አሜሪካ በቻይና ድሮን አምራቹ ዲጄአይ ላይ ማዕቀብ ጣለች

የፎቶው ባለመብት, Reuters
አሜሪካ በቻይና የሰው አልባ አውሮፕላን (ድሮን) አምራቹ ዲጂአይ እና በሌሎች ሰባት የቻይና ኩባንያዎች ላይ ማዕቀቦችን ጥላለች።
በያዝነው ሳምንት ሐሙስ የአሜሪካ የፌደራል ግምጃ ቤት (ትሬዠሪ ዲፓርትመንት) ኩባንያዎቹን ከኢንቨስትመንት ከሚያገልበት ዝርዝር ውስጥ ያስገባቸው ሲሆን አሜሪካውያን ዜጎችም በነዚህ ኩባንያዎች ላይ ድርሻ እንዳይገዙም ሆነ እንዳይሸጡ ከልክሏል።
የዲጄአይ ሰው አልባ አውሮፕላን ቴክኖሎጂ በቻይና የኡይጉር ሙስሊሞች ክትትል ጥቅም ላይ ውሏል ተብሏል።
ሆኖም ዲጄአይ በአክሲዮን ባለቤትነት የተደራጀ ኩባንያ ስላልሆነ ዕቀባው ለይስሙላ ነው እየተባለ ነው።
ይህም ማለት በአሜሪካ ያሉ ሸማቾች የዲጄአይ ሰው አልባ አውሮፕላኖችን መግዛት እና መጠቀማቸውን መቀጠል ይችላሉ።
በመከላከያ የብሔራዊ ደህንንት ስጋት ነው ለተባለው ለዚህ ኩባንያ በአውሮፓውያኑ 2020 የአሜሪካ የንግድ ዲፓርትመንት የአሜሪካ ኩባንያዎች ምርቶችን እንዳይልኩ አግዷል።
ሆኖም እንደ ሮይተርስ የዜና ወኪል በኒውዮርክ ከተማ ፖሊስን ጨምሮ ከ900 በላይ የአሜሪካ የህዝብ ደህንነት ኤጀንሲዎች የዲጂአይ ምርቶችን ይጠቀማሉ።
የብሔራዊ ፓርክ አገልግሎት በካሊፎርኒያ የሰደድ እሳትን ለመዋጋት የዲጄአይ ድሮኖችን ተጠቅሟል።
ኩባንያው ባለፈው አመት በአሜሪካ ውስጥ በሰው አልባ አውሮፕላን ወደ 80 በመቶ የሚጠጋ የገበያ ድርሻ ነበረው ሲል ድሮን ኢንዱስትሪ ኢንሳይትስ ዘግቧል።
ግዙፉ የቴሌኮም ኩባንያ ሁዋዌ በትራምፕ አስተዳደር የአሜሪካ ኩባንያዎች የንግድ እንቅስቃሴ እንዳይያደርጉ በከለከለው የአሜሪካ የንግድ ማግለያ ዝርዝር ውስጥ አሁንም ይገኛል።
የባይደን አስተዳደር በቻይና ትልቁ 'ቺፕ' አምራች፣ በሆነው ሴሚኮንዳክተር ማኑፋክቸሪንግ ኢንተርናሽናል ኮርፖሬሽን (ስሚክ) ላይ ላይ ተጨማሪ ማዕቀብ ለመጣል እያሰበ መሆኑን ሮይተርስ ዘግቧል።












