰጥ መጠቀም ማቆም አለበት" ብለው ነበር።
"ምን ያህል ግብር እንደምከፍል ማወቅ ለሚፈልጉ ሰዎች በዚህ ዓመት ከ11 ቢሊዮን ዶላር በላይ ግብር እከፍላለሁ" ሲል ቢልየነሩ መልሷል።
የቴስላ ኤሌክትሪክ መኪና እና የስፔስ ኤክስ የሕዋ ታክሲ መስራች ኤለን መስክ በአውሮፓውያኑ ዓመት መጀመሪያ የዓለማችን አንደኛ ባለጸጋ ሆኗል።
በብሉምበርግ ቢሊየነርስ ዝርዝር መረጃ መሰረት የኤለን መስክ ሃብት በገንዘብ ደረጃ 243 ቢሊዮን ዶላር ሲሆን፣ የኤሌክትሪክ መኪናው ቴስላ አንድ ትሪሊዮን የሚገመት ዶላርና ስፔስ ኤክስ ደግሞ 100 ቢሊዮን ዶላር ዋጋ እንዳለው ተቀምጧል።
ባለፈው ሳምንት ኤለን መስክ የታይም መጽሄት የዓመቱ ምርጥ ሰው ተብሎ ተመርጧል።
ይህንንም ተከትሎ ሴናተሯ በትዊተራቸው ላይ ባለጸጋውን በሚሸነቁጥ መልኩ መልዕክታቸውን አስፍረዋል "የዓመቱ ምርጥ ሰው' ግብር እንዲከፍልና በሌሎች ጫንቃ መረማመድን እንዲያቆም የተጭበረበረውን የግብር ኮድ እንለውጥ" በማለት አስፍረዋል።
ምንም እንኳን የሕግ አውጪው አካል ዕቅዶች በምክር ቤቱ ውስጥ ለጊዜው ተይዘው ቢቆዩም የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን በአገሪቱ ቱጃሮች ላይ ግብር መጨመር ይፈልጋሉ።
ሴናተሯ ዋረንን ጨምሮ አንዳንድ የምክር ቤት አባላት የአሜሪካ ባለጸጎች ከገቢያቸው ላይ ብቻ ሳይሆን ከንብረታቸው ላይ ለምሳሌ ከአክሲዮን ድርሻቸው ላይ ግብር ሊቆረጥባቸው ይገባል የሚለውን ሀሳብ ይደግፋሉ።
አብዛኞቹ የአሜሪካ ሀብታሞች ከደመወዛቸው ላይ በቀጥታ ግብር አይቆረጥባቸውም። ይልቁንም ሀብታቸውን በአክሲዮን ድርሻዎች እና በሌሎች ኢንቨስትመንቶች የሚያስቀምጡ ሲሆን እነዚህንም ንብረቶች እንደ ማስያዣነት በመጠቀም ብድር ይወስዳሉ።
ኤለን መስክ ለሴናተር ዋረን የትዊተር መልዕክት በሰጠው ምላሽ "በዚህ ዓመት በታሪክ ውስጥ ከየትኛውም አሜሪካዊ በበለጠ ግብር እከፍላለሁ" ብሏል።












